በጊዜያዊ አስተዳደር ያሉ የህወሓት አመራሮች ድርጅቱን እንደማይወክሉ ደብረጽዮን አስታወቁ

በከፍተኛ አመራሮቹ ክፍፍል መካከል በተደረገው በ14ኛው የህወሓት ጉባኤ ያልተገኙ እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ስራ አስፈጻሚዎች ድርጅቱን እንደማይወክሉ የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል አስታወቁ።

ከፍተኛ አመራሮቹ እንዲሁም አባላቶቹ አንሳተፍበትም ያሉት የሰባት ቀናት የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጉባኤ ከተጠናቀቀ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ይህንን ያስታወቁት።

ህወሓት ከ14ኛው ጠቅላላ ጉባኤው ራሳቸውን ያገለሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም የፓርቲው ማዕከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን አመራሮች በተራ አባልነት ከመቀጠል ውጪ ሌላ ኃላፊነት እንደሌላቸው ከሰሞኑ ማስታወቁ ይታወሳል።

የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የድርጅቱ ቁጥጥር ኮሚሽን፣ አብዛኞቹ የደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ወረዳዎች እንዲሁም የመቀለ ከተማ ክፍለ ከተሞች በዚህ ጉባኤ ሳይገኙ ቀርተዋል።

ደብረጽዮን ነሐሴ 15/ 2016 ዓ.ም ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ከዚህ ቀደም ህወሓትን ወክለው በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የገቡ አመራሮች፣ በአሁኑ ጉባኤ ባለመሳተፋቸው እና ባለመመረጣቸው ህወሓትን መወከል አይችሉም ብለዋል።

14ኛው የህወሓት ጉባኤ 45 ማዕከላዊ ኮሚቴን መርጦ ማጠናቀቁን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ህወሓትን የወከሉ የጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች በ13ኛው ጉባኤ የተመረጡ እና የስልጣን ዘመናቸው መጠናቀቁን ጠቅሰዋል። እነዚህ አመራሮች በጊዜያዊ አስተዳደሩ ህወሓትን ስለማይወክሉ ድርጅቱ ወካዮቹን ማስቀመጥ እንዳለበት ጠቅሰዋል።

ህወሓትን አይወክሉም የተባሉት የጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ከዚህ ቀደም በማዕከላዊ ኮሚቴ፣ በስራ አስፈጻሚ ደረጃ ያሉ እና በጉባኤው ያልተሳተፉ መሆናቸውን ጠቅሰው ከአመራር በታች ያሉ አባላት ሊታይ እንደሚችል ጠቁመዋል።

በጊዜያዊ አስተዳደሩ ያሉ ሁሉም የህወሓት ተወካዮች “ያፈነገጡ” ናቸው ማለት እንደማይቻል እና በጉባኤው የተሳተፉ እንዳሉ ደብረ ጽዮን ጠቅሰዋል።

ህወሓት በልዩ ሁኔታ መመዝገቡን እንዲሁም የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠቱን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው ተቋሙ ሳያውቅ እንዲሁም የቦርዱ ታዛቢዎች ባልተገኙበት ሁኔታ ጠቅላላ ጉባኤው ሊካሄድ እንደማይችል አስታውቋል።

ጠቅላላ ጉባኤው ከቦርዱ ፍቃድ ውጪ ከተካሄደ ለዚህ ጉባኤም ሆነ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ዕውቅና እንደማይሰጥም ከጉባኤው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ለህወሓት በጻፈው ደብዳቤ ላይ መግለጹ ይታወሳል።

ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በቋጨው የፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ህወሓት በጊዜያዊ አስተዳደሩ የራሱ ያልሆኑ ሰዎችን አንስቶ የሚወክሉትን መመደብ እንደሚችል ደብረጽዮን ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

በትግራይ በኩል በተደረሰው ስምምነት በጊዜያዊ አስተዳደሩ የህወሓት ድርሻ 50+1 በመቶ እንዲወሰን እንዲሁም ከትግራይ ኃይሎች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ እና ምሁራን እንዲሁም ከተቃዋሚ ፓርቲ ተውጣጥቶ መመስረቱን አስታውሰዋል።

በዚህም መሰረት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ያለው የህወሓት ቦታ "በኛ ተወካዮች ሊያዝ ይገባል" ያሉት ደብረጽዮን ህወሓት ሊወከል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሆኖም ህወሓት የራሱን ሰዎች በጊዜያዊ መንግሥቱ መመደብ ቢችልም አሁን ባለው ሽኩቻ ምክንያት ውይይት እንደሚያስፈልግ አስምረዋል።

ውይይቱም ጊዜያዊ አስተዳደር ከመሰረቱት አካላት ከትግራይ ኃይሎች፣ ከምሁራን እና ከተቃዋሚ ድርጅቱ ጋር በመቀጠልም ከፌደራሉ መንግሥት ጋር እንደሚሆን ጠቁመዋል።

"አፈጻጸሙ የራሱ ችግሮች ስላሉት ህዝቡን በማይረብሽ እና በማይጎዳ መልኩ፣ እንዲሁም የአስተዳደሩን ተግባር በማያደናቅፍ መልኩ በመግባባት በሰለጠነ መንገድ የሚፈጸምበት ሁኔታ እንጀምራለን" ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራውን ህወሓት “አፈንጋጭ ቡድን” ሲሉ የጠሩት ሲሆን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ስልጣን የመንጠቅ ስራ እንደሆነ ከትግራይ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

በህወሓት አመራሮች መካከል ያለውን መፈራቀቅ የስልጣን ሽኩቻ እንደሆነ ጠርተው በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራውን ህወሓት ስልጣን ፈላጊ ነው ሲሉ ተችተውታል።

በቅርቡ የተደረገውን ጉባኤ የፓርቲውን ህገ ደንብ የጣሰ፣ ተቋማቱን እና ማዕከላዊ ኮሚቴ ያላከበረ እንዲሁም የምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያላገኘ “ሃሰተኛ ጉባዔ” ሲሉ አጣጥለውታል።

ትክክለኛው የሕወሓት ተወካዮች መሆናቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው የክልሉ መንግሥት መዋቅሮች የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የማያውቀውን ስብሰባ እንዳያደርጉ ከሰሞኑ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

አቶ ጌታቸው ለክልሉ ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ ከተማዎች፣ ክፍለ ከተማዎች እና የወረዳ ምክር ቤቶች በጻፉት ደብዳቤ ስብሰባ ለማካሄድ ከፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ጋር “መግባባት” እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

ደብረጽዮን ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ያነሱት ጉዳይ የምርጫ ቦርድ የህወሃትን ህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ጥያቄ ነው

የተሰረዘውን የህወሓት ህጋዊ ሰውነት በማስመለስ ረገድ ያልተመለሰ ጥያቄ ስላለ እሱም በውይይት ሊፈታ ይገባል ብለዋል።

"የፕሪቶሪያ ስምምነት ፈራሚው አካል ህወሓት እንዲሁም ያፈራረመ ሶስተኛ ወገን እንዳለ ጠቅሰው ለፈራሚው አካል እውቅና አልሰጥም ማለት የማይሆን ነገር ነው" ሲሉ አስረድተዋል።

ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ያሉ የሰው ኃይል ለውጦች እንዲሁም የተሰረዘውን ህጋዊ ሰውነት የማስመለስ፣ ፖለቲካዊ ውይይቶች እንዲሁም የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸምን በተመለከተ ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ውይይቶች እንደሚኖሩ ጠቅሰዋል።

በአመራሮቹ እና በአባላቱ መካከል ክፍፍል በተፈጠረው የሕወሓት ፖለቲካዊ ክፍፍል ወደ ጸጥታ ስጋቶች እንዳይቀየር እየተሰራ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ተናግረዋል።

የጸጥታ ኃይሉ ገለልተኛ እንዲሆን እና ፖለቲካዊ ልዩነቶች በውይይት እንዲቋጩ ጄነራል ታደሰ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ልዩነቶችን በኃይል አማራጭ ለመፍታት መሞከር ቀይ መስመር ናቸው የተባሉትን መተላለፍ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።