ማንቸስተር ዩናይት ከብራይተን፤ አስቶን ቪላ ከማንቸስተር ሲቲ. . . የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ግምት

ብራይተን ባለፉት ሦስት ዓመታት ወደ ኦልድ ትራፎርድ አቅንቶ ማንቸስተር ዩናይትድን ማሸነፍ ችሏል። ዘንድሮስ?
ዩናይትድ ባለፈው ሳምንት ሊቨርፑልን በማሸንፍ ድንቅ ውጤት ማስመዝገብ ቢችልም ወጥ አቋም አለማሳየቱ መተማመን እንዲጠፋ አድርጓል ብሏል የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን።
"ማንቸስተር አያሸንፍም ስል ሰዎች ቢናደዱብኝም ስለምንም ቡድኑን አምነዋለሁ?" ሲል ይጠይቃል።
ሱተን ይህንን ጨዋታ ጨምሮ ዛሬ፣ ቅዳሜ እና እሑድ የሚካሄዱ የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎችን እንደሚከተለው ገምቷል።
አርብ
ሊድስ ከ ዌስት ሃም
ኑኖ እስፕሪንቶ ሳንቶ ወደ ዌስት ሃም የመጡት ቡድኑን ከመውረድ ለማትረፍ ቢሆንም ከባድ ሥራ ይጠብቃቸዋል።
ከቡድኑ ደካማ መሆን አንጻር እንዴት ሊያሸንፉ ስል እጠይቃለሁ።
ሊድስ በጥሩ ጉዞ ላይ ባይገኝም ተፎካካሪ ቡድን መሆኑን አሳይቷል።
ጃሮድ ቦዌን ጎል እንደሚያስቆጥር ብገምትም የቡድኑ የተከላካይ መስመር ብዙ ክፍተቶች አሉበት።
ግምት፡ 2 -1
ቅዳሜ
ቼልሲ ከ ሰንደርላንድ
ቼልሲ መጀመሪያ ላይ ከገጠመው የውጤት ቀውስ በመውጣት አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችሏል።
ሰንደርላንድ በደንብ ተደራጀ ቡድን ቢሆንም ቼልሲ ሦስቱን ነጥቦች እንደሚያሳካ አስባለሁ።
ግምት፡ 2- 0
ኒውካስል ዩናይትድ ከ ፉልሃም
በሻምፒዮንስ ሊግም ቢሆን ኒውካስል በሜዳው ሲጫወት ሁሌም እንደሚያሽነፍ እገምታለሁ። ይህ ጨዋታም የተለየ አይደለም።
ፉልሃም በደንብ የተደራጀ ቡድን ሲሆን ባለፈው ዓመት ወደ ሴንት ጀምስ ፓርክ አቅንቶ ቢያሽንፍም በዚህ ጨዋታ ግን አያሳካውም።
ግምት፡ 3 - 1
ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ብራይተን
ጨዋታው መቆም ሲገባው በመቀጠሉ ማንቸስተር ዩናይትድ ባለፈው ሳምንት የመጀመሪያዋን ጎል ማስቆጠር ችሏል። ሊቨርፑልን ማሸነፉ ድንቅ ውጤት ቢሆንም የቡድኑን መሻሻል አያሳይም።
ሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታዎችን በሩበን አሞርም ስር ያሸንፋሉ ብዬ አላስብም።
ብራይተን ከሜዳው ውጭ ቢጫወትም ካለመፍራቱም በላይ አጥቂው ዳኒ ዌልቤክ ጎል የሚያስቆጥር ይመስለኛል።
ውጤት አስመዝግቦ ግምቴ ትክክል አለመሆኑን ማሳየት ያለበት ዩናይትድ ይመስለኛል።
ግምት፡ 1 - 2

ብሬንትፎርድ ከ ሊቨርፑል
ሊቨርፑል አጥቂው አሌክሳንደር አይዛክ ከፍራንክፈርት ጋር በነበረው የሻምፒዮንስ ሉግ ጨዋታ በመጎዳቱ ከዚህ ጨዋታ ውጭ የመሆን ዕድል አለው።
አጥቂው ወደ ቀያዮቹ ለመዘዋወር ሲል የቅድመ ውድድር ዝግጅቶችን ባለማድረጉ አቋሙ ከመውረዱም በላይ ጉዳት እያስተናገደ ነው።
ቡድኑ ፍራንክፈርትን ቢያሽንፍም አሁን የሚፈተንበት ጨዋታ ነው።
ብሬንትፎርድ ኳስ ይዞ መጫወት ቢመርጥም አሰልጣኝ ኬት አንድሪውስ ለእንደዚህ ዓይነት ጨዋታዎች መልሶ ማጥቃትን ይመርጣሉ።
የሊቨርፑል የአጥቂ መስመር በዚህ ጨዋታ ባይሆንም ወደ ውጤታማነት መመለሱ እንደማይቀር ብገምትም የተከላካይ ክፍሉ ግን ክፍተት አለበት።
ግምት፡ 1 - 1
እሑድ
በርንመዝ ከ ኖቲንግሃም ፎረስት
ሾን ዳይሽ ለፎረስት አለቃ ሆነው መሾማቸው ትክክለኛ እርምጃ ነው ብዬ አስባለሁ።
ዳይሽ በአጨዋወታቸው ከቀድሞው አሰልጣኝ አሰንጅ ፖስትኮግሉ ይልቅ ወደ ኑኖ እስፕሪቶ ይቀርባሉ። አሁን ትኩረቱ ቡድኑን በሊጉ ማቆየት ላይ ነው።
በጥሩ አቋም ላይ ከሚገኘው በርንመዝ ጋር የሚደረገው ይህ ጨዋታ ግን ለአሰልጣኙ ፈታኝ ይሆናል።
በርንመዝ በተለይም በሜዳው ዕድሎችን መፍጠር ይችላል።
ግምት፡ 1 - 0
አርሴናል ከ ክሪስታል ፓላስ
በዚህ ወቅት ማን አሚኬል አርቴታን ቡድን ሊያስቆም ይችላል?
አሁን መድፈኞቹን ሊገዳደር የሚችለው ፓላስ ሲሆን ይህንንም ከሊቨርፑል ጋር አስመስክረዋል።
ፓላስ ሐሙስ በአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ መጫወቱ ግን ከቡድን ጥልቀቱ አንጻር የሚጠቅመው አይመስልም።
የመድፈኞቹ የተከላካይ መስመር አስደናቂ እንቅስቃሴውን ቀጥሎበታል።
ግምት፡ 2 - 0

አስቶን ቪላ ከ ማንቸስተር ሲቲ
ኧሪሊንግ ሃላንድ ምን አይነት አስደናቂ ተጫዋች ነው።
ሲቲ ግን ወደ ድንቅ ብቃቱ የተመለሰውን ፊል ፎደንን እና ምርጡን ግብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ዶናሩማን አስፈርሟል።
እንደሲቲ ሁሉ ቪላም በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎችን በማሸነፉ ለፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን ፈተና ይሆናል።
ሲቲ ወደ ቪላ አቅንቶ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች በመሸነፉ ይህንን መርሐ ግብር በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ይመስለኛል።
ግምት፡ 1 - 1
ዎልቨስ ከ በርንሌይ
ዎልቭስ በሜዳው እና በደጋፊዎቹ ፊት ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይኖርበታል።
በርንሌይ ባለፈው ሳምንት ሊድስ አሸንፈው በጥሩ መንፈስ ላይ ይገኛሉ።
ይህንን ጨዋታ ካሸነፉ ለዎልቭስ ከባድ ውጤት ይሆናል።
ግምት፡ 2 - 0
ኤቨርተን ከ ቶተንሃም
ቶተንሃም እንደተጋጣሚው አጨዋወቱን እየቀያየረ ቢሆንም የቡድኑ የአትቂ መስመር ክፍተት አለበት።
ኤቨርተንም ተመሳሳይ አቀራረብ ቢኖረውም ጎሎችን የሚያስቆጥሩት አጥቂዎቹ አይደሉም።
ቡድኑ ምን አይነት አጥቂ ሊያገኝ ይችላል የሚለው አጠያያቂ ነው።
በእነዚህ ምክንያት ጨዋታው አቻ የሚጠናቀቅ ይመስለኛል።
ግምት፡ 1 - 1















