የፊፋው ፕሬዝዳንት ኢንፋንቲኖ የአፍሪካ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ ያሳዩትን ብቃት አወደሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ለግማሽ ፍጻሜ መድረሱ የአፍሪካ እግር ኳስ ብሩህ ተስፋ እንዳለው የሚያሳይ መሆኑን እንደሚያምኑ የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ተናገሩ።
ከዚህ ቀደም በተካሄዱት የዓለም ዋንጫዎች አብዛኞቹ የአፍሪካ ቡድኖች በውድድሩ ላይ እምብዛም የጎላ ፉክክር ሳያደርጉ ከዙር ጨዋታዎች ባሻገር ለማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። ወደ ጥሎ ማለፍ ዙር ያለፉትም ቢሆኑ ከሁለት የበለጡ አይደሉም።
ነገር ግን በኳታሩ የዓለም ዋንጫ አምስት የአፍሪካ ተወካይ አገራት በምድብ ጨዋታቸው ላይ አሸንፈዋል። ኋላ ላይም ሞሮኮ በጥሎ ማለፍ ውድድሮች ላይ የበላይነትን በማግኘት ታላላቅ ቡድኖችን ለማሸነፍ በቅታለች።
“ለበርካታ ዘመናት የአፍሪካ እግር ኳስ ስለሚያድግበት ሁኔታ እና ወደ ፊት ስለሚመጣበት ወቅት ስንነጋገር ቆይተናል፣ አሁን ግን ጊዜው ነው፣ በዚህም ደስ ብሎኛል” ብለዋል ኢንፋንቲኖ።
የ52 ዓመቱ የፉፋ ፕሬዝዳንት ለዚህ በምሳሌነት ያነሷት ዛሬ ለሦስተኛነት ከክሮሺያ ጋር የምትገጥመውንና እዚህ ደረጃ ላይ በመድረስ ከአፍሪካ ቡድኖች የመጀመሪያ የሆነችውን ሞሮኮን ነው።
“ሞሮኮ በተለየ ሁኔታ በውድድሩ ላይ ጥሩ ጨዋታ አሳይታለች፣ በጣም በጣም ጥሩ ሰርተው ታላቅ ስኬትን አስመዝግበዋል” በማለት ተጫዋቾቹ በታላቅ ፍላጎት፣ በቆራጥነትና በብቃት መጫወታቸውን መስክረዋል።
“ለፍጻሜ መድረስ በዕድል የሚገኝ ውጤት አይደለም። ይህም በሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የቴክኒክ ቡድን እና በአገሪቱ ቡድኖች ውስጥ ባሉ አሰልጣኞች የረጅም ጊዜ ጥረት ቡድኖች የተገኘ ውጤት ነው።”
“ማራኪ እና ውጤታማ እግር ኳስን እንዴት መጫወት እንደሚቻል አሳይተውናል” ሲሉ ኢንፋነቲኖ የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድንን አወድሰዋል።
ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በተለየ የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተጫዎቾች እና በስፖርቱ መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር አውጥቷል። የዚህ ልፋት ውጤትም በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ታይቷል።
በዚህ ውድድር ሌሎቹ የአፍሪካ ቡድኖች የማይናቅ ጨዋታ አድርገው ለማሸነፍም በቅተዋል። በዚህም ቱኒዚያ ለዋንጫ የደረሰችውን ፈረንሳይን፣ ካሜሩን ደግሞ የዓለም ዋንጫ አምስት ጊዜ አሸናፊዋን ብራዚልን በዙር ጨዋታ ለማሸነፍ ችለዋል፥
የዓለም እግር ኳስ የበላይ አካል ፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖም በዚህ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ውድድር የተሳታፉትን የአፍሪካ ተወካዮች የሆኑትን ሴኔጋልን፣ ካሜሩንን፣ ጋናን እና ቱኒዚያን በስም ጠቅሰው ላሳዩት ግሩም ጨዋታ እና ፉክክር ሳያደርንቁ አላለፉም።
በፈረንሳይ እና በአርጀንቲና መካከል ከሚካሄደው የዓለም ዋንጫው የፍጻሜ ጨዋታ ቀደም ብለው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ኢንፋንቲኖ፣ የአፍሪካ ቡድኖች ያሳዩት መሻሻል የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ አገራት ቁጥር ከፍ እንዲል በታቀደበት ጊዜ መሆኑ ትክክለኛ ወቅት ነው ብለዋል።
በዚህም ከአራት ዓመት በኋላ በአሜሪካ፣ በካናዳ እና በሜክሲኮ በጥምረት በሚስተናገደው የዓለም ዋንጫ አፍሪካ ቢያንስ በዘጠኝ ቡድኖች የመወከል ዕድል ይኖራታል።
ፊፋ በውድድሩ የሚሳተፉ አገራት ብዛትን ወደ 48 በማድረስ በኳታር ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ የነበረው ቢሆንም፣ ትንሿ ጠባሕረ ሰላጤው አገር ይህንን ትልቅ ውድድር ለማስተናገድ እንደማትችል እንዲሁም ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ ማስተናገዱም አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ ወደ ቀጣዩ ጊዜ እንዲዘዋወር ተወስኗል።












