ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በትግራይ ኃይሎች እና በ'ነጻ መሬት' ታጣቂዎች መካከል የተፈጠረው ምንድን ነው?
በትግራይ ክልል ወጀራት በተባለው ወረዳ በትግራይ ኃይሎች እና በሌሎች ታጣቂዎች መካከል ግጭት መፈጠሩን ቢቢሲ አረጋገጠ።
ግጭቱ የተከሰተው በትግራይ ክልል ደቡባዊ ምሥራቅ ዞን ሰንዓለ የዞኑ አካባቢ በሁለቱ የታጠቁ ኃይሎች መካከል ማክሰኞ ሰኔ 24/2017 ዓ.ም. አመሻሽ ከ10 አስከ 11 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ግጭቱ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ስጋት እና ፍራቻ የፈጠረ ሲሆን፣ የአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች በሁለቱ ታጣቂዎች መካከል ገብተው ለማሸማገል መሞከራቸውን የቢቢሲ ምንጮች ገልጸዋል።
ከትግራይ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ የገቡት ታጣቂዎች እስካሁን ድረስ ይፋዊ ስም ባይኖራቸውም በተለምዶ 'የነጻ መሬት ተዋጊዎች' በመባል ይታወቃሉ።
በሁለቱ ታጣቂ ኃይሎች መካከል የተፈጠረውን ፍጥጫ እና ተኩስ በተመለከተ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አስካሁን ያለው ነገር የለም።
ፍጥጫው እንዴት ጀመረ?
ይህ ማክሰኞ ዕለት ያጋጠመውን ግጭት ታጣቂዎቹ ከትግራይ ክልል ጋር ከሚዋሰነው ከአፋር ክልል ወደ ወጀራት ወረዳ እንደገቡ ከሰዓት በኋላ መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ቢቢሲ ከአካባቢው ነዋሪዎች እንዳረጋገጠው ከእሁድ ምሽት አንስቶ አስከ ሰኞ ድረስ . . . ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው 'የነጻ መሬት' ታጣቂዎች ወደ ሰንዓለ አካባቢ ገብተዋል።
ታጣቂዎቹ ወደ አከባቢው መግባታቸውን ተከትሎ የተቆጡት የትግራይ ኃይሎች በአካባቢው ተኩስ እንደከፍቱባቸው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በሰንዓለ ነዋሪ እና የአገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ግደይ አለመን ሐጎስ "ተፋላሚዎቹ ሁሉም የትግራይ ተወላጆች ናቸው። እነኚ የነጻ መሬት ታጣቂዎች እሁድ ምሽት ከመጋሌ [ከአፋር ክልል] ተጕዞው ሰኞ ከጥዋቱ 12:00 ሰዓት ሰንዓለ ታይተዋል" ብለዋል።
ነገር ግን በአካባቢው ያሉት የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎቹን 'ለምን መጡ?' በማለት መፋጠጣቸውን እና ሁለቱም ቦታ ይዘው "ለመፋለም ሞክረው ነበር" በማለት የአገር ሽማግሌው አስረድተዋል።
ይህንም ተከትሎ በሰንዓለ ለረጅም ጊዜ እንደቆዩ የሚነገርላቸው የትግራይ ኃይል አባላት በታታቂዎቹ ላይ ከሦስት እስከ አራት ጊዜ ዲሽቃ [ከባድ መትረየስ] ተኩሰዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንዳሉት ከማክሰኞ 10 ሰዓት ጀምሮ የትግራይ ኃይሎች ቀድመው ታጣቂዎቹ ላይ ተኩስ ከፍተው የጥይት ድምጽ መሰማቱን ተናግረዋል።
'የነጻ መሬት' ታጣቂዎች በድንገት ወደ አካባቢው ከገቡ በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጨማሪ የትግራይ ኃይል አባላት ወደ አካባቢው መሰማራታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ሁኔታው በሕዝቡ ላይ ስጋት መፍጠሩን የገለፁት ነዋሪዎቹ ጉዳዩን ለማረጋጋት የአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች ጥረት አድርገዋል።
ሻለቃ ገብረ አብርሃ ግጭቱን ለማረጋጋት ሁለቱን የታጠቁ ኃይሎች እስከ ምሽቱ 1፡30 ድረስ ሲያነጋግሩ ከነበሩት የአገር ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ናቸው።
"ከባድ ግጭት ነው ተፈጠረው። የትግራይ ኃይሎች እና የነጻ መሬቱ ታጣቂዎች ክፍለ ጦር አሰልፈው እንዋጋለን አሉ. . . እነዚህ የትግራይ ኃይሎች መተኮስ ጀመሩ. . . በነጻ መሬት ታጣቂዎች ላይ ተኰሱ።"
ይህንንም ተከትሎ የአገር ሽማግሌዎች "ይተላለቃሉ እንርዳቸው ተባባልን . . . ወታደር ታጣቂዎቹ እንዳይጨራረሱ መሀል ገብተን ገላገልናቸው። እናንተ ወንድማማቾች ናችሁ፤ ስለዚህ ቃላችንን ኣክብሩ ብለን የነፃ መሬት ታጣቂዎች ተማጸንናቸው፤ እነሱም ሰሙን፡ ምላሽ [ለተኩሱ] አልሰጡም" በማለት አስረድተዋል።
ሌላኛው የአገር ሽማግሌ አቶ ግደይ በበኩላቸው የነጻ መሬት ታጣቂዎች የአገር ሽማግሌዎችን ጠያቄ ተከትሎ ሰንዓሌን ለቀው ቢወጡም አሁን የት እንዳሉ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ለቢቢሲ ተናግሯል።
በሁለቱ ኃይሎች መካከል በተፈጠረው ፍጥቻ እና በተከሰተው ተኩሱ የተገደለ ወይም የተጎዳ ሰው እንደሌለ ቢቢሲ ከነዋሪዎች ለማወቅ ተችሏል።
የአገር ሽማግሌው ሻምበል ገብረ አክለውም "ሰንዓለ የገቡ የነጻ መሬት ታጣቂዎች በጣም ብዙ ነበሩ፤ ሁሉም የታጠቁ ነበር፡" በማለት ሰኞ ጠዋት ሰንዓለ አከባቢ የደረሱትን ታጣቂዎችን ብዛት ያስረዳሉ።
'የነጻ መሬት' ታጣቂ ኃይሎች አዛዥ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆኑት ሌ/ጄነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ (ወዲ አንጥሩ) ባለፈው ወር ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ልዩ ቃለ ምልልስ ኃይላቸው የተደራጀ መሆኑን ተናግረዋል።
ቡድኑ በአራት ክፍለ ጦሮች መደራጀቱን እና ዋና ዓላማቸውም በወታደራዊ ኃይል መፈንቅለ መንግሥት ፈጽሟል ያለውን ህወሓት ከሥልጣን መጣል እና በየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት የማይመራ ገለልተኛ ወታደራዊ ኃይል መገንባት መሆኑን ተናግረው ነበር።
"ድርድር እያሉ ኃይላቸውን እያጠናከሩ ነው"
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የነጻ መሬት ታጣቂ ኃይል አንድ የግንባር አመራር በወጀራት ወረዳ የተከሰተውን ግጭት አረጋግጠው፤ ከአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች ጋር በመግባባት ከሰንዓለ ቢወጡም አሁንም ወጀራት ወረዳን ጨምሮ ታጣቂዎቻቸው በብዙ የትግራይ አካባቢዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ተቀናቃኙ ኃይል "በውስጥ እንወያይ እያሉ ነው። ነገር ግን ይህ ለመዘጋጀት ጊዜ መግዣ ስልት ነው፣ ወደ ትግራይ ይገባሉ ብለው አልጠበቁም ነበር፤ አሁን እንደገባን ግን መንጫጫት ጀመሩ፣ እንደራደር እያሉን ነው።
"እስካሁን ግን እንደራደር እያሉ ሠራዊት እያስገቡ ነው፤ እኛ አንደራደርም አንልም፤ ነገር ግን ሥራችንን እየሠራን ነው የምንደራደረው። ምክንያቱም በታሪካቸው እንደራደራለን ብለው ስብሰባ ጠርተው ታጋዮች ገድለው ነው ያደሩት" ብሏል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ማክሰኞ በሁለቱ ታጣቂዎች መካከል ስላጋጠመው ግጭት እስካሁን ያለው ነገር የለም።
ይህን አዲስ ቀጥተኛ ግጭት ተከትሎ በትግራይ ሌላ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ሊከሰት ይችላል በሚል ብዙዎች እያሳሰበ ነው።
የትጥቅ ፍጥጫው ትግራይን ለ50 ዓመታት ሲመራ በነበረው ህወሓት ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል ወደ ትግራይ ኃይሎች ውስጥ በመግባቱ ነው ወደ ውጥረት የተፈጠረው።
አንዳንድ የትግራይ ኃይሎች አዛዦች ባለፈው ጥር ወር በአቶ ጌታቸው ይመራ የነበረውን ጊዜያዊ አስተዳደር በመቃወም በደብረፂዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ለሚመራው የህወሓት ቡድን አጋርነታቸውን በይፋ መግለጻቸው ይታወቃል።
ውሳኔው በትግራይ መሪዎች መካከል ያለውን የፖለቲካ ልዩነት ወደ ፖለቲካዊ አመራሩ በማውጣት ውጥረቱ እንዲባባስ አድርጓል።
ውሳኔውን የተቃወሙ አንዳንድ የትግራይ ኃይሎች ጄነራሎች ስብሰባውን ረግጠው በመውጣት የራሳቸውን ጦር በማደራጀት በአፋር እና በትግራይ 'ነጻ መሬት' እየተባለ በሚጠራው ቦታ የትጥቅ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።