በርካቶችን ያስቆጣው እና ያነጋገረው የእንግሊዛዊት እና የኬንያዊው ጋብቻ

ሩት ሆልዌይ እና ጆን ኪሙዩ

የፎቶው ባለመብት, SUPPLIED

ነጭ እንግሊዛዊት ሴት በጥቁሩ ዓይነ ስውር ኬንያዊ ፍቅር ወድቃ ትዳር የመመስረቷ ዜና፤ ከማነጋገርም አልፎ የነጭ የበላይነት ስሜት ያላቸውን ያስቆጣ ድርጊት ነበር።

ሩት ሆልዌይ እና ጆን ኪሙዩ ግን ከደረሱባቸው ነቀፌታዎች በላይ ፍቅራቸው ጸንቶ በትዳር ተጣምረው ንዲንዳ ኪሙዩን ወልደዋል።

ሩት ከእንግሊዝ ተነስታ ኬንያ ያመጣት “የሚሽነሪ” ስራዋ ነበር። እርሷ በምትሰራበት የዓይነ ስውራን ማዕከል ውስጥ ነበር ከጆን ጋር የተዋወቀችው።

ነጯ እንግሊዛዊት ሴት ከጥቁሩ ኬንያዊ ጋር ትዳር እንደምትመሰረት ይፋ ስታደርግ ከሥራዋም ተባራ ነበር።

ዛሬ ላይ ሴት ልጃቸው ንዲንዳ እአአ 1957 የጀመረውን የወላጆቿን የፍቅር ታሪክ የሚተርክ መጽሐፍ መጻፍ ጀምራለች።

በኖቲንግሃምሻየር ተወልዳ ያደገችው ሩት፣ እግሯን ወደ ኬንያ ያነሳችው ገና የ19 ዓመት ወጣት ሳለች ነበር።

አደገኛ በሚባለው ወቅት ኬንያ እንደደረሰች ከጆን ጋር ተዋውቃ በፍቅር ወደቀች።

ወቅቱ ማኦ ማኦ የሚባሉ የኬንያ ነጻነት ተፋላሚዎች ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ ለመውጣት ትግል የሚያደርጉበት ወቅት ነበር።

ንዲንዳ

ሩት ኬንያዊውን ልታገባው እንደሆነ ለወላጆቿ እንዲሁም ለቀጣሪዋ ለማሳወቅ በመርከብ ወደ ዩኬ ባቀናች ወቅት ከወላጆቿ እና ከአሰሪዋ ትልቅ ውግዘት ገጠማት።

የአገሩ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀሩ በዘገባዎቻቸው ተዘባበቱባት።

“ለሰርጋቸው ቀለበት ገዝታ የጋገረችው ኬክ ውስጥ ደብቃ ወደ ኬንያ ለማምጣት ተገድዳ ሁሉ ነበር” በማለት ንዲንዳ ትናገራለች።

ጥቁር እና ነጭ በትዳር ሲጠመሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመ እንደሆነ በመታሰቡ የጥንዶቹ ሠርግ ትልቅ ትኩረትን ስቦ ነበር።

“በወቅቱ ሠርጉ ልክ እንደ ትልቅ ነገር ነበር የታየው” በማለት የጥንዶቹ መጋባት ከእንግሊዝ አልፎ በአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን መዘገቡን ንዲንዳ ታስታውሳለች።

“ትልቁ ተቃውሞ ገጥሟቸው የነበረው በኬንያ ከነበረው የቅኝ ግዛት ኃይል ነበር። እነርሱ ጭራሽ አልፈለጉትም ነበር” ትላለች ንዲንዳ።

ንዲንዳ ከሦስት ዓመት በኋላ ትወለዳለች። ለአባቷም በጣም ቅርብ ነበረች።

ይሁን እንጂ የኬንያን ነጻ መውጣት ተከትሎ ቤተሰቡ ለሁለት መከፈሉ ግድ ሆነ።

በወቅቱ ጋብቻውን የዘገቡ ጋዜጦች

የፎቶው ባለመብት, SUPPLIED

እአአ 1965 ላይ ሩት ከባለቤቷ ተነጥላ ሴት ልጇን ይዛ ወደ እንግሊዝ መሄድ ግድ ሆነባት። “ጊዜው ለአባቴ በጣም ከባድ ነበር። ለእናቴም ቢሆን ስሜት የሚረብሽ ግዜ ነበር”

ንዲንዳ አባቷ በኬንያ ለመቅረት የወሰነው ከቤተሰቡ ጋር ወደ እንግሊዝ ቢያመራ ዓይነ ስውር እና ጥቁር ለሆነ ሰው ሥራ ማግኘት ቀላል አይሆንም በሚል ስጋት መሆኑን ታስታውሳለች።

ጆን ከቤተሰቡ ጋር ወደ እንግሊዝ መጓዝ ባይችልም ካሴት ላይ ድምጹን እየቀረጸ መልክት ይልክላቸው ነበር። ንዲንዳ ትልቅ ስፍራ የምትሰጣቸው ካሴቶች አሁንም በእጇ ላይ እንደሚገኙ ትናገራለች።

ሩት ከ30 ዓመታት በኋላ ሕይወቷ ያልፋል። ከሩት ከተለያየ በኋላ ሁለት ግዜ ትዳር መስርቶ የነበረው ጆን በ90ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ገብቶ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኅዳር 2016 ላይ እንዲሁ ሕይወቱ አልፏል።

ሩት እና ጆን

የፎቶው ባለመብት, SUPPLIED

ንዲንዳ በአባቷ ቀብር ላይ ለመገኘት ከ30 ዓመታት በኋላ ወደ ኬንያ ተመልሳለች።

ወደ ኬንያ ያደረገችው ጉዞ ስለ ወላጆቿ የፍቅር ሕይወት መጽሐፍ እንድትጽፍ አነሳስቷታል።

“ወደ አገሬ እንደመጣሁ ነው የተሰማኝ። በአባቴ ሞት መረሪ ሐዘን አልተሰማኝም። እንደውም እረፍት እንዳገኘ ነው የሚሰማኝ።

ንዲንዳ ወላጆቿን በታሪክ ውስጥ “ፈር ቀዳጅ” አድርጋ እንደምታስባቸው ተናግራ፤ “እጅግ የሚገርመው አሁን በጣም በተለየ ዓለም ውስጥ ነው የምንኖረው” ትላለች።

“ለፍቅር የትኛውንም ዓይነት መስዋዕትነት ይከፈላል። ለፍቅር ስትል ተራራ ትወጣለህ። አንድ ያደረጋቸው ፍቅር ነበር፤ ለፍቅራቸውም ሲሉ መስዋዕትነት ከፍለዋል” ስትል የወላጆቿን ግንኙነት ታስታውሳለች