ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዝነኛዋ የሙዚቃ አቀንቃኝ ‘በእስልምና ትምህርት ቤቶች’ ላይ ቀልደሻል በሚል ታሰረች
“የቱርኳ ማዶና” በሚል ቅጽል የምትታወቀው ዝነኛዋ የሙዚቃ አቀንቃኝ ጉልሸን “ቀልድሽ መስመር አለፈ” በሚል ታስራለች።
የ46 ዓመቷ ጉልሻን የተመሠረተባት ክስ በማኅበረሰብ ዘንድ “ጥላቻን መንዛትና መዝራት” የሚል ነው።
የዚህች ዝነኛ አቀንቃኝ እስር በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን መንግሥትን 'አበጀህ' ያሉትም ጥቂት አይደሉም።
ዘፋኟ ጉልሻን መስመር አልፈሻል ያስባላትን ቀልድ የቀለደችው ከወራት በፊት ነው።
መድረክ ላይ ሆና አንድ የእሷ ሙዚቃ ባንድ አባል የሆነ ወዳጇን፣ “አንተ’ኮ በጾታ አፈንጋጭ የሆንከው የኢማም ሓጢብ የሃማኖት ትምህርት ቤት በመማርህ ነው” ስትለው ይሰማል።
ለዚህ እስር ያበቃትም ይህ ቀልዷ ነው።
እንዲህ የተባለው የሙዚቃ ባንዱ አባል በስም አልተገለጸም፤ በተንቀሳቃሽ ምሥሉም ላይ አይታይም።
ኢማም ሐጢብ የሃይማኖት ትምህርት ቤቶች በቱርክ ሲቋቋሙ ሰባኪያን እና ኢማሞችን ለማፍራት ነበር።
አቀንቃኟ ይህን ቀልድ መድረክ ላይ ከቀለደችው ሰንበትበት ቢልም “ያልተገባ” የተባለው ቀልድ እንደ አዲስ በማኅበራዊ ሚዲያ መዛመቱን ተከትሎ ሐሙስ ጠዋት ፖሊስ ከመኖርያ ቤቷ ወስዶ ወደ ዘብጥያ አውርዷታል።
አንዳንዶች ይህ እስር በቱርክ የፖለቲካ እና የሃይማኖት መስመር የቱ ጋ ነው የሚለውን የሕዝብ ሙግት ዳግም እንዲቀሰቀስ አስችሏል ይላሉ።
በተለይ የዘፋኟ እስር በሚቀጥለው ዓመት ለምርጫ እየተዘጋጁ ላሉት ረሲብ ጣይብ ኤርዶዋን ድጋፍ ለማሰባሰብ የተደረገ እርምጃ ነው ብለው የሚጠረጥሩ አልጠፉም።
የጣይብ ኤርዶዋን የድጋፍ መሠረት በቱርክ የሃይማኖት ወግ አጥባቂዎችን የሚወክል ነው።
ጉልሻን ለዓመታት በቱርክ ወግ አጥባቂ ማኅበረሰብ ዘንድ ፀረ ኢስላምና ፀረ ሞራል ተደርጋ ስትወገዝ ኖራለች።
አቀንቃኟ በይፋ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ደጋፊ በመሆን ትታወቃለች።
ጉልሻን በዚህ የሃማኖት ትምህርት ቤት ላይ በተናገረችው ቀልድ ይፋዊ ይቅርታ መጠየቋ ይታወሳል።
“ይህን በጓደኞቼ መሀል የተናገርኩትን ቀልድ ለጥጠው የወሰዱት በማኅበረሰባችን መካከል መራራቅና መቃቃር እንዲፈጠር የሚሹ ናቸው” ስትልም ወቀሳ አቅርባ ነበር።
የእሷን እስር ተከትሎ ዝነኛ የዓለማችን ሙዚቀኞች ጎልሻን ትፈታ የሚል ቅስቀሳ እያደረጉላት ነው።
በቱርክ የአሁኑ መሪ ራሲብ ጣይብ ኤርዶዋንን ጨምሮ በርካታ የፓርቲ ሰዎቻቸው ከቱርክ የሃይማኖት ትምህርት ቤቶች የተማሩ ናቸው።
ኢማም ሓጢብ የሚባሉት የዕደ ጥበብ እና የሃይማኖት ትምህርት ቤቶቹ ቀደም ባለው ዘመን የተቋቋሙት በዋናነት የኢስላም ኢማሞችን እና ሰባኪያንን ለማስመረቅ ነበር።
የጉልሸንን እስር ተከትሎ ለመንግሥት ይወግናል የሚባለው 'የኒ ሳፋክ' ጋዜጣ በትናንት አርብ ዕትሙ፣ “ጅላጅሏ ሙዚቀኛ ቀዩን መስመር አለፈች” ሲል ለዜናው ርዕስ ሰጥቷል።