የውሃ አገልግሎት በተቋረጠባት የአሜሪካዋ ከተማ ነዋሪዎች የዝናብ ውሃ እየተጠቀሙ ነው

አሪዞና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካዋ ግዛት አሪዞና ስር በሚገኝ አንድ አከባቢ የውሃ አገልግሎት መቋረጡን ተከትሎ ነዋሪዎች ጥቅም ላይ የዋለ የሻወር ውሃ እና መጸዳጃ ቤቶች የሚለቀቅ ውሃን በዝናብ ውሃ ለመተካት መገደዳቸው ተሰምቷል። 

በአሜሪካዋ አሪዞና ግዛት ስር የምትገኘውና የስኮትዴል አጓራባች የሆነችው ሪዮ ቬርድ ከፈረንጆቹ ጥር 1 ጀምሮ የውሃ አቅርቦት ተቋርጦባታል።

ይህ አወዘጋቢ ውሳኔ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከውሃ አቅርቦት ውጪ ያደረገ ሲሆን ነዋሪዎች የውሃ አቅርቦትን መልሶ ለማግኘት ክስ ለመመስረት እየተዘጋጁ ነው ተብሏል።

አጓራባቿ ስኮትዴል በሪዮ ቬርድ ለተቋረጠው የውሃ አግልገሎት ኃላፊነት አልወስድም ብላለች።

ከቀናት በፊት የስኮትዴል ከተማ ባወጣው መግለጫ አሁን ውሃ የተቋረጠባት ሪዮ ቬርድ ከተማ ለዓመታት “ማስጠንቀቂያና ምክር” ስንሰጥ ነበር ብሏል።

ማሪኮፓ በተባለው ካውንቲ ስር ያለችው ሪዮ ቬርድ በከተማው የውሃ አቅርቦት ላይ በተለየም በድርቅ ጊዜ መመርኮዝ የለባትም ሲል ገልጿል።

መግለጫው አክሎም “ሕጉ ከተማውን የሚደግፍ እንደሆነ ሙሉ እምንት አለን” ብሏል።

ከስኮትዴል ከተማ በውሃ ቦቴዎች ለመጨረሻ ጊዜ የቀረበላቸው እና የውሃ አገልግሎት የተቋረጠባቸው ወደ 500 የሚጠጉ ቤቶች መፍትሄ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ነው ተብሏል።

አስተያየታቸው ለኒዎርክ ታይምስ የሰጡ ነዋሪዎች በመጸዳጃ ቤቶች ውሃ ለመልቀቅ የዝናብ ውሃ እንደሚጠቀሙና የመመገቢያ ዕቃ ለማጽዳት የሚውል ውሃን ለመቀነስ በወረቀት እየተመገቡ እንደሆነ ገልጸዋል። በተጨማሪም ልብሳቸውን ለማሳጠብ ወደ ጓደኞቻቸው እየላኩ እንደሆነም ገልጸዋል።

ለሌላ መገናኛ ብዙሃን አስተያየቱን የሰጠ ዲ ቶማስ ደግሞ ቤተሰቡ በመዋኛ ገንዳ የተጠራቀመ ውሃ ለመጠቀም መገደዱን ገልጿል።

“ቢያንስ ያንን በውሃ ጎማ ወስጄ ለገላ፣ ለልብስ ማጠቢያና ለመጸዳጃ ቤት መጠቅም ችለናል” ብሏል።

በሪዮ ቬርድ ናዋሪዎች ስም የተከፈተው የክስ ፋይል ስኮትዴል ከተማ የውሃ አግልግሎትን በማቋረጥ አጎራባቾቿን ነዋሪዎች ሊታሰብ በማይችል ጭንቅ ውስጥ ጥለዋል ይላል።

ክሱ ጨምሮም “የውሃ አቅርቦት ለንጽህና ወይም ለመጸዳጃ ቤቶች ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆ ገልጽ ነው” ይላል።

ክስ የቀረበበት ከተማ በበኩሉ “ሪዮ ቬርድ ናዋሪዎች ውሃን ከሌላ ቦታ ለመግዛት የሚከለክላቸው የለም” ብሏል።

መግለጫው ጨምሮው ከዚህ ቀደም ወደ አከባቢው ውሃ የሚሄደበት ማስተላለፊያ አሁንም አግልግሎት እየሰጠ ነው ሲል ገልጿል።

የአካባቢውን የውሃ ችግር ለመቅርፍ በርካታ አማራጮች የቀረቡ ሲሆን ከዚህ ቀደም ከአጎራባቿ ከተማ ውሃ በሚቀርብበት መስመር የግል ኩባንያ ውሃ ያቅርብ የሚለው አንዱ ነው።

በሌላ በኩል በቅርቡ የግዛቲቱ ሕግ አውጪዎች የወጣ ረቂቅ ለተፈጠረው የውሃ እጥረት ስኮትዴል ከተማ በገንዘብ ተጠያቂ የሚያደርገ ነው።

የአሜሪካ የድርቅ ቅኝት ተቋም ባወጣው መረጃ አሪዚና በአሜሪካ ከሚገኙ እና የድርቅ ሁኔታ ከሚታይባቸው 33 ግዛቶች አንዷናት።