ግብፅ "የግድቡን ጉዳይ ወደ ዓለም አቀፍ የፍትሕ ፍርድ ቤት እወስዳለሁ" ማለቷን ኢትዮጵያ አጣጣለች

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት "በታችኛው ተፋሰስ የሚኖሩ የሚሊዮኖችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥላለች" ብለው በመክሰስ አገራቸው ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት እንደምትወስድ ተናገሩ።

በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ ተወካይ ዮሴፍ ካሳዬ ለግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሰጡት ምላሽ፤ "ግብፅ ስለ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያደረገችው ንግግር መሠረት አልባ እና አሳሳች ነው" ሲሉ አጣጥለዋል።

ግብፅ "ስለ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተዓማኒ ያልሆኑ ክሶችን በተደጋጋሚ ወደ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አቅርባለች" ሲሉም አክለዋል።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ኢትዮጵያ "በዓባይ ላይ የተናጠል እርምጃ ወስዳ ግድብ በመገንባት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የግብፅ እና የሱዳን ሕዝቦችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥላለች" ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት 80ኛ ጠቅላላ ጉባዔ በተካሄደበት ወቅት የሁለቱ አገራት ተወካዮች ጠንካራ ቃላትን ተለዋውጠዋል።

ግብፅ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በምሥራቅ ናይል ተፋሰስ "አፍራሽ የተናጠል ፖሊሲ" እየተከተለች ነው ስትል ከሳለች።

የሕዳሴ ግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት "አደጋ የደቀነ" ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በተመድ የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ ተወካይ ዮሴፍ ካሳዬ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ በተደጋጋሚ ዓለም አቀፍ ሕግና መርሕን በሠረት በማድረግ ምላሽ መስጠቷን አንስተዋል።

አምባሳደር ዮሴፍ "የኢትዮጵያ ዘላቂ የትብብር ፖሊሲ እና የግብፅ አዋኪነት ያላቸው ልዩነት ግልጽ ነው" ሲሉም አክለዋል።

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላት በአቋም ዓለም አቀፍ ሕግጋት እና በእኩል ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ እንደሆነም ገልጸዋል።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው "ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግን መጣስ መርጣለች። በተናጠል ፖሊሲዋ የአፍሪካ ቀንድና የምሥራቅ ናይል ተፋሰስን እያወከች ነው" ብለዋል።

ግድቡ በተመረቀበት ዕለት ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ባስገባችው ይፋዊ ደብዳቤ ላይ ግድቡን "ሕገ ወጥ የተናጠል እርምጃ የተወሰደበት" በማለት ገልጻለች።

በደብዳቤው ላይ ግብፅ ለዓመታት ጉዳዩን "በዲፕሎማሲ እና እንደ ተመድ ባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት አማካኝነት ለመያዝ" መሞከሯን ጠቅሳለች።

ግብፅ "ለዓመታት ትዕግስት ያሳየችው ደካማ ስለሆነች ሳይሆን በዓባይ ተፋሰስ አገራት መካከል በሚኖር ትብብር ስለምታምን ነው" በሚልም በደብዳቤው ተመልክቷል።

አምባሳደር ዮሴፍ ለግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሰጡት ምላሽ "ግብፅ ከቅኝ ግዛት ስምምነት የተወረሰ 'ታሪካዊ መብት' አለኝ በሚል የተፋሰሱን አገራት አግልላች" ብለዋል።

ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ለኃይል አቅርቦት፣ ለምግብ ደኅንነትና ለንጹሕ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት እንደምትጠቀም ጠቅሰው፤ ግብፅ ግን "ይህንን መብት ለመንፈግና በዓባይ ላይ በብቸኛነት ተጠቃሚ ለመሆነ ትሻለች" በማለት ከሰዋል።

ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ በተመለከተ ከግብፅ ጋር ምክንያታዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ በተደጋጋሚ ንግግር ማድረጓን አምባሳደሩ አጣቅሰዋል።

አያይዘውም ግብፅ ለቀጣናው አገራትን ሰላም እና ትብብር "ዋጋ እንደማትሰጥ" እንዲሁም በአጎራባች አገራት መካከል "አለመረጋጋት እንዲፈጠር የጦር መሣሪያ በማቅረብ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነትን እንደምታራምድ" ከስሰዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጉዳይ "ዓለም አቀፋዊ" ለማድረግ እየሞከረች እንደሆነ የተናገሩት አምባሳደር ዮሴፍ፤ ግብፅ የተመድን መድረክ "ለጠባብ የፖለቲካ ግብ" እንዳዋለች እንዲሁም ይህንንም "ለአገር ውስጥና ቀጣናዊ ጉዳዮች ትኩረት እንዳይቸር ለማድረግ እንደምትጠቀምበት" ገልጸዋል።

ግብፅ በኃይል ከተሞላ አካሄድ ይልቅ ገንቢ በሆነ አካሄድ ላይ እንድታተኩርም አሳስበዋል።

የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ለግድቡ ጉዳይ እልባት ለመስጠት ዝግጁ ብትሆንም ኢትዮጵያ ለመተባበር ፈቃደኛ እንዳልሆነች ጠቅሰዋል።

"በዓለም አቀፍ ሕግ ለመዳኘት ዝግጁ ከሆኑ እኛም ጉዳዩን በሕግ ለመያዝ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነን። እውነታው ግን [በኢትዮጵያ በኩል] እንዲህ ያለ ፍላጎት አለመኖሩ ነው" በማለት አክለዋል።

በተመድ ስምምነት እና በዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት ግብፅ ከዓባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ ደኅንነቷን የማስጠበቅ መብት እንዳላት ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ በማዘናጋት የሚሊዮኖችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥላለች። መብታችን ሲጣስ ዝም አንልም" ብለዋል ሚኒስትሩ።

ሱዳን በ2021 ግብፅ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በከፈተችው አቤቱታ ላይ የተቀላቀለች ሲሆን በ2025 ደግሞ ሱዳን በተናጠል ጉዳዩን ወደ ምክር ቤቱ ወስዳዋለች።

ከዚህ ቀደምም እአአ በ2020 ግብፅ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጉዳይ ወደ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት መውሰዷ ይታወሳል።

በ2021 በግብፅ እና በሱዳን የጋራ ጥያቄ ምክር ቤቱ በግድቡ ዙርያ ውይይት አድርጓል። ኢትዮጵያ እየወሰደች ያለው "የተናጠል እርምጃ ለቀጣናው መረጋጋት አደጋ ነው" ሲሉ አገራቱ ከስሰዋል።

የፀጥታው ምክር ቤት ውይይት ሦስቱ አገራት "የሦስትዮሽ ተቀባይነት ያለው አሳሪ ስምምነት" ላይ እንዲደርሱ ምክረ ሐሳብ ቢያስቀምጥም፤ አገራቱ ለዓመታት ያደረጓቸው ውይይቶች ውጤታማ አልሆኑም።