የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቀሳውስት በዩክሬን ጥቃት ለተቃጠለው የነዳጅ ማከማቻ ፀሎት አደረጉ

የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቀሳውስ በእሣት አደጋው ሥፍራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሩሲያ ኦርዶክስ ቤተክርስትያን ቀሳውስት በዩክሬን የድሮን ጥቃት ደርሶበት ላለፉት ሶስት ቀናት እሣቱ ያልጠፋውን የነዳጅ ማከማቻ ጎብኝተዋል።

በሮስቶቭ ግዛት የሚገኘው የፕሮሌታርስክ ነዳጅ ማከማቻ በድሮን ጥቃት ምክንያት የደረሰበትን ቃጠሎ ለማስቆም ከ500 በላይ የእሣት አደጋ ሠራተኞች እየተረባረቡ ይገኛሉ።

ከ74 የነዳጅ ማከማቻዎች 20 ገደማው እሣት መያዛቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት አርአይኤ ለተሰኘው የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ረቡዕ ዕለት የአካባቢው የኦርቶዶክስ ቀሳውስት በሥፍራው ተገኝተው እሣቱ እንዲቆም ፀሎት ያደረጉ ሲሆን ምስለ አድህኖ ይዘው የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችንም አበረታትዋል።

“ቀሳውስቱ ከእሣት አደጋ ሠራተኞች ጋር ተነጋግረዋል፤ የእሣት ማጥፊያ ቁሳቁሶችንም ባርከዋል” ሲሉ ከቀሳውስቱ መካከል አንዱ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

የእሣት ጠር ነው ተብሎ የሚታመን ትልቅ ምስለ አድህኖ ይዘው መጥተው እንደነበርም ተነግሯል።

የአካባቢው ሀገረ-ገዥ የሆኑት ቫሲሊ ጎሉቤቭ የአየር መከላከያ ኃይሎች የዩክሬንን ድሮን መትተው መጣላቸውን ተናግረው ነገር ግን ስብርባሪው ወድቆ ነው እሣት የቀሰቀሰው ብለዋል።

በሥፍራው የአደጋ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ቢሆንም የሩሲያ መንግሥት ቴሌቪዠን የከተማዋን አስተዳዳሪ ዋቢ አድርጎ እሣቱ ወደ መኖሪያ ቤቶች ስለማይስፋፋ ሰዎች “መደናገጥ የለባቸውም” ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሉቤቭ እንዳሉት 41 የእሣት አደጋ ጊዜ ሠራተኞች በነበልባሉ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና ተደርጎላቸዋል። አምስቱ ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ዩክሬን ስለጥቃቱ እስካሁን የሰጠችው አስተያየት የለም። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በምታደርገው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ሩሲያ ውስጥ ያሉ ቦታዎችን ዒላማ እያደረገች ነው።

ረቡዕ ዕለት የዩክሬን ኃይሎች በሩሲያዋ ኖቮሻክቲንስክ ከተማ የሚገኝ ኤስ-300 የተባለ የአየር መቃወሚያ መምታታቸው ተዘግቧል።

የዩክሬን ታጣቂ ኃይል በፌስቡክ ገፁ በለጠፈው መልዕክት የዩክሬን ባሕር ኃይል ከሌሎች ጋር በመተባበር ነው ይህንን ጥቃት የፈፀመው ብሏል።

“የዩክሬን ኃይል የሩሲያን የአየር መቃወሚያ እያዳከመው ይገኛል” ብሏል።

በተያያዘ ዜና ሩሲያ በዋና ከተማዋ ሞስኮው ላይ ሌሊቱን ጥቃት ሊያደርሱ የነበሩ 11 ድሮኖችን መትታ መጣሏን ተናግራለች።

የከተዋማ ከንቲባ ሰርጌ ሶብያኒን እንዳሉት ግጭቱ ከተጀመረ በኋላ በሩሲያዋ መዲና ላይ የተቃጣ ከፍተኛ ጥቃት ሲሆን በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት ግን የለም።

በተመሳሳይ የዩክሬን መከላከያ ኃይል ከሩሲያ የተቃጡ 50 የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃቶችን መመከታቸውን ተናግረዋል። በስብርባሪው ምክንያት አንድ መኖሪያ ቤት መጎዳቱን እና የኤሌክትሪክ ገመዶች መበጣጠሳቸውንም ጨምረዋል ገልፀዋል።

ምድር ላይ በሚደረገው ፍልሚያ ዩክሬን በደቡብ ሩሲያ ከርስክ ግዛት የምታደርገውን ግስጋሴ ቀጥላለች። ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በኋላ የውጭ ኃይል ወደ ሩሲያ ድንበር ዘልቆ ሲገባ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የሩሲያ ኃይሎች በበኩላቸው በምስራቅ ዩክሬኗ ዶኔስክ ግዛት የሚያደርጉትን ግስጋሴ ቀጥለው ወደ ፖክሮቭስክ ከተማ መቃረባቸው ተዘግቧል። የዩክሬን ባለሥልጣናት እንደሚሉት የሩሲያ ኃይል ከከተማዋ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው።