ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቡርቃ ለብሰው ምክር ቤት የተገኙት አውስትራሊያዊት ሴናተር ከሥራ ታገዱ
አውስትራሊያ ውስጥ ቡርቃ ለብሶ መንቀሳቀስ እንዲታገድ ጫና ለማሳደር በሚል ይህንኑ ኢስላማዊ ልብስ አድርገው በምክር ቤት የተገኙት ሴናተር ለአንድ ሳምንት ከሥራ ታገዱ።
ፖሊን ሀንሰን የተባሉት ሴናተር ቡርቃ ለብሰው ምክር ቤት መገኘታቸው "ፍጹም ዘረኛነት ነው" ሲሉ የሥራ ባልደረባቸውን ወቅሰዋል።
የክዊንስላንድ ሴናተር ፀረ ስደተኞች የሆነው 'ዋን ኔሽን' ፓርቲ አባል ናቸው።
ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ሙሉ ፊት እና ሰውነት የሚሸፍነውን ቡርቃ መልበስ የሚከለክል ሕግ እንዲወጣ ጫና ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ሴናተሯ ቡርቃ ለብሰው ምክር ቤት ሲገኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ሴኔቱ ያቀረቡትን ረቂቅ ሕግ ስላልተቀበለው ተቃውሟቸውን ለማሳየት ቡርቃ መልበሳቸውን ተናግረዋል።
ረቂቅ ሕጉን በምክር ቤት እንዳያቀርቡ ሕግ አውጪዎች ከተከላከሏቸው በኋላ ቡርቃ ለብሰው ወደ ምክር ቤቱ ገብተዋል።
የሙስሊም ግሪንስ ሴናተር መሕረን ፋሩቂ "ዘረኛ ሴናተር ናት። ያሳየችው ባህሪ ፍጹም ዘረኛነት የተሞላው ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አምና የአውስትራሊያ ፌደራል ፍርድ ቤት ሴናተር መሕረን ፋሩቂ፤ ቡርቃ በለበሱት ሴናተር ፖሊን ሀንሰን የዘር መድልዎ እንደደረሰባቸው ወስኗል።
ሴናተር ፖሊን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ አቤቱታ አሰምተዋል።
ሌላዋ የምዕራብ አውስትራሊያ ሴናተር ፋጢማ ፔይማን ድርጊቱን "አሳፋሪ" ሲሉ ገልጸዋል።
የሴኔቱ መሪ ሆነው የሚያገለግሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔኒ ዎንግ በበኩላቸው ሴናተሯ ፖሊን "ለዓመታት በተቃውሞ ስም መድልዎ እያሳየች ስለሆነ" ሴናተሯን ክፉኛ እንደሚነቅፉ ተናገረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ፔኒ በይፋ የሴኔቱ አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲያነሱ የሚጠይቅ ረቂቅ (motion to censure) አቅርበው በ55 የድጋፍ እና በአምስት የተቃውሞ ድምጽ ጸድቋል።
የሴናተሯ ድርጊት "ሰዎችን በሃይማኖታቸው ለማሸማቀቅ እና ለመቀለድ ያለመ" እንዲሁም አውስትራሊያውያን ሙስሊሞችን "ያዋረደ" ነው ሲሉም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም "ፖሊን የአውስትራሊያ ሴኔት አባል ለመሆን ብቁ አይደለችም" ብለው ነቅፈዋል።
ፖሊን በፌስቡክ ገጻቸው "ቡርቃ እንድለብስ ካልፈለጉ ያግዱት" ብለዋል።
እአአ በ2017 ቡርቃ ለብሰው ምክር ቤት በመሄድ ቡርቃ በአውስትራሊያ እንዲታገድ ጠይቀዋል።
በ2016 "አውስትራሊያ በሙስሊሞች ልትዋጥ ነው" ብለው በመናገራቸው በርካቶች ነቅፈዋቸዋል።
እአአ በ1996 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተደረገ "አውስትራሊያ በእስያውያን ተውጣለች" የሚለውን ንግግር በመቅዳት ነበር የ2016ቱን አወዛጋቢ ንግግር ያደረጉት።