ሐማስ የእስራኤልን መከላከያ ለማለፍ የተጠቀመው የ2ኛው የዓለም ጦርነት መሣሪያ

የፎቶው ባለመብት, Hamas
የእስራኤል እና የሐማስ ግጭት ከተጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል። ቅዳሜ ዕለት ሐማስ የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ የተጀመረው ግጭት ዓለምን እያነጋገረ ነው። አገራትንም ጎራ ለይተው እንዲቆሙ አድርጓቸዋል።
አሁንም ግን ሐማስ በአየር፣ በባሕር እና በምድር የእራኤልን ድንበር ጥሶ እንዴት ሊገባ እንደቻለ እንቆቅልሽ እንደሆነ ነው።
ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ሲከፍት የቡድኑ ታጣቂዎች ፓራሹት በመጠቀም ጥብቅ ጥበቃ የሚደረግለትን ድንበር ማለፍ ችለዋል።
የታጣቂ ቡድኑ ክንፍ የሆነው ኢዝ ዲን አል ቃሳም ብርጌድ ድንበሩን ጥሶ በመግባት በሙዚቃ ድግስ ላይ እየተዝናኑ የነበሩ ሰዎችን እንዲሁም በጋዛ ሰርጥ ዙሪያ ባሉ የእስራኤል ከተሞች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል። ድንገተኛ ጥቃቱንም ‘የአል አቅሳው ጎርፍ’ ብሎታል።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሪቻርድ ሔችት የፍልስጥኤም ተዋጊዎች በፓራሹት፣ በባሕር እና በየብስ መግባታቸውን አረጋግጠዋል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎችም የአል ቃሳም ብርጌድ ተዋጊዎች በፓራሹት ሲወርዱ አሳይተዋል።
ሆኖም ሐማስ እስራኤልን ለመውረር እንዲህ ዓይነት ስልት መጠቀሙ ሲታወቅ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የፍልስጥኤም ታጣቂዎች ጋዛን እና እስራኤልን የሚለየውን ጥብቅ የድንበር አጥር አንድ ወይም ሁለት ሰዎችን መያዝ የሚችሉ ፓራሹቶችን በመጠቀም በአየር ላይ ማለፍ ችለዋል።
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ስልት
የጦር ፓራሹቶች ብዙውን ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉት ለአንድ ሠራዊት ወታደሮችን፣ መሣሪያ አሊያም ሌሎች ቁሳቁሶችን ለማቀበል ነው። ዓላማውም ከጦር ግንባር ጀርባ ያሉትን የጠላት መስመሮች ሰብሮ በመግባት ለማጥቃት ነው።
የፓራሹት ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ ለውጊያ የተሰማሩትም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመን እና በአጋሮቿ ነበር። ጀርመን በዚህ ፈር ቀዳጅ እንደሆነች ይነገርላታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከ36 ዓመታት በፊት የተፈፀመው ጥቃት
የሐማስ የቅዳሜ ዕለቱ ጥቃት ከአስርት ዓመታት በፊት በፍልስጥኤም ነጻ አውጭ ግንባር ጠቅላይ ዕዝ፣ በሁለት ፍልስጥኤማውያን፣ በሶሪያዊ እና በቱኒዚያዊ የተካሄደውን ቀላል አውሮፕላን መሣይ በራሪ (ግላይደር) በመጠቀም የተፈፀመውን ጥቃት የሚያስታውስ ነው።
እነዚህ ተዋጊዎች እስራኤል ከሌባኖስ በምትዋሰንበት ደቡባዊ ድንበር በግላይደር ተንሳፈው በመግባት ነበር ጥቃቱን የፈፀሙት።
ታጣቂዎቹ እንደ አውሮፓውያኑ ኅዳር 1987 የእስራኤልን የጦር ሠፈር ለማጥቃት የተነሱት ከሊባኖስ ነበር።
በዚህ ጥቃት ስድስት የእስራኤል ወታደሮች ሲገደሉ ሰባቱ ደግሞ ቆስለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምድር ላይ ጥቃት
ሞተር እና አቅጣጫ መቆጣጠሪያ የተገጠመላቸውን ፓራሹቶች በመጠቀም ተዋጊዎቹ ከመሬት ላይ ሆነው ጥቃት መክፈት ችለዋል።
በዚህም ዳገት ላይ መንጠላጠል አሊያም ከጦር አውሮፕላን መውረድ ሳይጠበቅባቸው ወደፊት መጓዝ ችለዋል ማለት ነው።
ፓራሹቱ የተገጠመለት ሞተርም በሰዓት 56 ኪሎ ሜትር ለመጓዝ የሚያስችል ኃይል እንዲያገኝ ረድቶታል።
ፓራግላይደሮቹ በአማካይ ከመሬት በ5 ሺህ ሜትር ከፍታ ላይ ለሦስት ሰዓታት መብረር ይችላሉ።
እንደ ፓራግላይደር ድረ ገጽ ከሆነ እነዚህ ፓራግላይደሮች ከአራት ሰዎች ክብደት ጋር የሚስተካከል 230 ኪሎ ግራም ክብደትን መሸከም ይችላሉ።
ጃንጥላ የሚመስለው ይህ መንሳፈፊያ ለአንድ ሰው መቀመጫ አሊያም ሁለት ሰዎችን መያዝ የሚችል ባለ ሦስት ጎማ ጋሪ ሊኖረውም ይችላል።
በሐማሱ ኢዝ አል ዲን አል ቃሳም ብርጌድ የጦር ሚዲያ ላይ የተጋሩ ቅንጫቢ ቪዲዮች እያንዳንዳቸው በአንድ አሊያም በሁለት ተዋጊዎች የሚበሩ ፓራግላይደሮች ከመሬት ሲነሱ አሳይተዋል።
ሌላ ምስል ደግሞ ተዋጊዎቹ በእስራኤል ግዛት መሬት ላይ ከማረፋቸው እና ጥቃት ከመክፈታቸው በፊት በአየር ላይ ሆነው ሲተኩሱ አሳይቷል።
የተወሰኑት ፓራሹቶች በሞተር ሳይክል ላይ የተሳፈሩ ተዋጊዎችን ይዘው ነበር። ሐማስ ጋዛን ከእስራኤል ጋር የሚለየውን አጥር ጥሰው የገቡትን እና የአል አቅሳ ጥቃት ዘመቻ ክንፍ የሆነውን የፓራሹት ወታደሮች ቡድን “ሳቅር ስኳድሮን” ሲልም ጠርቷቸዋል።
የእስራኤል ጦር ፓራሹቶቹን ለምን መለየት አልቻለም ነበር?
በሐማስ ሚዲያ ላይ የተለጠፉ ቪዲዮዎች ከጋዛ የተነሱት የታጠቁት ፓራግላይደሮች ከጋዛ ሰርጥ በሚተኮስ መጠነ ሰፊ የሮኬት ጥቃት ሽፋን ተሰጥቷቸው ሲበሩ አሳይተዋል።
የተወሰኑት በዝቅተኛ ከፍታ፣ ሌሎቹ ደግሞ በከፍታ ሲበሩም ነበር። በጋዛ ሰማይ ላይ በዐይን በግልጽ መታየትም ይችላሉ።
ጦሩ ይህንን እንዴት መለየት እንዳልቻለ በእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እና በበርካቶች ዘንድ ጥያቄ አስነስቷል።
እስካሁን የእስራኤል ኃይሎች የአየር መከላከያቸው ማንም ተራ ሰው በግልጽ ተመልክቶ በስልኩ የቀረጻቸውን በተለይም በፓራሹት በአየር ላይ የሚበሩ ተዋጊዎችን አይቶ ያለመለየቱ ምክንያት ምን እንደሆነ አልገለጹም።
አይረን ዶም
አይረን ዶም (Iron Dome) የትኛውም የአየር ሁኔታ የማይበግረው ተንቀሳቃሽ የእስራኤል የአየር መከላከያ ሥርዓት ነው።
ይህ የአየር ጥቃት መከላከያ ሥርዓት ራፋኤል አድቫንስ ሲስተም በተባለ የእስራኤል ኤሮስፔስ ኩባንያ የተሠራ ሲሆን፣ እስከ 70 ኪሎ ሜትር ድረስ በአጭር ርቀት የሚተኮሱ ሮኬቶችን እና መድፎችን ማክሸፍ ይችላል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2011 ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው ይህ በአየር ላይ የሚመጡ ጥቃቶችን የመለየት እና የማክሸፊያ ሥርዓት እስራኤል ከፈጣሪ በታች የምትተማመንበት ጥቃት መመከቻዋ ነው ይባላል።
ሆኖም ሐማስ የቅዳሜ ዕለቱን ጥቃት የፈፀመው ይህንን ዘመናዊ የመከላከያ ሥርዓትን አልፎ ነው።
ይህም እስራኤሎች በዐይን ዕይታ ከሚደረጉ ቁጥጥሮች ይልቅ በቴክኖሎጂ ላይ ጥገኛ ናቸው ማለት ነው? የሚል ጥያቄን አጭሯል።
አንዳንድ ዘገባዎችም እንደ አይረን ዶም እና ራዳር ያሉ የእስራኤል የአየር መከላከያ ሥርዓቶች አነስተኛ የሆኑ በራሪ አካላትን ለመከታተል የተሰሩ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
የተቀናጀው ጥቃት
የአል ቃሳም ብርጌድ አዛዥ መሐመድ አል ዲፍ የመጀመሪያው ቀን ላይ በሰጡት መግለጫ ሐማስ ድንገተኛ ጥቃቱን የከፈተው 5 ሺህ ሮኬቶችን በመተኮስ ነው ብለዋል።
የሮኬት ጥቃቱ የሐማስ ተዋጊዎች በየብስ፣ የጦር ጀልባዎችን በመጠቀም በባሕር እና በአየር ደግሞ ፓራሹት በመጠቀም ሰርጎ መግባት ጋር የታጀበ ነበር።
መገናኛ ብዙኃን እና የጦር ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት የፓራሹቱ ጥቃት እና አየር መከላከያውን ማለፍ መቻላቸው ድንበሩን ጥሰው ለመግባት ዋናው ምክንያት ነው።
የመጀመሪያው ቀን ጥቃትም በእስራኤል በሰላማዊ ሰዎች እና ወታደሮች ላይ ከፍተኛ የሆነ እና ያልተጠበቀ ጉዳት አድርሷል።
ተዋጊዎቹ ከ100 በላይ እስራኤላውያንን እና የጦር ሠራተኞችን አግተው ወስደዋል።አሁን ላይ ሐማስ እነዚህን ታጋቾች እንደሚገድላቸውም እያስፈራራ ነው።
















