ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የቀረበበትን ቅሬታ ተከትሎ ታዋቂውን የሕጻናት ፓውደር ምርትን በሌላ ሊተካ ነው
ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ኩባንያ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በመላው ዓለም ታዋቂውን የሕጻናት ፓውደር ማምረት እና መሸጥ ለማቆም ወሰነ።
ለዚም ምክንያት የሆነው በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ይህ ታልክ የተሰኘ ንጥረ ነገር የያዘው ምርቱ ለማህጸን ካንሰር ዳርጎናል የሚል ክስ ካቀረቡ በኋላ ነው።
ኩባንያው ታልክ ከተሰኘ ንጥረ ነገር የሚያዘጋጀውን ይህንን የሕጻናት ፓውደር በአሜሪካ እና በካናዳ ማምረት እና መሸጥ ካቆመ ሁለት ዓመታት አልፈዋል።
ኩባንያው ለብዙ አሥርት ዓመታት የተካሄደ ጥናት ምርቱ ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ያሳያል ሲል ያስተባብላል።
"በዓለም አቀፍ ደረጃ ባደረግነው ግምገማ የሕጻናት ፓውደር ከበቆሎ ስታርች እንዲሠሩ ውሳኔ አሳልፈናል’’ ብሏል ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን በመግለጫው።
ተቋሙ ምንም እንኳ የሕጻናት ፓውደርን ለማምረት የሚጠቀምበትን ግብዓት ለመቀየር ቢወስንም አሁንም ታልክ ከተሰኘው ንጥረ ነገር የምሠራቸው ፓውደሮች ደኅንነታቸው የተጠበቀ ነው በሚለው አቋሜ እንደጸናሁ ነው ብሏል።
ኩባንያው ከሁለት ዓመታት በፊት በሰሜን አሜሪካ ምርቱን ከገበያ ያስወጣው በተሳሳተ መረጃ ምክንያት የምርት ፍላጎት በመቀነሱ ነው ብሎ ነበር።
በወቅቱ ኩባንያው ከታልክ የሚመረተውን የሕጻናት ፓውደር በዩናይትድ ኪንግደም እና በተቀረው ዓለም መሸጡን እንደሚቀጥል አስታውቆ ነበር።
ታልክ የተሰኘው ንጥረ ነገር ከመሬት ውስጥ ተቆፍሮ የሚወጣ ንጥረ ነገር ሲሆን አስቤስቶስ ከተሰኘው እና ካንሰርን እንደሚያመጣ ከሚታወቀው ንጥረ ነገር ጋር አብሮ ሊገኝ ይችላል።
የሮይተርስ የዜና ወኪል ከአራት ዓመታት በፊት ባካሄደው የምርመራ ዘገባ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን በታልክ ምርቶች ውስጥ አስቤስቶስ ንጥረ ነገር እንደሚገኝ ለአስርተ ዓመታት ያውቅ ነበር ብሏል።
ተቋሙ በፍርድ ቤቶች፣ በሚዲያ ዘገባዎች እና ከአሜሪካ ሕግ አውጪዎች የሚቀርቡበትን ክሶች በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጓል።
የኩባንያው ባለ አክሲዮኖች በሚያዚያ ወር ባደረጉት ጉባኤ የታልክ ንጠረ ነገር የያዘ ምርቶችን ለማስቆም እንዲወስኑ ሃሳብ ቢቀርብም ውድቅ አድርገውታል።
የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የሕጻናት ፓውደር ላለፉት 130 ዓመታት በመላው ዓለም የተሸጠ ሲሆን ምርቱ ሕጻናት ላይ የሚያጋጥም ሽፍታን ለመከላከል፤ ለመዋቢያ እና አንዳንዴም እንደ ደረቅ ሻምፑ ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል።