የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሜሪካ ትራንስፖርት ሚኒስቴር የገንዘብ ቅጣት ተላለፈበት

የዩናይትድ ስቴትስ ትራንስፖርት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢቲሀድ ኤርዌይስ ሕግ በመጣሳቸው በገንዘብ እንዲቀጡ ወስኗል።

ሚኒስቴሩ ባለፈው ሐሙስ ባወጣው መግለጫ መሠረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሜሪካው ዩናይትድ ኤርላይንስ መለያ (ኮድ) በመብረሩ 425 ሺህ ዶላር እንዲቀጣ ተወስኗል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶቹ ኤቲሀድ አየር መንገድ ደግሞ ጄትብሉ በተባለው የአሜሪካ አየር መንገድ መለያ ቁጥር በመብረሩ 400 ሺህ ዶላር ተቀጥቷል።

ሚኒስቴሩ በድረ-ገፁ ባወጣው መረጃ እንዳለው ሁለቱ አየር መንገዶች፤ በፌዴራል አቪዬሽን ባለሥልጣን (ኤፍኤኤ) የአሜሪካ አየር መንገዶች እንዳይበሩ በተከለከሉባቸው የአየር ክልሎች በመብረራቸው ነው ሕግ የጣሱት።

ሁለቱ አየር መንገዶች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውም ተዘግቧል።

አቪዬሽን ኮንሲዩመር ፕሮቴክሽን የተባለው የዩናይትድ ስቴትስ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ቢሮ ባደረገው ምርመራ ከአውሮፓውያኑ የካቲት 2020 እስካ ታኅሣሥ 2022 ባለው ጊዜ ነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥፋቱን ፈፅሟል የተባለው።

በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዩናይትድ ኤርላይንስን ኮድ ተጠቅሞ ከኢትዮጵያ ጂቡቲ በርካታ በረራዎችን አድርጓል፤ ይህ የአየር ክልል ደግሞ የአሜሪካ አየር መንገዶች እንዳይበሩበት በፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ክልከላ የተደረገበት ነው ይላል።

የአፍሪካ ግዙፉ አየር መንገድ ይህንን ድርጊት የፈፀመው ከዩናይትድ ስቴትስ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ፈቃድ ውጭ መሆኑን መግለጫው ያትታል።

ቅጣቱን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢቢሲ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

በተያያዘ ኢቲሀድ ኤርዌይስ ላይ በተደረገ ምርመራ አየር መንገዱ ከነሐሤ 2022 እስከ መስከረም 2022 ባለው ጊዜ የጄትብሉ ኤርዌይስን መለያ ተጠቅሞ በርካታ በረራ አድርጓል።

በረራዎቹ በዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል የተደረጉ ሲሆኑ በአቪየሽን አስተዳደሩ ለአሜሪካ አየር መንገዶች በተከለከሉ የአየር ክልሎች በኩል አልፏል ይላል።

ምንም እንኳ ሚኒስቴሩ ለኢቲሀድ ኤርዌይስ ስለጉዳዩ መስከረም 2022 እና ኅዳር 2022 ቢያሳውቅም አየር መንገዱ ግን ከጥር-ሚያዚያ 2023 ባለው ጊዜ የጄትብሉን መለያ ተጠቅሞ በረራዎች ማድረጉን መግለጫው ይጠቁማል።

የአሜሪካ ትራንስፖርት ሚኒስቴር በዩናይትድ ስቴትስ ለተመዘገቡ የመንገዶች አውሮፕላኖች በየጊዜው ማስታወቂያ ያወጣል።

አብዛኛውን ጊዜ የአየር ክልሎች ለበረራ የሚከለከሉት ለአየር ጉዞ አመቺ አይደሉም አሊያም የግጭት ቀጣና ናቸው ተብሎ ሲታሰብ ነው።

ባለፈው ጥቅምት ሚኒስቴሩ ለአውሮፓ ሕብረት አቪዬሽን ኤጀንሲ በላከው መመሪያ አውሮፕላኖች በኢራን የአየር ክልል እንዳይበሩ ዕግድ መጣሉ ይታወሳል። በጥቅምት ወር ኢራን እስራኤል ላይ የሚሳዔል ጥቃት ማድረጓ አይዘነጋም።

አየር መንገዶች የአሜሪካ የበረራ መለያዎችን የሚጠቀሙ በዩናይትድ ስቴትስ ትራንስፖርት ሚኒስቴር አሊያም በፌዴራል አቪዬሽን ባለሥልጣን መመሪያዎች መገዛት እንዳለባቸው ተንታኞች ያስረዳሉ።

ሚኒስቴሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአሜሪካ የአየርክልል ሕግ ውጭ የሚንቀሳቀሱ አየር መንገዶች ላይ ቅጣት እየጣለ ነው።

የካናዳው አየር መንገድ ኤር ካናዳ ባለፈው መስከረም በዩናይትድ ኤርላይንስ መለያ በኢራቅ የአየር ክልል በመብረሩ 250 ሺህ ዶላር ተቀጥቷል።

ኤሚሬትስ አየር መንገድ ደግሞ ከታኅሣሥ 2021 እስከ ነሐሤ 2022 ባለው ጊዜ የጄትብሉ መለያን ተጠቅሞ ከተፈቀደለት የበረራ ከፍታ በላይ በባግዳድ የአየር ክልል በመብረሩ 1.5 ሚሊዮን ዶላር መቀጣቱ የሚታወስ ነው።

ይህንን ቅጣት ተከትሎ ኤሚሬትስ አየር መንገድ ፓይለቶቹ ከተከፈተው ከፍታ መጠን በታች ለመብረር የተገደዱት በከባድ የአየር ሁኔታ ምክንያት ነው የሚል ምላሽ ሰጥቶ ነበር።