በዛምቢያ የተበከለ በቆሎ የበሉ 400 ውሻዎች መሞታቸውን ተከትሎ ስጋት ተፈጠረ

በበርካታ ዛምቢያዊያን ዘንድ የሚዘወተረው ንሺማ የተባለው ምግብ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በዛምቢያ ባለፈው የተበከለ በቆሎ የበሉ 400 ውሻዎች መሞታቸውን ተከትሎ ሰዎችም አደጋ ላይ መሆናቸውን የሀገሪቱ የጤና ሚኒስትር አስታወቁ።

ሚኒስትሩ ኤላይጃህ ሙኪሚ እንዳስታወቁት ምርመራ ከተደረገባቸው የዱቄት ፋብሪካዎች ግማሽ ያክሉ ከመጠን በላይ የሆነ አፍላቶክሲን የተባለ በአልጌ የሚከሰት መርዛማ ኬሚካል አዝለዋል።

በቆሎ ዛምቢያ ውስጥ በስፋት ጠረጴዛ ላይ የሚቀርብ እህል ሲሆን የጤና ሚኒስትሩ እንዳሉት ከምርመራው የተገኘው ውጤት “በጣም ለጤና አሳሳቢ ነው።”

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ከሆነ አፍላቶክሲን የተባለው ኬሚካል በሰዎች ዘንድ የጉበት ነቀርሳ [ካንሰር] ሊያመጣ ይችላል።

ዳይመንድ ቲቪ የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ባሠራጨው የምርመራ ዘገባ ነው በኬሚካሉ ምክንያት በርካታ ውሻዎች መሞታቸውን ያስታወቀው።

ይህንን የምርመራ ዘገባ ተከትሎ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት የዱቄት ፋብሪካዎች ምርመራ እንዲደረግባቸው አዘዋል።

ውሻዎቹ በቆሎ ያለበት የውሻ ምግብ ከበሉ በኋላ ነው የሞቱን የሚሉ ዘገባዎች እየተሰራጩ ነው።

ባለሥልጣናት ባደረጉት ምርመራ ከበቆሎ የሚሠራ የውሻ ምግብ የሚያመርቱ 10 የዱቄት ፋብሪካዎች ላይ ምርመራ ያደረጉ ሲሆን ሰዎች የሚጠቀሙትን የበቆሎ ዱቄት ማምረቻም ተመልክተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የጤና ሚኒስቴሩ እስካሁን የተበከለ በቆሎ በመብላት ምክንያት የሞቱ ሰዎች እንደሌሉ አስታውቋል። ነገር ግን የዛምቢያ ብሔራዊ የፐበሊክ ሄልዝ ተቋም የተበከለው የበቆሎ ዱቄት ኅብረተሰቡ ላይ ጉዳት አድርሶ እንደሆን ለመለየት እየሞከረ መሆኑን አስታውቋል።

ባለሥልጣናቱ ያደረጉትን ምርመራ ተከትሎ “የተበከሉ ዱቄቶች” እንዲሰበሰቡ የተደረገ ሲሆን “ለፋብሪካዎች” ደግሞ ማስታወቂያ መላኩን የጤና ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ሚኒስትሩ የዱቄት ፋብሪካዎቹን ስም ከመናገር ተቆጥበዋል።

ዳይመንድ ቲቪ ዘገባውን ከማሰራጨቱ ቀደም ብሎ ፋርምፊድ የተባለው የውሻ ምግብ አምራች ኩባንያ ምርቶችን ከገበያ ሰብስቦ ነበር።

ማክሰኞ ዕለት መግለጫ የሰጡት ሙኪሚ የአየር ንብረት ለውጥ እና በዛምቢያ የተከሰተው ድርቅ “በያዝነው ዓመት የአፍላቶክሲን መጠን ከፍ እንዲል አስተዋፅዖ አድርገዋል” ብለዋል።

እንደ አብዛኛዎቹ የደቡብ አፍሪካ ሀገራት ዛምቢያ በያዝነው ዓመት በተከሰተ ድርቅ መመታቷ ይታወቃል። ከአንድ ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች በድርቁ ምክንያት የተጎዱ ሲሆን በሀገሪቱ የማሽላ አቅርቦት ከወትሮው በጣም ዝቅ ብሏል።

የዛምቢያ ሕዝብ በቀን ከሚወስደው ኃይል ሰጭ [ካሎሪ] መካከል 60 በመቶው ከማሽላ የሚገኝ ነው ይላል የአሜሪካ ግብርና ሚኒስቴር። ይህ አሀዝ ነው ምናልባት በቆሎው ተበክሎ ከሆነ ሰዎች ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል የሚል ስጋት የፈጠረው።

“መንግሥት 400 ውሻዎች በኬሚካል ተመርዘው መሞታቸውን ተናግሯል። እኔም በዚህ ምክንያት በአንድ ሳምንት ብቻ 6 ውሻዎች አጥቻለሁ” ሲሉ የዛምቢያ ሕዝብ እንደራሴ የሆኑት የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ሰንደይ ቻንዳ በኤክስ ገፃቸው ፅፈዋል።

“መንግሥት ምርመራ ከፍቻለሁ ቢልም አሁንም የተበከለው በቆሎ ገበያ ላይ ነው ያለው” ሲሉ አክለዋል።

የዛምቢያ ዱቄት ፋብሪካዎች ማኅበር ችግሩን ለመቅረፍ ከፋብሪካዎች ጋር እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።