በዩኬ ፖስት ካርድ ከተላከ ከ121 ዓመታት በኋላ ወደ አድራሻው ደረሰ

የፎቶው ባለመብት, Swansea Building Society
በዩናይትድ ኪንግደም የተላከ ፖስት ካርድ ከ121 ዓመታት በኋላ ወደ አድራሻው ደረሰ።
ለገና በዓል እንዲደርስ የታቀደው ፖስት ካርድ በአውሮፓውያኑ 1903 የተላከ ቢሆንም ወደ አድራሻው የደረሰው መቶ ዓመታትን ዘግይቶ ነው።
ፖስት ካርዱ ወደታቀደው ስዋንዚያ ቢዩልዲንግ ሶሳይቲ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ከሰሞኑ ደርሷል።
ፖስት ካርዱ የተላከላቸው ሊዲያ ዴቪስ ዘመዶችን አግኝተው ለመስጠትም ሰራተኞቹ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ፖስታ አገልግሎት ሮያል ሜይል እንዳለው ፖስት ካርዱ ከአንድ መቶ አመት በላይ ጠፍቶ ሳይሆን ምናልባትም ተቀምጦ ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል።
የፖስት ካርዱ ላኪ ኤዋርት ሲሆን ኤል በሚል ለጠራትም ሴት “በጣም አዝኛለሁ” ካለ በኋላ በስም ያልጠቀሳቸውን ዕቃዎች መውሰድ እንዳልቻለም አስፍሯል።
አክሎም “ቤትሽ ውስጥ ጥሩ ጊዜ እያሳለፍሽ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲል አክሏል።
ኤዋርት በመቀጠልም የባቡር ትራንስፖርቱን ሳይጨምር 10 ሺልንግ እንዳለው ጠቅሶ “ጥሩ ሁኔታ ላይ ነኝ” ብሏል።
ሊዲያን ጊልበርት እና ጆንን እንድታገኛቸው በማስታወስ ለሁላችሁም ፍቅር ሲል ነው ግለሰቡ መልዕክቱን ያጠናቀቀው።
የስዋንዚያ ቢዩልዲንግ ሶሳይቲ የግብይት እና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሄንሪ ዳርቢ ፓስታዎቹን እየለየ በነበረ ወቅት ድንገት ፖስት ካርዱ እንደተገኘ ተናግረዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይም የፖስታ ካርዱን ተቀባይ ዘመዶች ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ዌስት ግላሞርጋን አርካይቭስ በተሰኘ የታሪክ ማህደሮችን የሚሰብስብ ተቋም ውስጥ የሚሰሩት አንድሪው ዱሊ በበኩላቸው በተቀባይዋ አድራሻ ጆን ኤፍ ዴቪስ የሚባል አባወራ ይኖር እንደነበር ገልጸዋል።
ግለሰቡ ከባለቤቱ ማሪያ እና ስድስት ልጆችም ነበር በዚሁ ቤት ከ100 ዓመታት በፊት የኖረው።
“ትልቋ ልጃቸው ሊዲያ ትባል ነበር። ፖስት ካርዱ በተላከበት ወቅት 16 ዓመቷ ነበር “ ይላሉ።
የሮያል ሜይል ቃል አቀባይ በበኩላቸው ፖስታ ካርዱ ለመቶ ዓመታት ተቀምጦ ሊሆን እንደሚችል ገልጸው አሁንም ቢሆን “ወደ ትክክለኛው አድራሻ የማድረስ ግዴታ አለብን” ብለዋል።












