ለአራት ዓመታት ከኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞች ጋር በመኖር የተቀረጸው ፊልም፡ ‘ሜድ ኢን ኢትዮጵያ’

አብዛኞቹ ሠራተኞች ወጣት ሴቶች ናቸው። ሙሉ ትኩረታቸውን ያደረጉት የልብስ ስፌት ማሽኖች ላይ ነው። ቀና ብሎ ለመመልከት ጊዜ ያላቸው አይመስሉም።

የጂንስ ቁርጥራጮች እና ተሰፍተው ያለቁ ጂንስ ሱሪዎች በየቦታው ይታያሉ።

ቻይናውያን ተቆጣጣሪዎች በየኢትዮጵያውኑ ሠራተኞች ወንበር ዙርያ እየሄዱ ሥራውን ይከታተላሉ።

‘ሙሉ ትኩረት’፣ ‘ዴሞክራሲያዊ’፣ ‘የጋራ ጥቅም ለማግኘት’ የሚሉ መፈክሮች በአማርኛ፣ በማንደሪን (በቻይና ቋንቋ) እና በእንግሊዝኛ ግድግዳው ላይ ተጽፈዋል።

ዘጋቢ ፊልሙ የሚያተኩረው ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ላይ ነው። ‘ሜድ ኢን ኢትዮጵያ’ ይሰኛል።

ዋና ገፀ ባህሪያቱ ሞቶ፣ ቤቲ እና ወርቅነሽ ናቸው።

የሚኖሩት ዱከም ነው።

ቻይናዊቷ ሞቶ፣ የኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ምክትል ዳይሬክተር ናት። ቤቲ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ተቀጥራ ትሠራለች። ወርቅነሽ ደግሞ አርሶ አደር ናት።

ፊልሙ የቻይና ባለ ሃብቶች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት፣ ሥራ አጥነትን፣ ባህልን፣ ቤተሰብን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት እና የአርሶ አደሮች የተጠቃሚነት ጥያቄን በዋናነት ይዳስሳል።

በአውሮፓውያኑ 2008 በቻይና ባለሃብቶች የኢንዱስትሪ ፓርኩ ተጀመረ። ፓርኩ ወደ 103 ፋብሪካዎችን ይዟል።

የፊልሙ የመጀመሪያው ቀረጻ የተካሄደው ከስድስት ዓመት በፊት ነበር።

የፓርኩ ሠራተኞች በኢትዮጵያ የተሠራ ልብስ እና ጫማ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ሲቀርብ የሚሰጠውን ስሜት ያወራሉ።

“አንድ ጓደኛዬ አሜሪካ ውስጥ ‘ሜድ ኢን ኢትዮጵያ’ የሚል ጫማ አይታ ስሜታዊ ሆና አለቀሰች” ትላለች ከገፀ ባህሪያቱ አንዷ።

ሞቶ የቻይና ባለሃብቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ ትሞክራለች።

“አፍሪካ ሰላም ካልሆነች ዓለም ላይ ሌላ ሰላም የሚሆን ቦታ የለም። ዋናው የወጣቶች ጉዳይ ነው። እንዲያድጉ መደረግ አለበት። ተስፋ ስጧቸው። ተስፋ ከተሰጣቸው ሁከት አያስነሱም” ትላለች።

ባለሃብቶቹ እና ሞቶ ኢትዮጵያ ለምን በግጭት ትናጣለች? በሚለው ላይ ይወያያሉ።

“. . . ምክንያቱም ወጣቶች ሕልማቸው ከእውነታቸው የራቀ ስለሆነ. . .” ይላሉ።

ሞቶ፣ ቤቲ እና ወርቅነሽ

ከ14 ዓመታት በላይ ኢትዮጵያ የኖረችው ሞቶ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኩን ሁለተኛ ክፍል ማስፋፊያ መገንባት ነው ዋነኛ ግቧ።

“ኢትዮጵያ አገሬ ናት፣ እወዳታለሁ” ትላለች በተሰባበረ አማርኛ።

“በመጀመሪያው ዙር 20 ሺህ የሥራ ዕድል ፈጥረናል። በሁለተኛው ዙር ማስፋፊያ ደግሞ 30 ሺህ የሥራ ዕድል እንፈጥራለን” ትላለች።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ማስፋፊያ እንዲገነባበት የተሰጠው መሬት ላይ የሚያርሱ አርሶ አደሮች መሬቱን ያለ ካሳ እና ምትክ ቦታ ለቀው እንደማይሄዱ ይናገራሉ።

ሞቶ ደግሞ ለመሬቱ ካሳ ከፍለው ሁለት ዓመት ቢጠብቁም መንግሥት ጉዳዩን እንዳላስጨረሰ ትናገራለች።

ለቤቲ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ መሥራት ሁለት የተለያየ ስሜት ይሰጣታል።

በአንድ በኩል “ከቤቴ እሠራለሁ ብዬ ወጥቼ መመለስ ብዙም ደስ አላለኝምና እዚሁ ቆየሁ” ትላለች።

ክፍያው ግን በቂ አይደለም። በወር የሚከፈላቸው 50 ዶላር ነው።

እንደዚህም ሆኖ በየቀኑ ብዙ ወጣቶች በፓርኩ ለመቀጠር ይሄዳሉ። የፓርኩ መግቢያ ላይ ሆነው ይጠባበቃሉ። “ሥራ ሲኖር እንጠራችኋለን” ብለው ጥበቃዎች ይመልሷቸዋል።

አንድ ሠራተኛ “ይህን ሥራ እስካገኝ ቁርስ፣ ምሳ እና እራቴ ለቅሶ ነበር” ትላለች።

በፓርኩ የሚሠሩ ቻይናውያን፣ “እኛ ቻይናውያን ዋጋ የምንሰጠው ለገንዘብ ነው። ታድያ ለምን አገር አቆራርጠን መጣን? ከኢትዮጵያውያን ጋር አብረን ገንዘብ ማግኘት አለብን” ይላሉ።

ቤቲ ሥራ የጀመረችው በስፌት ክፍል ቢሆንም ቀስ በቀስ ወደ ቢሮ ሥራ ታድጋለች። ማንደሪንም ትማራለች።

የፓርኩ ሠራተኞች ባለው የሥራ ሁኔታ ሲበሳጩ የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ ይወያያሉ። ቻይናውያን አለቆቻቸው ደግሞ በምን ያህል ሰዓት ውስጥ ምን ያህል ልብስ ተሰፍቶ ማለቅ አለበት የሚለው ፍትሐዊ አካሄድ ነው ብለው ይከራከራሉ።

ከፓርኩ በቅርብ ርቀት ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ጤፍ ያርማሉ።

አርሶ አደሯ ወርቅነሽ ለልጆቿ የተሻለ ሕይወት ትመኛለች።

ልጇ ርሆቦት “እናቴ ተጠልፋ ነው ያገባችው። ባትጠለፍ የተሻለ ሕይወት ይኖራት ነበር። እኛንም አጥኑ፣ ጎበዝ ሁኑ ትለናለች” ትላለች።

ወርቅነሽ የኢንዱስትሪ ፓርኩን በማስፋፋት “ገበሬው ሁሉ ወደዚያ እንዲዞር ይፈልጋሉ” ትላለች።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ለማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ለአካባቢው አስተዳደር ገንዘብ ከፍሏል። አስተዳደሩም ለነዋሪዎች ምትክ ቦታ እና ካሳ ለመስጠት ቃል ገብቷል። ነዋሪዎች ግን ጥያቄችን አልተመለሰም ይላሉ።

ማኅበረሰቡ ለብዙ ዓመታት በኖረ የኦዳ ዛፍ ዙርያ ተሰብስቦ ይፀልያል፣ በጋራም ይመገባል።

“. . . ዝናብ ለምነን አገኘን . . . ቻይናንም ከእኛ ላይ ለሦስት ዓመት በፀሎት ከለከልን . . . የሚመጣውን አናውቅም” ይላሉ።

ይህ ስፍራ በማኅበረሰቡ እምነት እና ባህል ውስጥ ትልቅ ዋጋ አለው። ጥለውት መሄድ ማንነታቸውን ማጣት እንደሆነ ይሰማቸዋል።

የተወሰኑት፣ “ቻይና ምንም አላደረገልንም። ድህነት ውስጥ ነው የከተተን” ሲሉ የተቀሩት ደግሞ “ግብርና አልፎበታል፤ ቀጣይ ሕይወታችንን ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ጋር መቀጠል አለብን” ይላሉ።

‘ሜድ ኢን ኢትዮጵያ’

የዘጋቢ ፊልሙ ደራሲ እና አዘጋጆች ማክስ ደንካን እና ዘንየን ዩ ናቸው። ከፕሮዲውሰሮቹ አንዷ ታማራ ማርያም ዳዊት ናት።

ታማራ ከዚህ ቀደም በሠራችው ‘ሳሊን ፍለጋ’ በተባለው ዘጋቢ ፊልሟ የበለጠ ትታወቃለች።

‘ሜድ ኢን ኢትዮጵያ’ በዋርሶው ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል፣ በትሪቤካ ፊልም ፌስቲቫል፣ በሼፊልድ ኢንተርናሽናል ዶክመንተሪ ፌስቲቫል አና በሌሎችም ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ዕውቅናን አግኝቷል።

ለዓመታት ጋዜጠኞች የነበሩት እና ስለቻይና ብዙ ዘገባዎች የሠሩት ሁለቱ አዘጋጆች የኢንዱስትሪ ፓርኩን ማስፋፊያ ፕሮጀክት ታሪክ ይዘው ወደ ታማራ ሄዱ።

ኢትዮጵያዊት ካናዳዊት ፊልም ሠርዋ ታማራ፣ ብዙ የውጭ አገር ጋዜጠኞች እና ፕሮዲውሰሮች ሐሳባቸውን ነግረዋት አብረዋት ለመሥራት ሲጠይቋት “99 በመቶ እምቢ ነው የምለው” ትላለች።

‘ሜድ ኢን ኢትዮጵያ’ን ለመሥራት ግን ተስማማች።

“ብዙውን ጊዜ እምቢ የምለው አብዛኛው ሐሳብ የቅኝ ግዛት ወይም ምዕራባዊ ዕይታ ያለው ስለሆነ ነው። ሁለት ቀን ቀርጸው እና የተጨመቀ ሐሳብ ወስደው ኢትዮጵያን በዘጋቢ ፊልም ለመወከል ይሞክራሉ” ትላለች።

ይሄኛው ፊልም “ጥቂት እሺ ካልኩባቸው አንዱ ነው” የምትለው ፕሮዲውሰሯ፣ የፊልሙ አዘጋጆች አተያይ፣ ጥልቅ አረዳድ፣ የታሪክ ነገራ እና ከገፀ ባህሪያቱ ጋር ለመሥራት ያሰቡበት መንገድ “ከእኔ ሰዋዊ ባህሪ ያለው የፊልም አሠራር ጋር አብሮ ይሄዳል” ስትል ታስረዳለች።

ቻይና ለምን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ትሳተፋለች? ለዓመታት በኢትዮጵያ እና በቻይና መንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል? የሚለውን ለመዳሰስ ሞክረዋል።

አዘጋጆቹ ዘጋቢ ፊልሙ ምን ሊመስል እንደሚችል ቀድመው የወሰኑት ነገር አልነበረም። የተሠራበት መንገድ ‘Observational documentary’ ወይም ምልከታዊ ዘጋቢ ፊልም ነው።

ይሄ አሠራር ተመልካቾችን ወደ ታሪኩ፣ ወደ ፓርኩ እንዲሁም ዱከም ወዳለው ማኅበረሰብ የሚጋብዝ እንደሆነ ታማራ ታስረዳለች።

“ይሄ ልክ ነው፤ ይሄ ስህተት ነው እያልን አለመሆኑ ደስ ይለኛል” ትላለች።

ባለታሪኮቹ በፊልሙ ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ተደርጓል። ‘ሜዲ ኢን ኢትዮጵያ’ ለዕይታ ከመብቃቱ በፊት ገፀ ባህሪያቱ ቀድመው እንዲያዩት እና አስተያየት እንዲሰጡ ተደርጓል።

“ፊልሙ ከመውጣቱ በፊት ስናሳየቸው፣ ለዓመታት ስንቀርጻችሁ የነበረው በዚህ ምክንያት ነው ለማለት ነው። ይህም ሰዋዊ አካሄድ መከተል ነው። ገፀ ባህሪያቱ ብዙ ጊዜያቸውን ሰጥተውናል። ወደ ሕይወታቸው እንድንገባ ፈቅደውልናል። ስለዚህ ፊልሙን ለዓለም ከማሳየታችን በፊት በፊልሙ ደስተኛ መሆናቸውን፣ በፊልሙ እንደተወከሉ እንደተሰማቸውም ለማረጋገጥ ለእነሱ ማሳየት ነበረብን።”

ከገፀ ባህሪያቱ ይሁንታ ማግኘትን “ለእኔ በዘጋቢ ፊልም ሥራ ሂደት ውስጥ ትልቅ ዋጋ ያለው ነው። ፊልሙ የእኛ የሆነውን ያህል የእነሱም ነው” ስትልም ታማራ ታስረዳለች።

“ስክሪን ላይ እኛ ስለእኛ ስንናገር አይታይም”

“እንደ ኢትዮጵያዊ ፊልም ፕሮዲውስ ሳደርግ የማስበው፣ ስክሪን ላይ እኛ ስለራሳችን ስንናገር አለመታየቱን ነው። ሌሎች ሰዎች ናቸው ታሪካችንን የሚናገሩልን” ትላለች ታማራ።

ምሁራን ወይም ባለሙያዎች ስለኢትዮጵያ ሲያወሩ ይስተዋላል።

ለዚያም ነው “ፊልም ሳዘጋጅም፣ ፕሮዲውስ ሳደርግም ኢትዮጵያውያን ስለራሳቸው ተሞክሮ የሚናገሩበት እና የሚደመጡበት መድረክ መስጠት ነው የምፈልገው” የምትለው።

ስለቻይና እና አፍሪካ ግንኙነት ወይም በኢትዮጵያ ስላለው የቻይና ኢንቨስትመንት ብዙ ረዣዥም ፊልሞችን መሥራት ቢቻልም፣ ትልቁን ታሪክ በትንሽ ሌንስ ውስጥ ማሳየትን ትመርጣለች።

የኢንዱስትሪ ፓርክን ታሪክ ከተለያየ አቅጣጫ ማየት የቻሉትም በዚህ መንገድ ነው።

ሞቶ እንደ ፓርኩ ኃላፊነቷ የኢንዱስትሪ ፓርኩን ማስፋፋትን ታስቀድማለች።

ለአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ ጥያቄው የእርሻ መሬት ማጣት ነው። “መሬታችን ተወስዶ አስተዳደሩ ዝም አለን። እኛን ይታገላሉ እንጂ፣ ለእኛ አይታገሉም” ሲሉ ይደመጣሉ።

የዱከም ከተማ በኢንዱስትሪ ፓርኩ አቅራቢያ የከተማ ፓርክ ለመሥራት አቅዷል። አስተዳደሩ፣ ፓርኩም ሆነ አርሶ አደሮች ‘አሸናፊ’ የሚሆኑበት መንገድ መቀየስ እንዳለበት ይናገራል።

ፊልሙ የሚከተለው ምልከታዊ የዘገባ ፊልም አካሄድ “ሲታይ ደስ ቢልም ሲሠራ ግን ቀላል አይደለም” ትላለች ተማራ።

ለጥቂት ሳምንታት ቀርጾ፣ የባለሙያ አስተያየት ጨምሮ ፊልሙን ከመሥራት ይልቅ ከገፀ ባህሪያቱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ መርጠዋል።

“ትስስር ለመፍጠር ስንል የገፀ ባህሪያቱን ሕይወት ለአራት ዓመታት ተከታትለናል” ስትል ፕሮዲውሰሯ ታስረዳለች።

የፊልሙ አዘጋጆች በኢንዱስትሪ ፓርኩ ዶርም ውስጥ ከገፀ ባህሪያቱ ጋር አብረው እየኖሩ ነበር ቀረጻውን ያካሄዱት።

“ዘጋቢ ፊልሙ እንደ ድራማ የመሰላቸው አሉ። ግን ዘጋቢ ፊልም ነው። ታሪኩ እውነተኛ ነው። ተዋንያኑ እውነተኛ ታሪካቸውን ነው የሚያካፍሉት” ትላለች ታማራ።

ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ብዙ ጊዜ በመቆየት ስለ ሕይወታቸው በግልጽ እንዲያወሩላቸው አድርገዋል።

ይሄንንም “በጣም ድፍረት የሚጠይቅ” እንዲሁም “በመካከላችን የተፈጠረውን ግንኙነት እና መተማመንም የሚያሳይ” ስትል ትገልጸዋለች።

አብዛኛውን ጊዜ በኢትዮጵያ ዘጋቢ ፊልሞች ሲሠሩ ገፀ ባህሪያቱ ዘጋቢ ፊልም ምን እንደሆነ፣ ለምን እየተቀረፀ እንደሆነ እና ሌሎችም ነገሮችን እንደማይገነዘቡ ታስረዳለች።

ፊልም ሲሠራ ግን “ሰዎችን በሚበዘብዝ መልኩ ሳይሆን ጥንቃቄ በተሞላበት እና ክብራቸውን በሚጠብቅ መንገድ” መሆን እንዳለበት ታክላለች።

በኢትዮጵያ የሚታዩ ዘጋቢ ፊልሞች በአብዛኛው “በመንግሥት የሚሠሩ የፕሮፓጋንዳ ፊልሞች” እንደሆኑ ታማራ ትገልጻለች።

ባለሙያዎች በግላቸው ሲሠሩም ማኅበረሰቡ “መንግሥት በሆን መንገድ እንድናስብ ለማታለል አስቦ የሠራው” ነው ብለው ሲወስዱት ይታያል።

ውክልና እና ከቅኝ ግዛት ትርክት መላቀቅ

ዘጋቢ ፊልሙን በኢትዮጵያ ለማሳየት ዝግጅት እያደረጉ ነው። ከዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ሽልማት እና ዕውቅና አግኝቷል።

በቅርቡ በካናዳ፣ ቶሮንቶ ‘ፕላኔት ኢን ፎከስ’ የፊልም ፌስቲቫል ላይ የምርጥ ዓለም አቀፍ ፊልም ሽልማት አሸናፊ ሆኗል።

ፊልሙን በእስያ፣ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በተለያዩ የአፍሪካ አገራት አሳይተዋል። በተለይም ምሥራቅ አፍሪካውያን እና እስያውያን ተመልካቾችን ታሳቢ ለማድረግ ሞክረዋል።

ፊልሙ ሲወጣ “ምን ዓይነት ምላሽ አገኛለሁ ብዬ እንደጠበቅኩ እኔ እንጃ” የምትለው ታማራ፣ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ፌስቲቫሉ ላይ መታደማቸውን በማንሳት “ኢትዮጵያውያን ስለራሳቸው ራሳቸው የሚናገሩበት ዘጋቢ ፊልም የማየት ዕድል ስለማያገኙ በፌስቲቫሎች ላይ ተገኝተው ፊልሙን ማየታቸው መልካም ነው” ትላለች።

ዱከምን ከኢንዱስትሪ ፓርኩ በፊት እና በኋላ የሚያውቁ እንዲሁም በተለያዩ ፋብሪካዎች ውስጥ ተመሳሳይ የሥራ ሕይወት የነበራቸውም በፊልሙ ውስጥ ራሳቸውን እንዳዩ መናገራቸውን ትጠቅሳለች።

ለዚህም ነው “ውክልና ትልቅ ነገር ነው። ሰዎች ስለራሳቸው ሌላ ሰው ሲያወራ ሳይሆን፣ ራሳቸው ሲያወሩ ማየት አለባቸው” የምትለው።

ምልከታዊ ዘጋቢ ፊልም አካሄዱን ቀድሞ ለመወሰን ቀላል እንዳልሆነ ትናገራለች። ቀድመው የወሰኑት የሚቀርጹበትን ቦታ እና የሚከተሏቸውን ሦስት ሴት ገፀ ባህሪያት ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2019 የፊልሙ ቀረፃ ሲጀመር እስከ ሁለት ዓመት እንቀርጻለን ብለው ነበር አዘጋጆቹ ያሰቡት። ፊልሙን ሲቀረጽ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የሰሜኑ የእርስ በእርስ ጦርነት እና አገር አቀፍ ምርጫ ተካሂዷል።

በቀረጻው ወቅት በዋነኛነት የገጠማቸው ፈተና የበጀት ውስንት እንደነበር ታማራ ትናገራለች።

“እንደዚህ ያሉ የአፍሪካ ፊልሞችን ለመቅረፅ ገንዘብ ማግኘት ቀላል አይደለም። ስለአፍሪካ የሚሠሩ ፊልሞች ዋጋ አይሰጣቸውም። ግን ታሪኮቹ መነገር አለባቸው። ገፀ ባህሪዎቹ የራሳቸውን ታሪክ መናገር እንዲችሉ ማድረግ ነው ሲገፋፋን የነበረው።”

“ለእኔ ፊልም መሥራት ፖለቲካዊ ነው”

ታማራ፣ በ1980ዎቹ ካናዳ ስታድግ ስለኢትዮጵያ ረሃብ፣ ለኢትዮጵያ ስለተላከውን እርዳታ እና ዝንብ ስለሚወራቸው ሕጻናት ብቻ ነበር የምትሰማው።

“ለኢትዮጵያውያን እኛ አንድ ዶላር በየቀኑ እርዳታ ካላክንላቸው ተስፋ የላቸውም፣ ምንም ማድረግ አይችሉም የሚል ምልከታ ነው የሚሰማው” ትላለች።

ይህንን በሚገዳደር መልኩ በምትሠራቸው ፊልሞች ማሳየት የምትፈልገው በራሳቸው መወሰን የሚችሉ፣ ስለራሳቸው መናገር የሚችሉ እና በሕይወታቸው ውስጥ በራሳቸው ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ሰዎችን ነው።

“ፈተና አለባቸው። ግን ከአውሮፓ ወይም ከሰሜን አሜሪካ የሚታደጋቸው ሰው እስከሚመጣ እየጠበቁ አይደለም። ራሳቸውን ነው የሚያድኑት” ትላለች።

ለዚህም ነው “ለእኔ ፊልም መሥራት ፖለቲካዊ ነው። ይህንን የቅኝ ግዛት ሐሳብ ይነቅፋል። ይቃረናል። ፊልም የምሠራበት ምክንያት እንደ ሰው ማን ነን? የሚለውን ትርክት ለማረም ነው” ስትልም ታክላለች።

“ታሪክ ነጋሪ ሴቶች”

ዘጋቢ ፊልሙ የሚከተለው የሞቶ፣ የቤቲና የወርቅነሽን ሕይወት ሲሆን፣ በነሱ የቤተሰብ ታሪክና የምጣኔ ሀብት ጥያቄ ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ውስብስብ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እውነታ ያሳያል።

ቤቲ መማርና የተሻለ ገቢ ማግኘት ትፈልጋለች። ሞቶ የኢንዱስትሪ ፓርኩን ማስፋፊያ ማስፈጸም ዋነኛ ግቧ ቢሆንም ቻይና ከምትኖረው ልጇ መለየቷ ልቧን ይሰብረዋል። ወርቅነሽ የእርሻ መሬቷ ኖረም አልኖረም ለልጆቿ የተሻለ ነገን መፍጠር ነው ሕልሟ።

ሁሉም ገፀ ባህሪዎች ሴቶች እንዲሆኑ ታስቦ ፊልሙ ባይጀመርም በዛ መንገድ እንደሄደ ፕሮዲውሰሯ ትናገራለች።

“ወርቅነሽና ልጇ በግልጽ ሲያወሩ በፊልሙ ማሳየትን በጣም ልዩ ቦታ እሰጠዋለሁ። በኢትዮጵያ ሴቶች ታሪክ ነጋሪና ታሪክ ጠባቂ ናቸው። ትውስታዎችን ወደ ቀጣይ ትውልድ ያስተላለፋሉ” ትላለች።

ታማራ አክላም “ሴቶች ሲያወሩና ታሪካቸውን ሲያጋሩ ስለራሳቸው ብቻ አይደለም። ወንዶች ሲናገሩ ‘እኔ እኔ እኔ’ እያሉ ነው። ሴቶች ሲናገሩ ከቤተሰብና ከማኅበረሰብ አንጻር ነው” በማለት ታስረዳለች።

በኢትዮጵያውያኑና በቻይናውያኑ መካከል ያለው ትስስር ገንዘብ የማግኘትና የዕድገት ጥያቄ ብቻ አይደለም።

ወርቅነሽና ልጇ ርሆቦት ያላቸው ቅርበት ሞቶና ልጇም አላቸው። ሁለቱም ለልጆቻቸው ያላቸው ተስፋ፣ የተሻለ ኑሮና ዕድል እንዲኖራቸው መፈለጋቸውም ይታያል።

“ሴቶች ነገሮችን የምናየው በተለየ መንገድ ነው። ያለፈውን ስንናገርም ወደፊት ነው የምንመለከተው” ትላለች ታማራ።