እስራኤል የአሳድን መውደቅ ተከትሎ በወረራ በያዘቻቸው የሶሪያ የጎላን ተራራዎች ሰፈራ ልታስፋፋ ነው

የፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድን በኃይል ከስልጣን መገርሰስ ተከትሎ እስራኤል በወረራ በያዘቻቸው የሶሪያ የጎላን ተራራዎች ሰፈራ ልታስፋፋ ነው።

አሳድ በወደቁ ማግስት በድንበር አካባቢ ተጨማሪ የሶሪያ መሬቶችን የወረረው የእስራኤል መንግሥት በነዚህ ስፍራዎች ላይ ዜጎቹን በማስፈር የማስፋፋትን ዕቅድ አጽድቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሰፈራ እርምጃው አስፈላጊ ነው ያሉ ሲሆን ለዚህም የሰጡት ምክንያት የአሳድ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ በድንበር አካባቢ "አዲስ ግንባር" በመከፈቱ ነው ብለዋል።

ኔታንያሁ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ህገወጥ የሚባለውን እና አገራቸው በወረራ በተቆጣጠረቻቸው የጎላን ተራራዎች ላይ የሰፈረውን የህዝብ ቁጥራቸውን እጥፍ ማድረግ እንፈልጋለን ብለዋል።

እስራኤል እነዚህን ስፍራዎች መጀመሪያ የተቆጣጠረችው በአውሮፓውያኑ 1967 በተካሄደው የስድስቱ ቀን ጦርነት ነው።

በሶሪያ ድንበር አካባቢ የነበረው ጦር ስፍራውን መልቀቁን ተከትሎ እስራኤል ከአመታት በፊት የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሷል በሚል ተጨማሪ የሶሪያ መሬትን ወራለች።

እስራኤል ተጨማሪ የሶሪያ መሬትን በመውረር የሰፈራ ስራዎችን ልታከናውን በዕቅድ ላይ ብትሆንም ኔታንያሁ እሁድ፣ ታህሳስ 6/ 2017 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ አገራቸው "ከሶሪያ ጋር ግጭት የመግባት ፍላጎት የላትም" ብለዋል።

"እስራኤል በሶሪያ ላይ የሚኖራትን ፖሊሲ በመሬት ላይ ባለው እውነታ መሰረት እንወስናለን" ብለዋል።

እስራኤል በወረራ በያዘቻቸው የጎላን ተራራዎች ከ30 በላይ ሰፈሮች የሚኖሩ ሲሆን በነዚህም ስፍራዎች 20 ሺህ የሚሆኑ እስራኤላውያን ይኖራሉ። እነዚህ ሰፈራዎች በአለም አቀፉ ህግ ህገወጥ ሲሆኑ እስራኤል ይህንን አትቀበለውም።

ኔታንያሁ እስራኤል መሬቱን በመያዝ እንደምትቀጥል ገልጸው "ሰፈራዎች እንዲገነቡ እና እንዲያብቡ እናደርጋለን" ብለዋል።

ሆኖም የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሁድ አልመርት እስራኤል ተጨማሪ የጎላን ተራራዎችን "የምትይዝበት ምንም አይነት ምክንያት" የለም ይላሉ።

"ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ከሶሪያ ጋር ግጭት ውስጥ ለመግባት ፍላጎት የለንም ይላል እናም በአሁኑ ወቅት ሶሪያን ከተቆጣጠሩት አማጽያን ጋር መዋጋት እንደማንፈልግ ተስፋ አደርጋለሁ። ታዲያ [ናታንያሁ] ተቃራኒውን ለምን ያደርጋሉ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አያይዘውም "በቂ ችግሮች አሉብን" ብለዋል።

ኔታንያሁ የሰፈራ ፕሮግራማቸውን ያስታወቁት የአሳድ ስርዓት መውደቅ ተከትሎ አገራቸው በሶሪያ ተከታታይ የአየር ጥቃቶችን በፈጸመች ማግስት ነው። የሶሪያ አዲሱ መሪ አህመድ አል ሻራ እስራኤል በአገሪቱ እያደረሰች ያለውን ጥቃት ተችተዋል። ጥቃቱ ወታደራዊ ተቋማትን ኢላማ ያደረገ ነው ተብሏል።