የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር መታመማቸውን 'የባይደን አስተዳደር አልሰማም ነበር'

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
የባይደን አስተዳደር ለቀናት ያህል የመከላከያ ሚኒስትሩ ኦስቲን ሎይድ ታመው ሆስፒታል ገብተው እንደነበር መረጃ እንዳልነበረው ተነገረ።
አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለአሜሪካው ሲቢኤስ ሚዲያ እንደተናገሩት የ70 ዓመቱ ኦስቲን ሎይድ፤ ዋልተር ሪድ ሆስፒታል የገቡት ሰኞ ዕለት ነው።
ሆስፒታል እንዲገቡ ያደረጋቸው ቀዶ ጥገና ተደርጎላቸው ያን ተከትሎት የጤና እክል ስለገጠማቸው ነበር።
ሆኖም ዋይት ሐውስ ስለ ጉዳዩ እስከ ሐሙስ ድረስ ምንም ዓይነት መረጃ አልነበረውም ተብሏል።
መከላከያ ሚኒስትሩ ስለተፈጠረው የመረጃ ክፍተት ይቅርታ ጠይቀዋል።
“ለሕዝብ ተገቢውን መረጃ በውቅቱ መስጠት ነበረብኝ። እንዲህ ዓይነቱ ነገር አይደገምም'' ብለዋል ኦስቲን።
በአሜሪካ የመንግሥት መዋቅር የመከላከያ ሚኒስትሩ ከፕሬዝዳንቱ ቀጥሎ ማንኛውንም ወታደራዊ ትእዛዝ ለመስጠት በተጠንቀቅ ያለ ሰው ነው።
“ጤናዬ እየተሻሻለ ነው። በቅርቡ ወደ ፔንታገን እመለሳለሁ። የተፈጠረው የመረጃ ክፍተት ኃላፊነቱ ሙሉ በሙሉ የኔ ይሆናል” ብለዋል ኦስቲን።
የመከላከያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ለኤፍፒ እንደገለጡት ሚኒስትሩ ዐርብ ዕለት ወደ ሥራ ተመልሰዋል።
ሚኒስትሩ ሆስፒታል በነበሩ ጊዜ ምን ያህል ውሳኔዎችን ምክትላቸው ካትሊን ሂክስ እንደወሰኑ የሚታወቀው ነገር የለም።
ጆ ባይደን ትናንት ቅዳሜ ለሚኒስትር ኦስቲን ስልክ ደውለው ዘለግ ላለ ሰዓት ማውራታቸውን ተዘግቧል።
“ፕሬዝዳንት ባይደን በሚኒስተሩ ላይ ከፍተኛ እምነት አላቸው። ፔንታገን በቅርቡ ተመልሰው ሥራቸውን ይጀምራሉ ብለውም ተስፋ ያደርጋሉ” ሲል ዘግቧል፣ ኤኤፍፒ።
የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ጉዳዩ የዋዛ አይደለም ሲሉ ተችተዋል።
ሴናተር ቶም ከተን የተፈጠረው የመረጃ ክፍተት ተራ ጉዳይ ሆኖ መታየት የለበትም ሲሉ ተከራክተዋል።
መከላከያ ሚኒስትሩ ኒክሊየርን ጨምሮ ትልቅ ውሳኔዎች የሚመለከቱት ኃላፊ ነው። በፕሬዝዳንቱና በሠራዊቱ መሀል ያለ አዛዥ ነው። ቅጽበታዊ ውሳኔዎች ይመለከተቱታል፤ እንዴት የመታመማቸው መረጃ ይደበቃል? ሲሉ ተችተዋል።
ሴናተር ሮጀር ዊከር በበኩላቸው ''ይህ መረጃ እውነት ከሆነ አንድ ሰው ኃላፊነት መውሰድና ለጥፋቱም መቀጣት አለበት። ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው” ብለዋል።
“የአሜሪካ ሠራዊት በመካከለኛው ምሥራቅ በተጠንቀቅ ባለበት ሰዓት፣ አሜሪካ በእስራኤልና ዩክሬን ከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊነትን በያዘችበት ወቅት ትልቅ ውሳኔ ሰጪ የሆኑት ሰው መታመማቸው መረጃው መደበቁ ፍጹም ተቀባይነት የለውም” ብለዋል ሴናተሩ።












