ግብፅ የውሃ ደኅንነቷን ለማስጠበቅ አስፈላጊ እርምጃዎችን ትወስዳለች - ፕሬዚዳንት አል ሲሲ

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ገንብታ ካስመረቀችው የሕዳሴ ግድብ አንጻር ግብፅ ብሔራዊ ጥቅሟን አና የውሃ ደኅንነቷን ለማስጠበቅ አስፈላጊ የሆኑትን ሁሉንም እርምጃዎችን እንደምትወስድ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በማስተዳደር ላይ እየተከተለችው ባለው "ኃላፊነት የጎደለው" አካሄድ ላይ አገራቸው "እጇን አጣጥፋ አትመለከትም" ብለዋል።

አል ሲሲ በዋና ከተማቸው ካይሮ ለተካሄደው 8ኛው የውሃ ሳምንት ተሰብሳቢዎች በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ግብፅ ዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት "በይበልጥ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት" ላይ መተማመኗ እንደ ድክመት መቆጠር የለበትም ብለዋል።

ግብፅ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከአባይ ወንዝ የምታገኘውን የውሃ መጠን ይቀንስብኛል ስትል አጥብቃ ስትቃወም የነበረ ቢሆንም፣ ፕሬዚዳንቱ እሁድ ዕለት ባደረጉት ንግግር ላይ ግን ባለፉት ሳምንታት በሱዳን ውስጥ ለተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ የኢትዮጵያን ግድብ ተጠያቂ አድርገዋል።

"ኢትዮጵያ ግድቡ ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ እያስተዳደረችው በመሆኑ ባልተመጣጠነ የውሃ ፍሰት ምክንያት ባለፉት ቀናት በሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ውስጥ ጉዳት ደርሷል" ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ላይ ከግድቡ ምርቃት ከጥቂት ቀናት በኋላ የተከሰተው ነገር "በግድቡ የሥራ ሂደት ላይ ሕጋዊ አሳሪ ስምምነት እንዲደረስ ያቀረብነውን ጥያቄ ትክክል መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ነው" ብለዋል።

አል ሲሲ ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን "አስቀድማ ሳታሳውቅ ወይም ሳትተባበር ወጥነት የሌለው ውሃ ትለቅቃለች" ሲሉም ወንጅለዋታል።

የኢትዮጵያ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር፤ ግብፅ ሕዳሴ ግድብ "በአግባቡ ባለመተዳደሩ ምክንያት የተለቀቀ ውሃ በሱዳን ጎርፍ እንዳስከተለ" በመግለጽ ከዚህ በፊት ያወጣቸውን መግለጫ፤ "በሐሰት የተሞላ" እና "ተንኮል አዘል" በማለት ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ባይኖር ኖሮ ባለፉት ወራት በኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች የታየው ከፍተኛ ዝናብ፤ "ሱዳን እና ግብፅ ውስጥ በሰው ሕይወት እና በመሠረተ ልማት ላይ ታሪካዊ ውድመት ሊያደርስ ይችል" እንደነበረ በመግለጽ በወቅቱ ምላሽ ሰጥቷል።

አልሲሲ አገራቸው የወሰደቻቸውን የዲፕሎማሲ እርምጃዎች " የጥንካሬ መገለጫ፣ የብስለት እና በንግግር የማመን እና የናይል ተፋሰስ አገራትን ፍላጎት አደጋ ላይ ሳይጥሉ ለመጠበቅ" የተደረገ መሆኑን አክለዋል።

የግብፁ ፕሬዚዳንት ድርቅ እና የውሃ መጥለቅለቅ በሚኖርበት ወቅት የውሃ አለቃቅን ለመቆጣጣር የሚያስችል አሳሪ የሆነ ስምምነት "በሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ያካተተ ስምምነት" እንዲኖር የጠየቁ ሲሆን "በላይኛው የተፋሰስ አገራት የዕድገት ፍላጎት እና የታችኛውን ተፋሰስ አገራት ከጉዳት ለመከላከል በሚኖር ሚዛን መካከል ብቸኛው አማራጭ ነው" ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ የሚኖርን የተናጠል እርምጃን የማትቀበለው "ዓለም አቀፍ አሠራሮችን እና ስምምነቶችን ወደ ጎን ስለሚል፣ የተፋሰሱ አገራትን ፍላጎት ስጋት ላይ ስለሚጥል እንዲሁም የፍትሕን እና መረጋጋት መርሆዎችን ዝቅ ስለሚያደርግ" መሆኑን በንግግራቸውን ላይ አንስተዋል።

"ልማት የአንድ አገር ብቻ ጉዳይ አይደለም" ያሉት አል ሲሲ "የወንዙ ሕዝቦች የጋራ በሆነ ኃላፊነት እና በትብብር ብቻ ሊጠበቅ የሚችል መብት ነው፣ የተናጠል እርምጃ አይደለም" ብለዋል።

በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅት ለ14 ዓመታት በተለያየ ዙር የተደረገውን ድርድር የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ "የሁሉንም ፍላጎት ከግምት ያስገባ አሳሪ ሕግ እና በመብቶች እና በግዴታዎች መካከል ሚዛን የጠበቀ አስገዳጅ ስምምነትን" ታሳቢ ያደረገ "ፍትሃዊ እና ብልሃት የተሞላው የዲፕሎማሲ መንገድ" እንደነበር ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ካይሮ "ኢትዮጵያ ያስቀመጠቻቸውን የልማት ግቦች የሚያሟሉ በርካታ ጥሩ ቴክኒካዊ አማራጮችን እና የሁለቱን የታችኛው ተፋሰስ አገራት ጥቅም የሚያስጠብቅ ሃሳብ አቅርባ" እንደነበረ ጠቅሰዋል።

ነገር ግን እነዚህ የግብፅ አማራጮች "የፖለቲካ ፍላጎት ባለመኖሩ እና በጠባብ የፖለቲካ እሳቤዎች የሚመራ የተናጠል እውነታን የመጫን ፍላጎት ብቻ ሊገለጽ በሚችል ግትርነት" ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል ብለዋል።

አል ሲሲ "ወንዙ የሁሉም የተፋሰሱ መንግሥታት የጋራ ንብረት እና በብቸኝነት ሊያዝ የማይችል የጋራ ሃብት ነው" በማለት "በናይል ላይ ብቸኛ የሉዓላዊነት ሐሰተኛ ይገባኛል ጥያቄ" ተቀባይነት እንደሌለው አመልክተዋል።

ግብፅ በዓለም ላይ የውሃ እጥረት ካለባቸው አገራት መካከል መሆኗን የጠቀሱት ፕሬዚዳንት አልሲሲ ከአገራቸው 100 ሚሊዮን ሕዝብ 98 በመቶ የውሃ ፍላጎታቸውን የሚያገኙት ከአባይ ወንዝ መሆኑን ጠቅሰው "የኅልውና ጉዳይ ነው" ሲሉ አስቀምጠውታል።

ፕሬዚዳንቱ አክለውም አገራቸው በአባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ ስትከተል የነበረው ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የደካማነት ምልክት አለመሆኑን በመጥቀስ፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ እየተከተለችው ካለው አካሄድ አኳያ ዝምታን እንደማትመርጥ እና ጥቅሟን ለማስከበር አስፈላጊ ያለቸውን እርምጃ እንድምትወስድ በድጋሚ ተናግረዋል።

አልሲሲ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች "የተፈጠሩት ዜጎችን ሊከፋፍሉ ሳይሆን ለውህደት እና ለትብብር ድልድዮች እንዲሆኑ ነው" ብለዋል።

"የውሃ ደኅንነት ቅንጦት እና ዘላቂ የልማት አማራጭ አይደለም" ካሉ በኋላ "እነሱ ሊጠበቁ የሚችሉት በዓለም አቀፍ ሕግ፣ በጋራ ጥቅም እና ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መርህ ላይ በተመሠረተ ፍትሃዊ አጋርነት ብቻ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ግብፅ እና ሱዳን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ አስተዳደር እና የውሃ ሙሌት ላይ ለዓመታት ድርድር ያደረጉ ሲሆን ሁሉንም የሚያስማማ መቋጫ ላይ ሳይደርሱ የግድቡ ግንባታ ተጠናቅቆ ሥራ ጀምሯል።

ግብፅ በአፍሪካ ግዙፉ የሆነውን ግድብ ጉዳይ ባለፉት ዓመታት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ለአፍሪካ ኅብረት እና ለአረብ ሊግ በማቅረብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ሞክራለች።

በዓለማችን በርዝመቱ የሚታወቀው የአባይ ወንዝ ከ85 በመቶ በላይ ውሃውን የሚያገኘው ከኢትዮጵያ ሲሆን፣ የወንዙን አብዛኛውን ውሃ የምትጠቀመው ግብፅ በኢትዮጵያ የተገነባው ግድብ በበላይነት ስትጠቀምበት የነበረውን የውሃ መጠን ያሳጣኛል የሚል ስጋት ፈጥሮባታል።

ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመው እና አብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት በመጥቀስ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት በማለት ኢትዮጵያ ይህ ሁኔታ መለወጥ እንዳላበት ስትከራከር ቆይታለች።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እና ግንባታው የግብፅን የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ እንደማይጥል በተደጋጋሚ ገልጻለች።