በቡርኪናፋሶ ጂሃዲስት እንደሆኑ በተጠረጠሩ ታጣቂዎች 50 ሴቶች መጠለፋቸው ተነገረ

በሰሜናዊ ቡርኪናፋሶ ጂሃዲስ እንደሆኑ የተጠረጠሩ ታጣቂዎች 50 ሴቶችን ጠልፈው እንደወሰዱ የአከባቢው ባለሥልጣናት አስታወቁ።

በከፍተኛ የምግብ እጥረት ሳቢያ ቅጠላ ቅጠል እና የዱር ፍሬዎቸን ሲሰበስቡ የነበሩ በሁለት ቡድን ውስጥ የነበሩ ሴቶች ተጠልፈው እንደተወሰዱ አርቢንዳ ተብሎ የሚጠራው አከባቢ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ከእነዚህ እገታዎች ጥቂት ሴቶች አምልጠው ጉዳዩን ነው ስለጉዳዩ ያሳወቁት።

ሴቶቹ የተጠለፉት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ እና አርብ ቢሆንም፣ ዜናው የተሰማው ግን አካባቢው በእስላማዊ ታጣቂዎች ሲከበብ ነው።

አንድ የአካባቢው ነዋሪ ስለክስተቱ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ሲናገሩ “በአካባቢው የሚላስ የሚቀመስ ሰላልነበረ በጋራ ተሰብበሰው ቅጠላ ቅጠል እና የዱር ፍሬዎችን ለመሰብሰብ ነበር ሴቶቹ የወጡት” ብሏል።

ሆኖም “ሐሙስ አመሻሽ ላይ ሳይመለሱ ሲቀሩ። ጋሪዎቻቸው ችግር የገጠማቸው ነበር የመሰለን። ነገር ግን ከጠለፋው ያመለጡ ሦስት ሴቶች የሆነውን ነገር አሳወቁን” ሲልም አክሏል።

በሳህል ቀጠና ከሚገኙ አካባቢዎች አንዷ የሆነችው አርቢንዳ በጂሃዲስት ታጣቂዎች የበረታ ጥቃት ደርሶባታል።

በዝቅተኛ የምግብ እጥረት ምክንያት በከፋ ርሃብ እና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ችግር ውስጥ የሚገኘው ይህ አካባቢ የመግቢያ እና መውጪያ መንገዶቹ በጂሃዲስት ታጣቂዎች ተዘግተዋል።

ባለፈው ወር ተቃዋሚዎች በአርቢንዳ ምግብ ለማግኘት መጋዘኖችን ሰብረው ገብተዋል።

በቡርኪናፋሶ ለአስርት ዓመታት የቆየው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።

ባለፈው ዓመት ሥልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊ መንግሥት የታጣቂዎቹን እንቅስቃሴ እቆጣጠራለሁ ቢሉም፣ ጥቃቶች ግን አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው።