ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አልሻባብ በሞቃዲሾ ሆቴል ላይ በፈጸመው ጥቃት ቢያንስ አስራ ሁለት ሰዎች ተገደሉ
የአልሻባብ ታጣቂዎች በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሆቴልን ጥሰው በመግባት በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ አስራ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ፖሊስ እንዳለው ጥቃት ፈጻሚዎቹ ሃያት ከተባለው ሆቴል ውጪ ሁለት ፈንጂዎችን ካፈነዱ በኋላ ወደ ሆቴሉ ሕንጻ በመግባት ተኩስ ከፍተው ነው ሰዎችን የገደሉት።
ታጣቂዎቹ ወደ ሆቴሉ ከገቡ ከሰዓታት በኋላ በሕንጻው የመጨረሻ ፎቅ ላይ መሽገው መቆየታቸው ተዘግቧል።
ጥቃቱን ተከትሎ ወደ ሆቴሉ የተሰማራው የሶማሊያ ልዩ የፖሊስ ኃይል ወደ ሆቴሉ በመግባት በርካታ የሆቴሉ እንግዶች እና ሠራተኞችን ከታጣቂዎቹ ማትረፍ ችሏል።
“በሆቴሉ ውስጥ የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች እንዲወጡ ሲደረግ፣ አብዛኞቹ ሰላማዊ ሰዎች የሆኑ አስራ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል” ሲሉ ሞሐመድ አብዲካዲር የተባሉ የደኅንነት ባለሥልጣን መናገራቸው ተዘግቧል።
ቀደም ሲል ከአልሻባብ ጋር ቅርበት ያለው ድረ ገጽ የቡድኑ ታጣቂዎቹ ወደ ሆቴሉ “በኃይል ጥሰው” መግባታቸውን እና “ተኩስ መክፈታቸውን” ጽፎ ነበር።
ጥቃቱ የተፈጸመበት የሞቃዲሾው ሃያት ሆቴል የአገሪቱ ፌደራል መንግሥት ሠራተኞች የሚገናኙበት ታዋቂ ቦታ እንደሆነ ይነገራል።
በሞቃዲሾ ውስጥ የአምቡላንስ አገልግሎት የሚሰጠው ተቋም ኃላፊ የሆነው አብዲካዲር አብዲራህማን ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገረው፣ በጥቃቱ የቆሰሉ ዘጠኝ ሰዎችን መውሰዳቸውን ገልጿል።
ፍንዳታ እና የሰዎች ጩኽት የሚሰማበት እንዲሁም ከሆቴሉ ጭስ ሲወጣ የሚያሳዩ ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጡ ምስሎት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲዘዋወሩ ታይተዋል።
“ሁለት በመኪና ላይ የተጠመዱ ቦምቦች ሆቴሉን ኢላማ አድርገው ፈንድተዋል” ሲሉ አንድ የፖሊስ መኮንን ለሮይተርስ በሰጡት ቃል ገልጸዋል።
“አንደኛው ከሆቴሉ በር ፊት ያለውን ማገጃ የመታ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የሆቴሉን የውጪ በር መትቷል። አሁን ታጣቂዎቹ በሆቴሉ ውስጥ እንዳሉ እናምናለን።”
ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለው አል ሻባብ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ለዓመታት የዘለቀ ጦርነት ውስጥ የሚገኝ ታጣቂ እስላማዊ ቡድን ነው።
የአልሻባብ ቡድን አብዛኛውን የደቡብ እና ማዕከላዊ የሶማሊያ ክፍልን በቁጥጥሩ ስር ያስገባ ሲሆን፣ ተጽዕኖውን መቀመጫውን ሞቃዲሾ ውስጥ የሚገኘው የአገሪቱ ፌደራል መንግሥት በመቆጣጠራቸው ስፍራዎች ጭምር ማስፋት ችሏል።
በቅርቡ ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንባቸው የድንበር አካባቢዎች ጥቃት ሰንሰረው ነበር። ይህም አልሻባብ አዲስ አይነት የጥቃት አቅጣጫን እየተከተለ ይሆን የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
አልሻባብ ትናንት አርብ በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ውስጥ የፈጸመው ጥቃት ባለፈው ግንቦት ወር የተመረጡት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።