ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዋይት ሃውስ ኮኬይን ተገኘ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ይፋዊ መኖሪያ እና የሥራ ቦታ በሆነው በዋይት ሃውስ ኮኬይን የተበላው አደገኛ አደንዛዥ ዕጽ ተገኘ።
ባሳለፍነው እሁድ ምንነቱ ያልታወቀ ነጭ ንጥረ ነገር ሲገኝ ሠራተኞች ከዋይት ሃውስ በአስቸኳይ እንዲወጡ ተደርጎ ነበር።
ባለሥልጣናት በነጩ ንጥረ ነገር ላይ ምርመራ እንዲደረግ ካዘዙ በኋላ ኮኬይን መሆኑ ተረጋግጧል።
ዕጹ የተገኘው ለሕዝብ ክፍት ባልሆነ የሥራ አካባቢ መሆኑን ለአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጥበቃ የሚያደርገው ሴክሬት ሰርቪስ አስታውቋል።
ኮኬይን የተባለው ዕጽ እሁድ ዕለት በዋይት ሃውስ ሲገኝ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ባለቤታቸው ካምፕ ዴቪድ ተብሎ በሚጠራው መኖሪያ ቦታ ነበሩ።
የሴክሬት ሰርቪስ ቃል አቀባይ አንተኒ ጉግሌልሚ እሁድ ዕለት ምንነቱ ያልታወቀ ነጭ ንጥረ ነገር በሥራ ቦታ ላይ መገኘቱን ተከትሎ ለቅድመ ጥንቃቄ ሲባል ዋይት ሃውስ ለሰዎች ዝግ እንዲሆን ተደርጎ እንደነበረ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ፣ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞ ከተጠሩ በኋላ ነጩ ንጥረ ነገር በሕንጻው ውስጥ በሚሠሩ ሰዎች ላይ ጉዳት የሚያስከትል አለመሆኑን አረጋግጠዋል ብለዋል።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ የአገሪቱን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ በመጥቀስ እንደዘገበው ኮኬይኑ የተገኘው የዋይት ሃውስ ሠራተኞች እና ጎብኚዎች ስልካቸውን ለማስቀመጥ በሚጠቀሙበት ስፍራ ነው።
ሲቢኤስ በዋይት ሃውስ ሕንጻ በምዕራብ አቅጣጫ ካለው ክፍል ውስጥ የተገኘው ነጩ ንጥረ ነገር ኮኬይን መሆኑ በምርመራ የተረጋገጠው በተመሳሳይ ዕለት መሆኑን ጨምሮ ዘግቧል።
ኮኬይኑ የተገኘበት የዋይት ሃውስ ሕንጻ አካል ‘ኦቫል ኦፊስ’ እና ‘ሲቹዌሽን ሩም’ ጨምሮ የፕሬዝዳንቱ ቢሮዎች ይገኙበታል።
ከዚህ በተጨማሪ የዋይት ሃውስ በምዕራብ አቅጣጫ የሚገኘው ሕንጻ የምክትል ፕሬዝዳንት ቢሮ፣ የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈር ቤት ኃላፊ፣ የፕሬስ ሴክሬታሪ ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች የሥራ ቦታ ነው።