በግብፅ ሒጃብ የሚለብሱ ሴቶች መድልዎ እና መገለል እየደረሰባቸው ነው

ሙስሊም ሴቶች ጸጉራቸውን የሚሸፍኑበት ሻሽ (ሒጃብ) ከፍተኛ የሙስሊም ቁጥር ባለባት ግብፅ ለመገለል እንደሚዳርግ አንድ የቢቢሲ አረብኛ የምርመራ ዘገባ አረጋገጠ።

በግብፅ ሒጃብ የሚጠመጥሙ ሴቶች በተለይ በውድ ሱፐርማርኬት፣ በውድ ምግብ ቤቶችም ሆነ ሰው በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች እንዲገኙ አይበረታቱም።

አለመበረታታት ብቻም ሳይሆን እነዚህ መዝናኛዎች እና ምግብ ቤቶች ሒጃብ ለባሽ የሆኑ ሴቶች እንዳይመጡባቸው ማንኛውንም ጥረት ከማድረግ አይቦዝኑም።

ቢቢሲ አረብኛ በሠራው በዚህ የምርመራ ዘገባ በሒጃብ ለባሽ ሴቶች የሚደረገው መገለልና መገፋት በተለያዩ ከፍ ባሉ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተንሰራፍቶ እንደሚገኝም ማረጋገጥ ችሏል።

ይህ ድርጊት የግብፅ ሕገ መንግሥትን የሚጻረር ቢሆንም ድርጊቱ ግን እየባሰበት ሄዷል።

የግብፅ ሕገ መንግሥት በጾታ፣ በዘር እና በማኅበራዊ ደረጃ የትኛውንም ዓይነት መገለልን ይከለክላል።

ይህ በሒጃብ ለባሽ የግብፅ ሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን መድሎ በተመለከተ ግብፃውያን እንደ አውሮፓዊያኑ ከ2015 ጀምሮ ሲታገሉት ቆይተዋል።

ጉዳዩን ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ በማምጣትም የሕዝብ አጀንዳ ለማድረግ የሞከሩ ሴቶች ነበሩ።

ከእነዚህ መካከልም አንዷ ማያር ኦማር ናት።

ማያር ዕድሜዋ 25 ሲሆን የአንድ ጥናት ቡድን ኃላፊ ናት። በካይሮ የምትኖረዋ ማያር በሥራ አጋጣሚ ከፍ ያሉ ሬስቶራንቶች መሄድ ይኖርባታል።

ነገር ግን በር ላይ ‘ሒጃብ ለብሰሽማ አትገቢም’ እየተባለች መከራዋን ማየቷን ለቢቢሲ መስክራለች።

“አንድ ቦታ ስትሄጂ ራስሽን ሆነሽ መሆን አለበት፤ እነዚህ ቦታዎች ያን አይፈቅዱም” ትላለች።

‘ሒጃቢ የሕይወት ዘይቤዬ’ በሚል የተመሠረተ አንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ቡድን እነዚህ ሒጃብ ለብሳችሁ አትገቡም የሚሉ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በማጋለጥ ተሰማርቶ ይገኛል።

ቢቢሲ እነዚህ በቡድኑ የተጠቀሱ በርካታ ሥፍራዎች ድረስ ሄዶ ጉዳዩን ለማረጋገጥ ሞክሯል።

ናዳ ናሻት የሕግ አዋቂና የሴቶች መብት አቀንቃኝ ናት። “ዋናው የችግሩ መሠረት መደብ ነው” ትላለች።

“ብዙዎቹ መካከለኛ እና ከፍተኛ መደብ ተስተናጋጅ ያላቸው አገልግሎት ሰጪዎች ሒጃብ የለበሰች ሴት እንድትመጣባቸው አይፈልጉም።”

ናዳ ናሻት በሒጃብ መገለልና መድልዎ በስፋት የሚደርሰው ከፍተኛ መደብ ነን በሚሉ አገልግሎት ሰጪዎች ይሁን እንጂ፣ በታችኛው መደብ መድልዎው በጭራሽ የለም ማለት እንዳልሆነ ታስረዳለች።

ቢቢሲ አረብኛ ይህን ክስ ለማረጋገጥ 15 ከፍ ያሉ በካይሮ የሚገኙ ሬስቶራንቶችና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች ለመገልገል ‘ሪዘርቬሽን’ [ቦታ ለማስያዝ] ጠይቆ ነበር።

ከ15ቱ ውስጥ 11ዱ ሒጃብ የሚለብሱ ሴቶችን እንደማያስተናግዱ በግልጽ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ሁኔታዎችን ይበልጥ ለማረጋገጥ ባለትዳሮችን በድብቅ ወደእነዚህ ስፍራዎች ልኮም ነበር።

‘ሚስት’ ሒጃብ እንድትለብስ ተደርጋ ነበር።

ከፍተኛ የኑሮ መደብ ላይ የሚገኙ ደንበኞች ይስተናገዱበታልወደሚባለው የካይሮ ዛማሌክ ሰፈር፣ ላዎበርጂኒ ሬስቶራንት የተላኩት እነዚህ ባልና ሚስት እንዳይገቡ ተከልክለዋል።

የተሰጣቸው ምላሽ “ውስጥ መጠጥ ስለሚሸጥ ሒጃብ የለበሰች ሴት ምቾት አይሰማትም” የሚል ሰበብ ነው።

የዚህ ሬስቶራንት ሥራ አስኪያጅ በመጨረሻ እቅጩን ለመናገር ተገዷል፤ “ሒጃብ ለባሽ ተስተናጋጅ አናስተናግድም።”

በኋላ ላይ እንደ ቢቢሲ ቅሬታ በቀረበበት ጊዜ ግን ድርጅቱ በፍጹም ሒጃብ በሚለብሱ ሴቶች ላይ መድልዎና መገለልን እንደማያደርስ፣ ድርጊቱንም እንደሚያወግዝ አስታውቋል።

በዚሁ ዛማሊክ ሰፈር ካዛን በሚባል አገልግሎት መስጫ ሒጃብ የለበሱ ሴቶች በጥበቃ እንዳይገቡ ተከልክለዋል።

አንዲያሞ በሚባል ሬስቶራንት ደግሞ ባለትዳር የሆኑ ጥንዶች ሚስት ሒጃብ በመልበሷ እንዳይገቡ ሲደረጉ እንደሚከሱ በማስፈራራታቸው እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል። ሆኖም ግን በሬስቶራንቱ ደበቅ ባለ ሥፍራ እንዲቀመጡ ታዘዋል።

ቢቢሲ ጉዳዩን ለግብፅ የቱሪዝም ምክር ቤት ኃላፊ ኤደል አልሚስሪ ያቀረበላቸው ሲሆን፣ እሳቸው ይህን ድርጊት እንደማያውቁ፣ እንዲህ ዓይነት ሕግ እንደሌለና ድርጊቱ የሚፈጸም ከሆነም መወገዝ እንዳለበት ተናግረዋል።

ሒጃብ የሚለብሱ ሴቶች ከምግብ ቤቶች ብቻ ሳይሆን የሚገለሉት ለመዝናናት ወጣ ወዳሉ አካባቢዎች ሄደው ሆቴል ለመያዝም እንደሚቸገሩ ቢቢሲ ተረድቷል።

በካይሮ ይህን አገልግሎት የሚሰጥ ላ ቬስታ የሚባል ተቋምን ጨምሮ በርካታ የአፓርትመንት ኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ሒጃብ ለሚለብሱ ሴቶች አገልግሎት አይሰጡም።

ቢቢሲ ባልደረቦቹ ባልና ሚስት መስለው እንዲቀርቡና ‘ሚስት’ ሒጃብ እንድትለብስ በማድረግ ከዚህ ዝነኛ ከሆነው ላ ቬስታ ክለብ ቤት ለመግዛትና ለመከራየት ሞክሯል።

ሆኖም ቤት ሻጮችና አከራዮች ሒጃብ ለለበሱ ሴቶች ገበያው አስቸጋሪ እንደሆነ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋቸዋል።

አንድ የሪልስቴት ደላላ፣ በሽፋን ‘ሚስት’ መስላ ሒጃብ ለለበሰችው የቢቢሲ ባልደረባ ቁርጧን ነግሯታል።

“ላ ቪስታ ሒጃብ ለብሰሽ አያከራይሽም፤ ይህንንም በቀጥታ አላከራይም አይልሽም ግን ቤቱ ተይዟል ሲለቀቅ እንደውልልሻን ይሉሻል፤ ሆኖም አይደውሉልሽም” ሲል ለባልደረባችን ነግሯታል።

የቢቢሲ ባልደቦች ነገሩን ለመሞከር ያህል ሒጃብ ከለበሰችውና ‘ሚስት’ መስላ ከምትተውነው ሴት ጋር ላ ቪስታ ቢሮ ሄደው አፓርታማ ለመከራየት የጠየቁ ሲሆን “ሁሉም ተይዘዋል” የሚል ምላሽ አግኝተዋል።

በስልክ በተደጋጋሚ ቤቱ ተለቆ እንደሆነ ጠይቀው እንዳልተለቀቀ ተነግሯቸው ነበር።

ሆኖም እንደ ሚስት የምትተውነዋ የቢቢሲ ዘጋቢ፣ ሒጃቧን አውቅልቃ በሄደች ጊዜ የሚከራይ ቤት እንዳለ ተነግሯቸዋል።

ቢቢሲ የመዝናኛ አፓርትመነት አከራይ ኩባንያ የሆነውን ላ ቬስታን በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

አሚራ ሳቢር የግብፅ የምክር ቤት አባል ናት። ለሒጃብ ለባሽ ሴቶች መብት ድምጽ በማሰማት ትታወቃለች።

“በዚህ ረገድ የግብፅ ሕገ መንግሥት ድንጋጌ አሻሚ አይደለም፤ ይህ ለምን እንደሚሆን ጥያቄ ማንሳቴን እገፋበታለሁ፤ መድልዎና መገለሉን የሚፈጽሙም መቀጣት ይኖርባቸዋል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግራለች።