የዓለም ዋንጫ ለሜሲ ወይስ ለምባፔ? የእርስዎ ግምት ወዴት ያደላል?

የፎቶው ባለመብት, BBC/GETTY
ቦታ፡ የባሕረ ሰላጤዋ ሃገር ካታር
ቀንና ሰዓት፡ እሑድ ታኅሣሥ 09/2015 ዓ.ም.
ተጋጣሚዎች፡ የሜሲ አርጀንቲና ከኪሊያን ምባፔ ፈረንሳይ
ከ1400 ቀናት በላይ አስጠብቆን የመጣው የዓለም ዋንጫ እነሆ ነገ ሰንበት ፍፃሜውን ያገኛል፤ አርጀንቲና እና ፈረንሳይም ታሪክ ለመፃፍ ቋምጠዋል።
ቀጣዩ የዓለም ዋንጫ 1270 ቀናት ይቀሩታል። አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ያስተናግዱታል።
የዘንድሮውን የኳታር የዓለም ዋንጫን የኮመኮሙ “ይህን የመሰለ የዓለም ዋንጫ ተመልክተንም አናውቅ” እያሉ ነው።
“ኳታር የዓለም ዋንጫን ታዘጋጃለች” ተብሎ ሲታወጅ የአገሪቱን ዜጎችን ጨምሮ የዓለም ሕዝብ ያልጠበቁት ስለነበረ መደነቅና ድንጋጤ ተፈጥሮ ነበር።
በርካቶች የዓለም ዋንጫ ወደ በረሃማዋ ዶሃ ማቅናቱ ተገቢ አይደለም ሲሉ አጉረመረሙ፣ ኳታር ለሰብዓዊ መብቶች ግድ የላትም ሲሉ ከሰሱ፣ ጨዋታው በወርሃ ታኅሣሥ ሊሆን አይገባም ሲሉም ተቃውሟቸውን አሰሙ።
የጠላት ወሬ አልሰማም ያለችው ዶሃ የደመቀ የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት ለአስር ዓመታት ደፋ ቀና ማለቷን ቀጠለች።
ቀኑ ደርሶ የዓለም ሕዝብ ወደ ዶሃ ተመመ። የሚሊዮኖች ዐይን የቴሌቪዥን መስኮት ላይ ተተከለ።
የኳታር የዓለም ዋንጫ ብዙዎችን አጀብ ያሰኙ ክስተቶች የተስተዋሉበት ነበር። የመጀመሪያዋ የዚህ ክስተት ተጠቂ ደግሞ የዋንጫ ተፋላሚዋ አርጀንቲና።
አርጀንቲና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ልትጫወት ቀጠሮ ያዘች። ሳዑዲዎች ቡድናቸውን ሊደግፉ ድንበር አቋርጠው ወደ ዶሃ ፈለሱ። ጉዟቸው መና አልቀረም።
በርካቶች “እንዲህ ዓይነት እግር ኳሰኛ ዓይተንም አናውቅ” የሚሉለት ባለ ግራ እግሩ ተዓምረኛ ሜሲ የመጀመሪያዋን ጎል በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጠረ።
የሳዑዲዎች ቀፎ ተነካ። እንደ ንብ ተመው የመጀመሪያዋን ጎል አስቆጠሩ። ደጋፊው አበደ። ሁለተኛ ደገሙ። ምድር ተናጋች።
የአርጀንቲና ሽንፈት አስደንቆን ሳያበቃ ጃፓን ጀርመንን አርበድብዳ ጉድ አሰኘች። ደቡብ ኮሪያ ደግሞ ስፔንን አንገት አስደፍታ እንካችሁ ተዓምራት አለች።
እግር ኳስ ሁሉን አስረሳ። የኳታር ነቃፊዎች አፍ ተዘጋ። ሁሉም ትኩረቱን ወደ ሃያ ሁለቱ ተጫዋቾች እና ወደ ወደ ኳሷ አዞረ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሞሮኮ - የውድድሩ ክስተት
የኳታር የዓለም ዋንጫ ክስተት፤ የአህጉረ አፍሪካ ኩራት፤ የአረቡ ዓለም ትሩፋት፤ ሞሮኮ።
ሞሮኮ፤ ስፔንን ከርክማ፣ ፖርቹጋልን አጋድማ፣ ለግማሽ ፍፃሜ በቅታ ፈረንሳይን ነብስ ውጭ ነብስ ግቢ ታሰኛታለች ብሎ የገመተ ካለ እጅ ያውጣ - ከሳሙዔል ኤቶ በቀር።
ካለፈው የዓለም ዋንጫ ሁለተኛ ክሮሺያ እና ከወቅቱ የዓለም እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኖች ቁንጮ ቤልጂዬም ጋር የተመደበችው ሞሮኮ ኃያላኑን ገነዳድሳ ነው ለዚህ የበቃችው።
አሠልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉዊ ሞሮኮን ከተረከቡ መንፈቅ እንኳ ባይደፍኑም የተከላካይ መስመሩ የሚያስፈራ ቡድን መሥራት ችለዋል።
ሞሮኮ በመጀመሪያ ጨዋታዋ ከክሮሺያ አቻ፤ በሁለተኛው ቤልጂየምን 2 ለምንም ረመረመች። በሦስተኛው ካናዳን 2 ለ 1 ረታች።
በዙር 16 ስፔንን በፍፁም ቅጣት አሰናብታ ከክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር ቀጠሮ ያዘች።
በርካቶች ሞሮኮ ሩጫሽ መልካም ነበር፤ ነገር ግን የሮናልዶን ቡድንማ አትረችም ብለው ቢያሟርቱም የአትላስ አናብስቱ ፖርቹጋልን አሸንፈው ወደ ግማሽ ፍፃሜው በማለፍ ከአፍሪካ እና ከአረቡ ዓለም ቡድኖች የመጀመሪያው ሆኑ።
በሺዎች የሚቆጠሩ የሞሮኮ ደጋፊዎች ለቡድናቸው ከለላ ለመሆን ወደ ዶሃ በረሩ።
አህጉረ አፍሪካ ተቁነጠነጠ፤ የአረቡ ዓለም የሚይዝ የሚጨብጠውን ሳያውቅ በጉጉት የጨዋታዋን ሰዓት ጠበቀ።
ቢሆንም ሞሮኮ ለፍፃሜው ለማለፍ የነበራት ሕልም በኪሊያን ምባፔ ቡድን ከሰመ።
በተጋጣሚ ቡድን ጎል ከተቆጠረባት ዘመናት ያየችው ሞሮኮ [ከካናዳ ጋር በነበረው ጨዋታ የተቆጠረው በራስ መረብ ላይ ነው] በፈረንሳይ 2 ለምንም ተረታች።
እነሆ አንድ ምድብ ውስጥ ተደልድለው የነበሩት ሞሮኮ እና ክሮሺያ ዛሬ ቅዳሜ አመሻሹን የሦስተኛነት ክብር ለማግኘት ይፋለማሉ።
ሁለቱ “አሳዛኝ ተሸናፊዎች” የብዙዎችን ግምት አክሽፈው ለዚህ በመብቃታቸው “ኩራት ሊሳማቸው ይገባል” የሚሉ ብዙዎች ናቸው።

የመጨረሻው ፍልሚያ
በበርካታ መገናኛ ብዙኃን የእሑዱን ፍልሚያ ሊዮኔል ሜሲ ከከሊያን ምባፔ የሚል የዳቦ ስም ሰጥተውታል።
ለፈረንሳዩ ፒኤስጂ የሚጫወቱት ሁለቱ የአንድ ክለብ አጋሮች በዓለም ዋንጫው ባላንጣ ሆነው ተገናኝተዋል።
የ23 ዓመቱ ፈረንሳዊ የእግር ኳስ ኮከብ ሁለተኛ የዓለም ዋንጫውን ሊያነሳ ተሰናድቷል። በ12 ዓመት የሚበልጠው የኳስ ፈርጥ ደግሞ ለመጀመሪያ እና ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫውን ለመጨበጥ ጓጉቷል።
የዓለም ዋንጫን ለመጨረሻ ጊዜ በተከታታይ ያነሳችው ብራዚል ናት። ጊዜው ደግሞ በፈረንጆቹ 1958 እና 62።
ፈረንሳይ በ2018 ክሮሺያን 4 ለ 2 በመርታት ዋንጫ ስታነሳ ጎል ካስቆጠሩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ኪሊያን ምባፔ ነው።
የወንዶች ዓለም ዋንጫን ሦስት ጊዜ ያነሳው ብቸኛው የዓለማችን ተጫዋች ብራዚላዊው ፔሌ ነው።
ፔሌን ጨምሮ 21 ወንድ ተጫዋቾች ብቻ ናቸው የዓለም ዋንጫን ከአንድ ጊዜ በላይ የማንሳት ዕድል ያገኙት።
ኪሊያን ምባፔ ገና በለጋ ዕድሜው ይህን ታሪክ ይቋደስ ይሆን?
ወደ ሊዮኔል እንምጣ።
ሜሲ ጫማ ወደ መስቀያ ዕድሜው እየተቃረበ ነው። በእግር ኳስ ዓለም ያሉ ዋንጫዎችን ሁሉ አጋብሷል - ከዓለም ዋንጫ በቀር።
ሜሲ በፈረንጆቹ 2014 ለፍፃሜ ደርሶ ዋንጫውን አጨብጭቦ ለጀርመን አስረክቦ መመለሱ ይታወሳል።
ሊዮኔል ሜሲ የእሑዱ ግጥሚያ የመጨረሻው የዓለም ዋንጫ ጨዋታው እንደሆነ ተናግሯል።
አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ጠቢብ እሑድ ምሽት የዓለም ዋንጫን ካነሳ በእግር ኳስ ደጋፊዎች ዘንድ የምንም ጊዜ ምርጡ የተሰኘውን የክብር ስም ይቆናጠጣል።
ለዚህ ነው የእሑዱ የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ አጓጊነቱ፤ ልብ አንጠልጣይነቱ ከፍ ያለው።
የኳታር የዓለም ዋንጫ አንድ ነገር አስተምሮናል። ማንም ከማንም ይጫወት ዘንድሮ እከሌ ይረታል ብሎ መገመት ከባድ ነው። ቢሆንም እርስዎ ከመገመት ወደኋላ እንዳይሉ እናበረታታለን።
ዋንጫውን ማን ያነሳል? ሜሴ ወይስ ምባፔ? የእሑድ ሰው ይበለን።












