አውስትራሊያ ቻይናን በመስጋት የመከላከያ ሠራዊቷን በአዲሰ መልክ ልታዘምን ነው

አውስትራሊያ መከላከያዋን በአዲስ መልክ ለማዘመን በፍጥነት እየሠራች እንደሆነ አንድ የአገሪቱ የመከላከያ ስትራቴጂ ግምገማ ሰነድ አመላከተ።

አውስትራሊያ ይህን ተግባር ማፋጠን ያስፈለጋት ዋንኛው ምክንያት የቻይና እያደገ ያለ ሠራዊት ስጋት እየሆነባት ስለመጣ ነው።

የመከላከያ ስትራቴጂክ ሰነዱ ከዚህ በኋላ አውስትራሊያ በባህር መከበቧ በራሱ በቂ ደኅንነት ሊሆናት አይችልም ይላል።

አሁን ዘመኑ የሚሳኤል እንደሆነና አገሪቱን የሚመጥን ዘመናዊ መከላከያ መገንባት ጊዜ የሚሰጠው ተግባር እንዳልሆነም ሰነዱ ይገመግማል።

በዚህም መሠረት የአውስትራሊያ መንግሥት ለዚህ የጦር ሠራዊት ማዘመኛ 19 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ ተጠቅሷል።

ይህ 110 ገጾችን የያዘው ሰነድ አውስራሊያ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ለመከላከያ ዝመና ያወጣችው ከፍተኛው ገንዘብ እንደሆነ ይጠቅሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ ይህ የመከላከያ ስትራቴጂ ሰነድ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ትልቁና ወሳኙ ነው ካሉ በኋላ ብሔራዊ ደኅንነታችንን ለመጠበቅ ሁልጊዜም ከጊዜው ጋር መራመድ ያሻል ብለዋል።

ይህ ሰነድ ይፋ የሆነው ቻይና ታይዋንን በተመለከተ እያሳየችው ያለው ጠንካራ አቋምና ይህን ተከትሎም የወታደራዊ ውጥረት መፈጠሩን ተከትሎ ነው።

ቻይና አስፈላጊ ከሆነ አንድ ግዛቴ ናት የምትላትን ታይዋንን በኃይል ለመጠቅለል እንደምትችል በተደጋጋሚ ስትዝት ይሰማል።

የቻይና ባሕር ኃይል በደቡባዊ ቻይና ባሕር መገኘቱና ከዓለም አቀፍ ሕጎች በተጻረረ መልኩ በባሕሩ አካባቢ በከፊል የይገባኝ ጥያቄ ማንሳቱ አውስራሊያን ስጋት ላይ የጣለ ጉዳይ ነው።

ሰነዱ የቻይና ወታደራዊ ግንባታ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ትልቁ እንደሆነ ካወሳ በኋላ ይህ እየሆነ ያለው ግልጽነትና መተማመን በሌለበት የኢንዶ ፓሲፊክ አካባቢ ነው ይላል።

በዚህ ስትራቴጂክ ሰነድ መሠረት የአውስትራሊያ መከላከያ ከእግረኛ ሠራዊት ግንባታ ወደ ረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል ግንባት ይገባል፤ ይህም በአገሪቱ በሚመረቱ መሣሪያዎች ይሆናል ብለዋል መከላከያ ሚንስትር ሪቻርድ ማርለስ።

በቀጣይ የሚመረቱና ኢላማቸውን የማይስቱ ሚሳኤሎች በአካባቢው ተመጣጣኝ አቅም ለመፍጠር እንደሚረዱ መከላከያ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። ሚሳኤሎቹ 55 ኪሎ ሜትር ድረስ መምዘግዘግ የሚችሉ ናቸው።

ከዚህ ሌላ አውስትራሊያ ፈጣን ተንቀሳቃሽ ተተኳሽ ሮኬት ወይም በእንግሊዝኛ HIMARS የሚባሉትን የምድር ተዋጊ መሣሪያዎች እንደሚኖራት ተጠቅሷል። ዩክሬን እነዚህ ዘመናዊ መሣሪያዎች የሩሲያን ወረራ ለመመከት ተጠቅማባቸዋለች።

ሰነዱ አውስትራሊያ የመርከብ ግንባታ ዘርፍ ላይ ያላትን አቅም አጠናክራ እንደምትቀጥል ይጠቅሳል።

ባለፈው መጋቢት የአሜሪካ መንግሥት ዋጋቸው 900 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጉ 220 ክሩዝ ሚሳኤሎችን ለአውስትራሊያ እንዲሸጡ ማጽደቁ አይዘነጋም።