ማይክሮሶፍት በቀይ ባሕር ስር በሚገኘው 'ኬብል' መቆረጥ ምክንያት አገልግሎቱ መስተጓጎሉን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Image
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ማይክሮሶፍት በቀይ ባሕር ስር በሚገኘው የኬብል መቆረጥ ምክንያት አዙሬ የተሰኘው የክላውድ (የመረጃ ማዕከል) አገልግሎቱ መስተጓጎሉን አስታወቀ።
በዚህ የባህር ስር ኬብል መቆረጥ ምክንያት በተባባሩት አረብ ኤምሬትስ እና በእስያ ባሉ አንዳንድ አገራት የአገልግሎት መቆራረጥ በሳምንቱ መጨረሻ እንዳጋጠመ ተገልጿል።
በመካከለኛው ምስራቅ ኢንተርኔት ፍሰት ላይ ያጋጠመው እክል በመረጃ ማዕከሉ አገልግሎት መዘግየት እንዳስከተለ በዓለማችን በክላውድ ኮምፒውቲንግ (የኮምፒውተር ስሌት የመረጃ ማዕከል) ቀዳሚ የሆነው አዙሬ ገልጿል።
እስራኤል በጋዛ በምታደርገው ጦርነት ባለው ግንኙነት የሚተቸው ማይክሮሶፍት በባህር ስር ያሉ ኬብሎች ላይ የደረሰው ጉዳት መንስኤ ምን እንደሆነ ባይገልጽም ነገር ግን የኢንተርኔቱን ፍሰት ወደሌሎች አቅጣጫ መቀየር መቻሉን ገልጿል።
በውቅያኖስ ወለል ላይ የተዘረጉት እነዚህ ኬብሎች በአህጉሮች መካከል መረጃን ለማስተላለፍ የሚያገለግሉ ሲሆን የኢንተርኔት (በይነ መረብ) የጀርባ አጥንት እንደሆኑ ይገለጻል።
ማይክሮሶፍት ቅዳሜ ዕለት በለጠፈው መረጃ መስረት በመካከለኛው ምስራቅ የሚያልፈው የአዙሬ መስመር "በቀይ ባህር ውስጥ የኢንተርኔት ፋይበር መቆራረጥ ምክንያት መዘግየት ሊያጋጥመው ይችላል" ብሏል።
አክሎም "በመካከለኛው ምስራቅ አቋርጦ የማያልፈው ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ አይኖረውም" ሲል አክሏል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢንተርኔት ተደራሽነትን የሚከታተለው ኔት ብሎክስ በቀይባህር ባሉ ኬብሎች መቆረጥ ምክንያት ህንድና ፓኪስታንን ጨምሮ በበርካታ አገራት ላይ የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥ ማጋጠሙን አስታውቋል።
የፓኪስታን ቴሌኮሙዩኒኬሸን ኩባንያ በበኩሉ በሳዑዲ አረቢያ መዲና ጂዳ በሚገኝ የባህር ስር ኬብል መቆረጥ ምክንያት የኢንተርኔት አገልግሎቶች መቆራረጥ ሊያጋጥም እንደሚችል አስጠንቅቋል።
የባህር ስር የኢንተርኔት ኬብሎች በመርከቦች በሚጣሉ መልህቆች ሊጎዱ የሚችሉ ቢሆንም ከዚህ ቀደም ሆን ተብለው ዒላማዎች ተደርገዋል።
በአውሮፓውያኑ 2004 በርካታ በቀይ ባህር የሚገኙ የኮሙዩኒኬሽን ኬብሎች ተቆርጠው በእስያ እና አውሮፓ የኢንተርኔት ፍሰቶች አስተጓጉሏል።
ድርጊቱ የተፈጸመው በአለም አቀፍ እውቅና ያለው የየመን መንግሥት በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማጺያን በቀይ ባህር ውስጥ በሚገኙ ኬብሎች ላይ እንዲሁም መርከቦች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ካስጠነቀቀ ከአንድ ወር በኋላ ነበር።
ሁቲዎች ኬብሎቹ ላይ ጉዳት አድርሰዋል መባላቸውን ውድቅ አድርገዋል።
ሩሲያ በዪክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ በባልቲክ ባህር የሚገኙ የባህር ስር ኬብሎች እንዲሁም የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።
የስዊድን ባለስልጣናት ከባልቲክ ባህር ወደ ላቲቪያ የተዘረጉ መስመሮች ላይ ሆን ተብሎ ጉዳት በመፈጸም የተጠረጠረ አንድ መርከብ በቁጥጥር ስር አውለዋል።
አቃብያነ ህግ እንዳሉት ይህ ሆን ተብሎ ስለመፈጸሙ ምርመራዎች ማሳየታቸውን አክለዋል።















