ታዋቂ የሆሊዉድ ዳይሬክተር እና ተዋናይ የሆኑ ወላጆቹን በመግደል የተጠረጠረው ልጃቸው በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ክስ ተመሰረተበት

የሎስ አንጀለስ አቃቤ ሕግ የሆሊውድ ዳይሬክተር እና ተዋናይ የሆኑትን ወላጆቹን በመግደል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለው ልጃቸው ላይ የወንጀል ክስ መሠረተ።

የሆሊውድ ዳይሬክተር ሮብ ራይነር እና በባለቤቱ ሚሼል ሲንገር ሞት ምክንያት ልጃቸው ኒክ ራይነር በቁጥጥር ሥር መዋሉ ይታወሳል።

ኒክ ራይነር ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ግድያ ክሶች የቀረበበት መሆኑን የአካባቢው አቃቤ ሕግ ናታን ሆችማን ተናግረዋል።

ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ያለ ይግባኝ የእድሜ ልክ እስራት ወይም የሞት ቅጣት ሊፈረድበት ይችላል።

ልጃቸው ላይ አስፈላጊው የጤና ምርመራ በእስር ቤቱ ባለሥልጣናት ከተደረገ በኋላ ፍርድ ቤት ቀርቦ በይፋ ክሱ እንደሚመሰረት አቃቤ ሕግ ሆችማን ተናግረዋል።

ክሱ የተመሰረተው ባልና ሚስቱ በብሬንትዉድ ካሊፎርኒያ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ በስለት በርካታ ቦታ ተወግተው ሞተው ከተገኙ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።

ክሱ ላይ ራይነር ወላጆቹን ለመግደል ቢላዋ ተጠቅሟል የሚል "ልዩ ክስ" መካተቱ ተገልጿል።

ሆችማን ማክሰኞ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አቃቤ ሕጎች የሞት ቅጣት እንዲፈረድበት ይጠይቃሉ የሚለውን በተመለከተ ምንም ዓይነት ውሳኔ ላይ እንዳልተደረሰ ተናግረዋል።

የ32 ዓመቱ ተጠርጣሪ "አደገኛና ገዳይ የሆነ መሳሪያ፣ ቢላዋ" በመጠቀም ተከሷል።

ማክሰኞ ዕለት ዳኛ ፊት ቀርቦ በይፋ ክስ ይመሰረትበታል ተብሎ ይጠበቅ ነበር።

በኋላ ላይ የዲስትሪክቱ አቃቤ ሕግ ፍርድ ቤት ቀርቦ ክስ የመመስረት ሂደቱ ለሌላ ጊዜ እንደሚቆይ ተናግረዋል።

ዝነኛው የሆሊውድ ዳይሬክተር ሮብ ራይነር በተለያዩ ዘውጎች በርካታ ታዋቂ ፊልሞችን አዘጋጅቷል።

ከእነዚህም ውስጥ ዚስ ስፓይናል ታፕ፣ ሚዝሪ እና ኤ ፊው ጉድ ሜን ይገኙበታል።

ሚሼል ሲንገር ራይነር ተዋናይት፣ ፎቶግራፍ አንሺ እና ፕሮዲዩሰር እንዲሁም የፎቶግራፍ ኤጀንሲ እና ፕሮዳክሽን ኩባንያ የሆነው የራይነር ላይት መስራች ነበረች።

የሎስ አንጀለስ ፖሊስ ኃላፊ ጂም ማክዶኔል በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት "ይህ ወንጀል ለሬይን ቤተሰብ እና ለሚወዷቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለመላው ከተማም ልብ የሚሰብር ነው።"

"በዚህ አሳዛኝ አደጋ ለተጎዱ ሁሉ ጥልቅ ሐዘናችንን እንገልፃለን።"

አቃቤ ሕግ ሆችማን ግድያ የተፈጸመበት መሳሪያ ተገኝቶ እነደሆን ተጠይቀው ይህ ይፋ የሚሆነው በችሎት ፊት ነው ሲሉ መልሰዋል።

ባለሥልጣናት ዝነኞቹን የሆሊውድ ዳይሬክተር እና ተዋናይ ባለትዳሮች ለሞት ያበቃው ትክክለኛ መንስዔ፣ ግድያው የተጸፀመበት መንገድ እና ጊዜን የሚወስኑ መጠናቀቅ ያለባቸው የአስከሬን ምርመራዎች እንዳሉ ተናግረዋል።