“ያለብኝ ራስ ምታት እየጮህኩ ጭንቅላቴን ከግድግዳ እንዳጋጭ ያስገድደኛል”

ዳረን ፍራንኪሽ ለ17 ዓመታት ያክል ከባድ የራስ ምታት ሲያሰቃየው ኖሯል።

ይህ ራስ ምታት ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ጭንቅላቱን ከግድግዳ እያላተመ እና እየጮኸ ነው ስቃዩን የሚወጣው።

የ53 ዓመቱ እንግሊዛዊ ራስ ምታቱ ሲነሳ አንዳች ቅቤ የጠገበ ዱላ ጭንቅላቱን የመታው ያህል ይሰማዋለ። ይህ አልበቃ ብሎ ዓይኑን በጩቤ የተወጋ ያክል ያመዋል።

በእንግሊዝኛው ክላስተር ሄድኤክ የተሰኘ ስም ያለው ይህ ራስ ምታት እጅግ በጣም ስቃዩ የበዛ ነው።

“በኮቪድ ወቅት ወደ ሆስፒታል ስሄድ ትዝ ይለኛል። አውቶቡስ ሲመታ ዘለህ ግባ ግባ ይለኛል። ራስ ማጥፋት የሚያስመኝ ራስ ምታት ነው ቢሉ አይገርምም” ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።

የሆርቲካልቸር ኢንጂነር የሆነው ዳረን “መች እንደሚጀምረኝ ስለማላውቅት በፍርሀት ነው የምኖረው” ይላል።

“ይህ ስነ-ልቡናዊ ስቃይ ነው። በየትኛውም ሰዓት ሊጀምረኝ ይችላል። በጣም ያስፈራኛል።”

ይህ ዓይነቱ ራስ ምታት ከ15 ደቂቃ ጀምሮ እስከ 3 ሰዓታት ሊቆይ የሚችል ሲሆን በቀን ሰባት አሊያም ስምንት ጊዜ ይነሳል።

ነገር ግን ዳረን ለ12 ሰዓታት የቆየ ራስ ምታት እንዳጋጠመው ያስታውሳል።

ራስ ምታቱ ሲጀምረው በግራ ጭንቅላቱ በኩል ከግራ ዓይኑ ከፍ ብሎ ባለው ክፍል ነው።

ግራ ዓይኑ መቅላት ሲጀምር እና ውሀ ሲሞላው እንዲሁም አፍንጫው ሲደፈን እና ጭንቅላቱ በአንዳች ስቃይ ሲሞላ ራስ ምታቱ ጀመረ ማለት ነው።

“የማደርገው ይጠፋኛል። በትራስ ታፍኜ እጮኃለሁ። ጭንቅላቴን ወስጄ ከግድግዳ አሊያም ከአንዳች ጠንካራ ነገር ጋር አላትመዋለሁ። ብርሀን ካየሁ ስለሚብስኝ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እቀመጣለሁ።”

ዳረን አንዳንድ ጊዜ ውሀ የሚሞላውን ግራ ዓይኑን ሸፍኖ የእግር ጉዞ ለማድረግ እንደሚወጣ ይናገራል።

“ራስ ምታቱ ሲመጣብኝ ከማንም ጋር መነጋገር አልችልም” ይላል።

እሱ እንደሚለው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ራስ ምታቱ በተደጋጋሚ እየጎበኘው መሆኑ ሳያንስ ከተለመደው ጊዜ በላይ እየቆየ ነው።

ባለፈው ግንቦት ሁለት ጊዜ ወደ ሕክምና መስጫ እንዲሄድ ያደረጉት ሁለት ራስ ምታቶች እያንዳንዳቸው ለ12 ሰዓታት የቆዩ ናቸው።

‘ክላስተር ሄድኤክ’ ምንድነው?

ክላስተር ሄድኤክ የተሰኘው የራስ ምታት ዓይነት ከ1000 ሰዎች መካከል አንድ ሰው ነው የሚያጠቃው።

ይህ ማለት በዩናይትድ ኪንግደም 65 ሺህ ሰዎች በዚህ ራስ ምታት ይሰቃያሉ ማለት ነው።

“ይህ ከራስ ምታት በላይ ነው” ይላሉ የብሬይን ሪሰርች ዩኬ የጥናት ባለሙያዋ ኬቲ ማርቲን።

“ዳረን እንደገለጠው ይህ ራስ ምታት እጅግ ከባድ ነው። መሸከም የሚችሉት አይደለም። ሰዎች በስቃይ እንዲጮሁ የሚያደርግና ከራስ ምታቱ ለመገላገል ከግድግዳ የሚያላትም ነው።”

በዚህ ራስ ምታት የሚሰቃዩ አብዛኛዎቹ ሰዎች ዕድሜያቸው ከ30 በላይ ሰዎች ናቸው።

ይህ ራስ ምታት ብዙውን ጊዜ ከሴቶች በላይ በወንዶች ላይ ይስተዋላል።

አንዳንድ ጊዜ ይህ ራስ ምታት በጥቂት ቀናት እየቆየ ይመጣል፤ በሌላው ጊዜ ደግሞ ተጠቂዎችን በቀን በተደጋጋሚ ሊጎበኝ ይችላል።

ይህ ራስ ምታት ያለባቸው ሰዎች በተደጋጋሚ ሆስፒታል ሊጎበኙ ግድ ይላቸዋል።

የሕይወት ዘይቤን የሚያመሰቃቅለው ይህ ራስ ምታት ተጠቂዎችን ሥራ አልባ ሊያደርጋቸው ይችላል።

አልፎም ይህ ራስምታት ተጠቂዎችን ድባቴ ሊጥልና የራስ ማጥፋት አዝማሚያቸውን በሶስት እጥፍ ሊጨምረው እንደሚችል ጥናቶች ይጠቁማሉ።

በሽታው መድኃኒት የለውም።

ዳረን ለመጀመሪያ ጊዜ ይህ ራስ ምታት የጀመረው በ37 ዓመቱ ነው።

“ከቤተሰቦቼ ጋር ልዝናና ወደ ፕራግ አቅንቼ ነበር። በጣም ኃይለኛ ራስ ምታት ሲጀምረኝ መጀመሪያ የመሰለኝ የጭንቅላቴ ዕጢ ነበር” ይላል የሁለት ልጆች አባት የሆነው ዳረን።

ይህ ራስ ምታት ከጀመረው ወዲህ እንደ ስቴሮይድ፣ ሊቲየም፣ የልብ ሕክምና እና የሚጥል በሽታ [ኤፒለፕሲ] መድኃኒቶችን ወስዷል።

“የሚጥል በሽታ የለብኝም። ነገር ግን ምናልባት ከሠራ በሚል መድኃኒት ሰጡኝ። ነገር ግን የትኛውም መድኃኒት ሊሠራ አልቻለም። አንዳንዴ የሚሠራልኝ በመርፌ የሚሰጥ መድኃኒት ነው።”

ዳረን ሕመሙን ለማስታገስ የሚውል ኦክሲጂን የሚያመነጭ ብልቃጥ ቤቱ አይጠፋም።

ሕመሙ እንዲቀልለት በሚል የተለያዩ ምግቦች ሞክሯል፤ ከአልኮል መጠጦችና ትምባሆ ማጨስ አቁሟል። ነገር ግን ሕመሙ ሊቆም አልቻለም።

“ቀጣዩ እርምጃ ወደ ጭንቅላቴ የሚሄደውን ነርቭ የሚከላከል መድኃኒት መወጋት ነው” ይላል።

ይህ ሕክምና በሽታውን ለጥቂት ጊዜም ቢሆን የሚያስታግስ ነው። ስቴሮይዱ ለአንድ ዓመት ያክል ራስ ምታቱ የሚመጣበት ጊዜ ሊቀንስለት ይችላል።

“ትዳሬ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል። ለፍቺዬ ምክንያት ከሆኑ ነገሮች አንዱ ነው። ልጆቼ የኔን ጩኸት እየሰሙ ማደጋቸው ያሳዝነኛል።”

ዳረን ለጊዜው ከዚህ ራስ ምታት ጋር ከመኖር ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም።