በአክሱም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ እንዳይለብሱ መከልከላቸውን ተከትሎ የተፈጠረው ምንድን ነው?

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃብ እንዳይለብሱ በመከልከላቸው ትምሕርት ማቋረጣችን ተከትሎ የከተማዋን ትምህርት ቢሮ ወቅሷል።

ምክር ቤቱ በአክሱም ከተማ እየሆነ ያለውን ጉዳይ ሲከታተል መቆየቱን አስታውቆ ነገር ግን እልባት እንዳላገኘ መረዳቱን ገልጿል።

በአክሱም ከተማ የሚገኙ አምስት የሚሆኑ ትምሕርት ቤቶች ሂጃብ መከልከላቸውን ተከትሎ ከትምሕርት ገበታ መስተጓጎልን ጨምሮ እስር እና እንግልት እንደደረሰባቸው ተማሪዎች እና ወላጆች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ክልከላውን የጣለው የትግራይ ክልል ትምሕርት ቢሮ፤ የትምህርት ቤቶች አደረጃጀት እና መመሪያ የተባለው ሕግ ላይ ተመስርቶ እንደሆነ አስታውቋል።

ክልከላውን ያደረጉት በአክሱም የሚገኙት ወራዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የአክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት፣ አብርሃ አፅብሃ፣ ቀዳማዊ ሚኒሊክ እና ክንደያ ትምህርት ቤቶች መሆናቸው ተነግሯል።

የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት "የአክሱም ከተማ ሙስሊም ነዋሪዎች ለዘመናት የነበረባቸው የእምነት ነፃነት፣ የመስገጃ ቦታ ችግር እና የቀብር ቦታ ችግር እልባት ያልተሰጠውና ወደ ባሰ ሁኔታ እየሄደ ነው" ሲል ቅሬታውን አሰምቷል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው በከተማዋ ያለው ሁኔታ "የሀገሪቱን እሴት የሚሸረሽር ተግባር" ስለሆነ "በጥብቅ እናወግዛለን" ብሏል።

ቢቢሲ ያናገራት ተማሪ ከዚህ ቀደም ሂጃቧን ለብሳ ትምሕርቷን ትማር እንደነበር ገልፃ፤ ካለፉት ሦስት ሳምንታት ጀምሮ ግን ትምሕርት መታደም መከልከሏን አስታውቃለች።

"ሂጃብ አታድርጉ በሚል በወጣ ህግ መሰረት ትምህርት አቋርጫለሁ። 'ሂጃባችሁን ካላወለቃችሁ አትማሩም' ነው የሚሉን። አሁን ከትምሕርት ገበታ ውጭ ነው ያደረጉን። እኔ እስከ ዛሬ ሂጃቤን አውልቄ አላውቅም። ሁሌም ቢሆን ትምህርት ቤት ሂጃቤ ለብሼ ነበር የምሄደው" ብላለች።

ሌላ ትምሕርቷን እንዳቋረጠች የተናገረች ተማሪም ከትምሕርት ቤት በፖሊስ እንዲወጡ መደረጋቸውን ተናግራለች።

"ከዚህ [ከትምህርት ቤት] ልቀቁ አለበለዚያ ፖሊስ እንጠራባችኋለን ተባልን። ከዚያ ፖሊስ ጠርተው 'እነዚህ ናቸው ዋነኛ በጥባጭ' ብለው አስወጡን። ከትናንት በስቲያ ከዚያ በፊትም ሄደን ነበር። ግን አራት ፖሊሶች ትምህርት ቤቱ ደጃፍ ላይ ቆመዋል። እንዳያዩን ብለን ሸሸን" በማለት የነበረውን ሁነት ተናግራለች።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት "የሙስሊም ማኅበረሰቡ መብቶች ሳይሸራረፉ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆኑ እና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ይህን እንዲያስፈፅሙ" ጠይቆ "ድርጊቱን በፈፀሙ ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ" አሳስቧል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተማሪዎች እና ወላጆች ኃይማኖታዊ መብታችንን በመጠየቃችን ለእንግልት እና እስር ተዳርገናል ይላሉ።

ወ/ሮ ናአራይሚ መሐመድ ልጃቸው ከትምሕርት ቤት ተወስዳ ስለመታሰሯ ተናግረዋል።

ልጃቸው ትምሕርቷን ወይም ኃይማኖቷን እንድትመርጥ በፖሊስ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።

"'ልጆቻችሁ የትምሕርት ቤቱን ህግ አክብረው ይመለሱ ወይም ወደ መስጊድ ይሂዱ፤ አንዱን ምረጡ' አሉን" ብለዋል።

በቀዳማዊ ሚኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑ መብርሃቱ ጸጋዬ ሂጃብን በትምህርት ቤቶች መልበስን የሚከለክለው ህግ ቀድሞ የነበረ ነው ይላሉ።

ክልከላውን የጣለው ክልሉ ነው የሚሉት መምህሩ፤ የትምህርት ቤቶች አደረጃጀት እና መመሪያ የተባለው ሕግ ዳግም መተግበር መጀመሩን ገልጸዋል።

"የትምህርት ቤቶች አደረጃጀት እና መመሪያ በሚል 1997 ዓ.ም.፤ ከዚያ በኋላም በ2003 ዓ.ም. የወጣ መመሪያ ነው። መመሪያው ወደ ትምህርት ቤት ለመግባት ኮፍያ፣ ሻርፕ፣ ሂጃብ እና እንደዚህ አይነት ነገሮች አይፈቀዱም ይላል። በክልል ደረጃ የወጣ መመሪያ ነው። ጦርነቱ እስኪጀመር ድረስ ተግባራዊ እየተደረገ ነበር። በመሀል ቸል ተብሎ አሁን ወደ ትግበራ ስለተመለሰ ነው አዲስ ነገር የመሰለው እንጂ የተለየ ነገር ኖሮ አይደለም" ብለዋል።

ወ/ሮ ነጃት አብዱልቃድር የተባሉ ወላጅ በተማሪዎች ሂጃብ አለባበስ ዙሪያ ከትምሕርት ቤቶች ጋር በተወካዮቻቸው በኩል ውይይት ቢያደርጉም መልካም ምላሽ እንዳላገኙ ገልፀዋል።

"እኛ የመረጥናቸው ተወካይ ሴቶች ወደ ትምሕርት ቤቶች ሄደው እባካችሁ ብለው ተማፅነዋል። ቢያንስ 12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ፎርም ሲሞሉ የሚነሱት ፎቶ ለታሪክም ሲለሚቀር ሂጃብ አድርገው ይነሱ ብለን ነበር። ለሱ እንኳ ፍቀዱላቸው ብለን ጠይቀን ነበር። ዛሬም ነገም አይፈቀድም፤ በድምጽ ብልጫ ውድቅ ያደረግነው ነው ብለው ዘጉን" ሲሉ የወላጆችን ጥረት ተናግረዋል።

ክልከላው ከተደረገበት ትምሕርት ቤቶች መካከል አንዱ የሆነው አክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት ስዩም ካህሳይ የሂጃብን ጥያቄ "ፖለቲካዊ ዓላማ" የያዘ ነው በማለት ጥያቄውን አውግዘዋል።

ርዕሰ መምህሩ ፖለቲካዊ ዓላማ ስላሉት ጉዳይ ባያብራሩም፤ "ሂጃብ የሚለው ጥያቄ እንዲነሳ የሆነው ለግርግር መነሻ እንዲሆን ለማድረግ እንጂ በአካባቢው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት ያደረገ አይደለም። የዚህ ጥያቄ ምንጩ ሌላ ነው። ግፊት የሚደረገው ከላይ ነው። ለፖለቲካ ፍጆታ ተፈልጎ ነው" በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

ቢቢሲ ከትግራይ ክልል ትምሕርት ቢሮ እና ከክልሉ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ምላሽ ለማድረግ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ክልከላውን "ኃይማኖታዊ ትንኮሳ" በሚል የገለፀው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤቱ፤ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ እና ሌሎች የእምነት ተቋማት ይህንን ጉዳይ እንዲያወግዙም ጥሪ አቅቧል።

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ የተፈረመ እና ለክልሉ እስልምና ጉዳዮች የቀረበ ነው የተባለ ደብዳቤ "አዲስ ክልከላ እንደሌለ እና ችግሩ እንደሚቀረፍ" የሚቀልጽ መሆኑን ቢቢሲ ለመመልከት ችሏል።

ከሙስሊም ሴት ተማሪዎች አለባበስ ጋር በተያያዘ በ2017 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበበባ ትምሕርት ቤቶችም ተመሳሳይ ክልከላዎች ተደርገው እንደነበር እና ትምሕርት ለቀናት መስተጓጎሉ የሚታወስ ነው።