መቀለን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ዝርፊያ እየተፈጸመ ነው ሲል መንግሥት ገለጸ

መቀለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የተደራጁ የዘረፋ ድርጊቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ገለጸ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ቅዳሜ ታኅሣሥ 08/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ባልደረሰባቸው የትግራይ አካባቢዎች ዘረፋዎች እየተፈጸሙ መሆናቸውን አመልክቷል።

ከአንድ ወር በፊት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ያንንም ተከትሎ ኬንያ ናይሮቢ ውስጥ ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ከስምምነት ተደርሶ ጦርነት መቆሙ ይታወሳል።

መንግሥት በመግለጫው ለሕዝብ እና ለአገር በሰላም ስምምነቱ የገባውን ቃል በመፈጸም ላይ መሆኑን አመልክቶ፣ “ይህን የሽግግር ወቅት እንደ አጋጣሚ በመጠቀም” በመቀለ እና በሌሎችም አካባቢዎች ዝርፊያ እየተፈጸመ ነው ብሏል።

“በአንዳንድ የመከላከያ ኃይላችን ባልደረሰባቸው የትግራይ አካባቢዎች የሕብረተሰቡን ሰላም የሚነሱ የተደራጁ ዘረፋዎች እየተካሄዱ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።”

ጨምሮም በተለይ በክልሉ ዋና ከተማ በመቀለ ውስጥ በመንግሥት እና በንግድ ተቋማት ላይ በተሽከርካሪ የታገዘ ከፍተኛ ዝርፊያ መኖሩን “መረጃዎች እየጠቆሙ ነው። ሕዝቡም በከፍተኛ ምሬት ላይ መሆኑን በስልክ እና በሌሎችም መንገዶች እያሳወቀ ይገኛል” በማለት ገልጿል።

ጦርነቱም ለማስቆም በተደረሰው ስምምነት የፈደራል መንግሥቱ ሠራዊት ወደ መቀለ በመግባት ዋና ዋና ተቋማትን እንደሚቆጣጠር የተገለጸ ቢሆንም እስካሁን ወደ ከተማዋ አልገባም።

መንግሥት ባወጣው መግለጫ እየተፈጸመ ነው በተባለው የዘረፋ ድርጊት ላይ የተሳተፉ በሙሉ ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ አስጠንቅቆ፣ መንግሥት “የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ ያለበትን ኃላፊነት ለመፈጸም አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል” ብሏል።

በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ውስጥ ዘረፋ እየተፈጸመ ነው በማለት መንግሥት ያወጣውን መግለጫ በተመለከተ ዋና ከተማዋን ጨምሮ ሌሎችንም አካባቢዎች የሚቆጣጠሩት የህወሓት ባለሥልጣናት ያሉት ነገር የለም።

በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ተካሂዶ ከባድ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳትን ያስከተለውን ጦርነት ለማስቆም በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የተደረሰው ስምምነት አፈጻጸም እስካሁን ስላለበት ደረጃ በይፋ የተሰጠ መረጃ የለም።

በስምምነቱ ዘላቂ ግጭት ማቆም፣ የሰብአዊ እርዳታ ያለመሰናክል እንዲቀርብ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ፣ የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ እና ከፌደራሉ ሠራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች ከክልሉ እንዲወጡ ስምምነት መደረሱ ይታወሳል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የሰላም ስምምነቱን አፈጻጸም በተመለከተ በሁለቱም ወገኖች ወታደራዊ አመራሮች መካከል ሽረ ውስጥ ውይይት መደረጉ እና የትግራይ ኃይሎች ከውጊያ ግንባሮች እየወጡ መሆናቸው ተዘግቧል።

የስምምነቱ መፈረምን ተከትሎ በፌደራም መንግሥቱ ጦር እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ሲደረግ የነበረው ጦርነቱ የቆመ ሲሆን፣ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትም በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ክልሉ እየገባ መሆኑን መንግሥትና የረድኤት ድርጅቶች አሳውቀዋል።