ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእስራኤል ጦር ከ325 ቀናት የሐማስ እገታ በኋላ አንድ ታጋችን ነጻ አወጣ
የእስራኤል ጦር ካኢደ ፋራን ኤልካዲ የተባለ ታጋችን ከ325 ቀናት የሐማስ እገታ በኋላ ነጻ መውጣቱን አስታወቀ።
ጦሩ ባወጣው መግለጫ በደቡባዊ ጋዛ “ውስብስብ በሆነ ወታደራዊ ኦፕሬሽን” የ52 ዓመቱን ታጋች ነጻ ማውጣቱን ገልጿል።
ጦሩ ለሌሎች ታጋቾች፣ በጋዛ ለሚገኙ ወታደሮቹ እና ለእስራኤል ብሔራዊ ደኅንነት ሲባል ስለዚህ ዘመቻ ተጨማሪ መረጃ አልሰጥም ብሏል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን የእስራኤል ጦር ካኢደ ኤልካዲ የታደገው ጥልቅ ከሆነ ዋሻ ውስጥ መሆኑን እየዘገቡ ይገኛሉ።
ግለሰቡ በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ሆስፒታል መወሰዱ ተዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በሆስፒታል ከሚገኘው ካኢደ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን ጽ/ቤታቸው ገልጿል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የወጣ መግለጫ “መላው የአገሪቱ ሕዝብ በካኢደ መመለስ ሐሴት አድርጓል” ይላል።
የታጋቹ ወንድም ካኢደ በሆስፒታል አልጋ ላይ ሆኖ የሚያሳያውን የመጀመሪያ ምስል አጋርቷል።
ቃኢደ ፋረሃን የተባለው ወንድም “የተሰማኝን የደስታ ስሜት መግለጽ አልችልም። ለፈጣሪ ምስገና ይድረሰው። ወንድማችን ጤናው ተመልሶ እስክናየው ድረስ ጓጉተናል” ሲል ለእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ተናግሯል።
የእስራኤል ጦር ባካሄዳቸው ዘመቻዎች እስካሁን ድረስ 8 ሰዎችን ከሐማስ እገታ ነጻ ማውጣት ችሏል።
የ11 ልጆች አባት የሆነው ካኢደ መስከረም 26 በሐማስ የታገተው በእስራኤል እና ፍልስጤም ድንበር አካባቢ በጥበቃ ስራው ላይ ሳለ ነበር።
ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፍቶ 1ሺህ 200 ሰዎችን ገድሎ 251 ሰዎችን አግቶ መውሰዱ ይታወሳል።
የእስራኤል መንግሥት ከእስራኤል ታግተው ከተወሰዱ ሰዎች መካከል በርካታውን በስምምነት እና በወታደራዊ ዘመቻ ነጻ አውጥቷል።
በዕለቱ በአጠቃላይ ከታገቱት 251 ታጋቾች መካከል መሞታቸው የተረጋገጡ የ34 ሰዎች አስክሬንን ጨምሮ 104 የሚሆኑት አሁንም በጋዛ ይገኛሉ።
ለአንድ ሳምንት በቆየ የተኩስ አቁም ስምምነት ሐማስ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና አዛውንቶች የሆኑ 105 ሰዎችን መልቀቁ ይታወሳል።
ከ10 ወራት በላይ ባስቆጠረው የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት በጋዛ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት የሆኑ ከ40ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።