ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአል-ቃኢዳ መሪ ግድያን ተከትሎ ከአገር ውጪ ያሉ አሜሪካውያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ዋሽንግተን አሳሰበች
የአል-ቃይዳው መሪ አይማን አል-ዛዋሂሪን መገደል ተከትሎ በውጭ በሚገኙ አሜሪካዊያን እና ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ የበቀል ጥቃቶች ሊደርሱ እንደሚችሉ አሜሪካ አሳሰበች።
የግለሰቡ ሞት የአል-ቃይዳ ደጋፊዎችን እና ከአል-ቃይዳ ጋር አብረው የሚሰሩ ቡድኖች በአሜሪካ ዜገች ላይ እንዲሁም ተቋማት እና ሠራተኞች ላይ የበቀል እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ገልጿል።
ቢን ላደንን የተካው ዛዋሂሪ እሁድ ዕለት በአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ጥብቅ ጥብቃ በሚደረግበት ግቢ ውስጥ ውስጥ መገደሉ ይታወሳል።
ዛዋሃሪ ከቀድሞው የአል-ቃኢዳ መሪ ቢን ላደን ጋር በመሆን ከ20 ዓመታት በፊት የተፈጸመውን የ9/11 ጥቃትን የመራ ሲሆን፣ አሜሪካ ለረጅም ዓመታት ስታፈላልገው የቆየችው የሽብር ቡድኑ መሪ ነው።
9/11 ተብሎ በሚታወቀው ጥቃት ከ3000 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የ71 ዓመቱ ግብፃዊ ዶክተር አይማን አል-ዛዋሂሪ እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ የኦሳማ ቢን-ላደን ሕልፈትን ተከትሎ አል-ቃይዳን ሲመራ ቆይቷል።
የግለሰቡን መገደል ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሰጡት መግለጫ እርምጃው በ9/11 ጥቃት ወዳጅ፣ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ አሜሪካዊያን ለሐዘናቸው መልስ የሚሆን የመጨረሻውን መደምደሚያ የሚሰጥ እርምጃ ነውም ሲሉ ተደምጠዋል።
ባይደን ዛዋሂሪ እ.ኤ.አ በጥቅምት 2000 በኤደን የአሜሪካ የባሕር ኃይል ግዙፍ የጦር መርከብ ላይ በተሰነዘረ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት 17 የአሜሪካ መርከበኞችን የገደለውን ጥቃት መርቷል ሲሉ ተናግረዋል።
እንዲሁም ለ223 ሰዎች ሕልፈት ምክንያት የሆኑት በ1998 በኬንያ እና በታንዛኒያ በአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ የተፈፀሙትን ጥቃቶችንም በማስተባበር ዛዋሂሪ ኃላፊነት እንዳለበትም አክለዋል።
"የስቴት ዲፓርትመንት የአል-ዛዋሂሪ መገደልን ተከትሎ ለፀረ-አሜሪካዊያን ጥቃት ከፍተኛ ተጋላጭነት እንዳለ ያምናል" ሲል የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ በዓለም አቀፍ የማስጠንቀቂያ ስርዓቱ ላይ አስፍሯል።
"እስካሁን ባለን መረጃም የአሸባሪ ድርጅቶች የአሜሪካ ጥቅም ባለባቸው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ላይ የሽብር ጥቃቶቻቸውን ማቀዳቸውን ቀጥለዋል" ሲል ማስጠንቀቂያው አክሏል።
ጥቃቶቹም የአጥፍቶ መጥፋትን፣ ግድያዎችን፣ አፈናዎችን፣ ጠለፋዎችን እና የቦምብ ጥቃቶችን ጨምሮ የተለያዩ ስልቶችን ሊጠቀሙ እንደሚችሉም መስሪያ ቤቱ አክሏል።