የአሜሪካ አምባሳደር በህወሓት እና በትግራይ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከክልሉ ባለስልጣናት ጋር እየመከሩ ነው

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በህወሓት እና የትግራይ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከክልሉ ባለስልጣናት ጋር እየተወያዩ መሆኑን የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ለሶስት ቀናት የስራ ጉብኝት ወደ ትግራይ መዲና መቀለ ሰኞ፣ ነሐሴ 19/ 2016 ዓ.ም ያመሩት አምባሳደሩ በህወሓት፣ በትግራይ ወቅታዊ ጉዳዮች እና በጦርነቱ የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደ ስፍራቸው መመለስን በተመለከተ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለስልጣናት ጋር እየተወያዩ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ በዚያው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት አምባሳደሩ በከፍተኛ አመራሮቹ መካከል ክፍፍል ውስጥ የገባው ህወሓትን በተመለከተ አየተደረገ ስላለው ውይይት ዝርዝር መረጃ አላሰፈረም።

አምባሳደሩ በትግራይ ቆይታቸው የፖለቲካ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን ሁኔታ ከክልሉ ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ማክሰኞ፣ ነሐሴ 20/ 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የኤምባሲው መግለጫ የፖለቲካ ልዩነቶች ሲል የገለጸው ከሰሞኑ በህወሓት መካከል የተፈጠረው ክፍፍል ጋር ስለመያያዙ ያለው ነገር የለም።

በተጨማሪም ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የቋጨውን የፕሪቶሪያውን ስምምነት ውጤታማ አፈጻጸምን እንዲሁም በክልሉ ዘላቂ ሰላም የሚመጣበትን መንገድ ላይ ውይይት እንደሚደረግ የኤምባሲው መግለጫ ጠቁሟል።

አምባሳደሩ ወደ ትግራይ ያመሩት ለበርካታ አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ጉልህ ሚና የተጫወተው ህወሓት በከፍተኛ አመራሮቹ መካከል የተፈጠረው ቅራኔ ጎልቶ ክፍፍል በተፈጠረበት ወቅት ነው።

በከፍተኛ አመራሮቹ ክፍፍል መካከል በተደረገው 14ኛው የድርጅቱ ጉባኤ ድጋሚ በተመረጡት የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ እና የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር ጌታቸው ረዳ ቡድን መካከል የተፈጠረው ክፍፍል ተካሮ ይገኛል።

አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የማዕካላዊ ኮሚቴ አባላት ፣ የድርጅቱ ቁጥጥር ኮሚሽን አንዳንድ ወረዳዎችን ያላሳተፈው የህወሓት 14ኛ ጉባኤ እንዲሁም ፓርቲው ህጋዊ ሰውነት ለማስመለስ ለምርጫ ቦርድ የቀረበው ጥያቄ በሁለቱ ቡድኖች መካከል መወዛገቢያ ሆነዋል።

በሁለቱም አመራሮች በኩል የህወሓት ህጋዊ ወኪሎች እኛ ነን የሚሉ እንዲሁም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ያሉ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ስራ አስፈጻሚዎች ትግራይን የማስተዳደር ጉዳይ እያከራከራቸው ይገኛል።

በሊቀ መንበሩ ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው ሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሚደረግ ሹም ሽር ተፈጻሚ እንደማይሆን ከሰሞኑ አስታውቋል።

በቅርቡ የህወሓት ፅ/ቤት ዋና ኃላፊ ተደርገው የተሾሙት ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር ለሁሉም የህወሓት የዞን እና ወረዳ ጽ/ቤቶች በላኩት ደብዳቤ "የፓርቲውን አሠራር እና ሕጋዊ አካሄድ ባልተከተለ መንገድ የስልጣን ሹምር ሽር እየተካሄ ነው" ብለዋል።

ፊትለወርቅ በደብዳቤያቸው ይህን ያሉት ከቀናት በፊት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የደቡባዊ ምስራቅ ዞን አስተዳዳሪ የነበሩትን ሊያ ካሳን ከሥልጣን ካሰናበቷቸው በኋላ ነው።

በአወዛጋቢው 14ኛው የሕወሓት ጉባኤ ያልተገኙ እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ስራ አስፈጻሚዎች ድርጅቱን እንደማይወክሉ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ከሰሞኑ አስታውቀዋል።

ደብረጽዮን ከዚህ ቀደም ህወሓትን ወክለው በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የገቡ ህወሓትን ስለማይወክሉ ድርጅቱ ወካዮቹን ማስቀመጥ እንዳለበት ጠቅሰዋል።

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ህወሓት በጊዜያዊ አስተዳደሩ የራሱ ያልሆኑ ሰዎችን አንስቶ የሚወክሉትን መመደብ እንደሚችል ደብረጽዮን ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው በደብረጽዮን የሚመራውን ህወሓት “አፈንጋጭ ቡድን” ሲሉ የጠሩት ሲሆን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ስልጣን የመንጠቅ ስራ እንደሆነ ከሰሞኑ ከትግራይ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

በህወሓት አመራሮች መካከል ያለውን መፈራቀቅ የስልጣን ሽኩቻ እንደሆነ ጠርተው በደብረጽዮን የሚመራውን የህወሓት ቡድን ስልጣን ፈላጊ ነው ሲሉ ተችተውታል።

በቅርቡ የተደረገውን ጉባኤ የፓርቲውን ህገ ደንብ የጣሰ፣ ተቋማቱን እና ማዕከላዊ ኮሚቴ ያላከበረ እንዲሁም የምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያላገኘ “ሃሰተኛ ጉባዔ” ሲሉ አጣጥለውታል።

ህወሓት በልዩ ሁኔታ መመዝገቡን እንዲሁም የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠቱን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው ተቋሙ ሳያውቅ እንዲሁም የቦርዱ ታዛቢዎች ባልተገኙበት ሁኔታ ጠቅላላ ጉባኤው ሊካሄድ እንደማይችል አስታውቆ ነበር።

ጠቅላላ ጉባኤው ከቦርዱ ፍቃድ ውጪ ከተካሄደ ለዚህ ጉባኤም ሆነ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ዕውቅና እንደማይሰጥም ከጉባኤው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ለህወሓት በጻፈው ደብዳቤ ላይ መግለጹ ይታወሳል።

አምባሳደሩ በክልሉ መዲና መቀለ አሉላ አባነጋ ማረፊያ ሲደርሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እና ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

አምባሳደሩ በሶስቱ ቀናት ቆይታቸው አገራቸው ድጋፍ የምታደርግለትን በጦርነቱ የመደፈር ሰለባዎች ማዕከል እንዲሁም የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ መበተን እና ወደ ማህበረሰቡ መልሶ ለማዋሃድ ፕሮጀክቶችን ይጎበኛሉ ተብሏል።