ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት በዕጩነት የቀረቡት ግለሰቦች እነማን ናቸው?

ሜላትወርቅ ኃይሉ እና ታደሰ ለማ

የፎቶው ባለመብት, NEBE

የምስሉ መግለጫ, ሜላትወርቅ ኃይሉ እና ታደሰ ለማ

ከሦስት ወራት በፊት ከኃላፊነት የለቀቁት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳን የሚተኩ ሁለት ዕጩዎች ተለይተው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ቀርበዋል። ዕጩዎቹን የመለየት ሥራን ያከናወነው ምልመላውን እንዲያከናውን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው ኮሚቴ ነው።

በ2011 ዓ.ም. ግንቦት ወር ላይ የጸደቀው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ [የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ] ዕጩ ሥራ አመራር ቦርድ አባላትን የሚመለምል” ኮሚቴ እንደሚያቋቁሙ ያትታል። በዚህ ድንጋጌ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድ ወር ገደማ በፊት ጥቅምት መጨረሻ ስምንት አባላት ያሉትን ኮሚቴ አቋቁመው ነበረ።

ይኽው ኮሚቴ ከኅዳር 3/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለአስር ተከታታይ ቀናት ዕጩዎችን ሲቀበል ቆይቷል። ኮሚቴው በእነዚህ ቀናት ከቀረቡለት 56 ጥቆማዎች መካከል ሴቶቹ አራቱ ብቻ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ 52 ተጠቋሚዎች ወንዶች ናቸው።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ የሚመሩት ዕጩ መልማይ ኮሚቴ በሦስት ዙሮች አምስት ዕጩዎችን መለየቱን ቅዳሜ ኅዳር 22 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። ስምንት አባላት ያሉት ኮሚቴው በመጨረሻ ሁለት ዕጩዎችን ለይቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረቡን ይፋ አድርጓል።

የዕጩ መልማይ ኮሚቴው የመጨረሻ ዕጩ አድርጎ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረባቸው ወይዘሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ እና አቶ ታደሰ ለማን ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለት ዕጩዎች መካከል ለቦርዱ ሰብሳቢ ይሆናሉ ያሏቸውን ግለሰብ ለፓርላማው አቅርበው ያሾማሉ።

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 102 መሠረት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን ጨምሮ የቦርዱ አባላት የሚሾሙት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በተወካዮች ምክር ቤት ነው።

ስለ ዕጩዎቹ የምናውቀው

ወይዘሮ ሜላትወርቅም ሆኑ አቶ ታደሰ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኃላፊነት አዲስ አይደሉም። ሁለቱም ዕጩዎች ቦርዱን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል። ወይዘሮ ሜላትወርቅ ለሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ሰርተዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ምርቋ ሜላትወርቅ የሥራ ሕይወታቸው የሚጀምረው በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ነው። በኮሚሽኑ ከጀማሪ የሕግ ኦፊሰርነት እስከ ኦፕሬሽን ኃላፊነት ድረስ ሰርተዋል። የኒው ጀኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተባባሪ መሥራች የሆኑት ሜላትወርቅ የሕግ ማማከር አገልግሎት የሚሰጥ የሕግ ድርጅት አቋቁመው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወይዘሮ ሜላትወርቅ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ ከሰላም እና ደኅንነት ጥናቶች ተቋም (አይፒኤስኤስ) የማስተርስ ዲግሪያቸው ተቀብለዋል። በተጨማሪም ከአሜሪካው ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ኬኔዲ ትምህርት ቤት በሕዝብ አስተዳደር ሌላ የማስተርስ ዲግሪ አላቸው።

የምርጫ ቦርድ ሰብሰባቢ ዕጩዋ በአካዳሚክ፣ በፖሊሲ እና በፐብሊክ ሴክትር ባለሙያነት፣ በሁለትዮሽ እና በዘርፈ ባለብዙወገን ስምምነቶች ተደራዳሪነት፣ በግልግል ዳኝነት አማካሪ በመሆን ሰፊ ልምድ እንዳላቸው በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ።

የሜላትወርቅ የትምህርት ዝግጅት እና የሥራ ልምድ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትኩረት ስቦ በቦርዱ ሰብሳቢነት የሚያሾማቸው ከሆነ ምርጫ ቦርድን በሰብሳቢነት በመምራት ሦስተኛዋ ሴት ይሆናሉ።

የመጀመሪያዋ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሴት ሰብሳቢ ሳሚያ ዘካርያ ናቸው። በ2010 ዓ.ም የተሾሙት ሳሚያ ቦርዱን የመሩት ለአንድ ዓመት ያህል ብቻ ነው። ሳሚያ በገዛ ፈቃዳቸው ከኃላፊነት መልቀቃቸውን ተከትሎ ቦርዱ ሁለተኛዋ ሰብሳቢ የሆኑት ብርቱካን ሚደቅሳ ከአምስት ዓመታት በፊት ኅዳር 13/2011 ዓ.ም. ቦርዱን እንዲመሩ ተሹመዋል።

የብርቱካን ሹመት በፓርላማው በጸደቀበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ብርቱካንን “ለመንግሥትም ቢሆን እጅ የማይሰጡ ለሕግ እና ለሥርዓት ጽኑ እምነት ያላቸው” ሲሉ አሞካሽተዋቸው ነበር።

የቀድሞዋ ፖለቲከኛ ብርቱካን ሚደቅሳ የቦርዱ ሰብሳቢነት ሥልጣንን ከያዙ በኋላ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ሦስት ሕዝበ ውሳኔዎችን አካሂዷል።

ብርቱካን ቦርዱን ለአራት ዓመት ከመንፈቅ ከመሩ በኋላ ባለፈው ነሐሴ ወር ጤናቸውን “በሚገባ ለመጠበቅ የረጅም ጊዜ እረፍት” እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ ነበር ከኃላፊነት የለቀቁት።

ብርቱካን ሚደቅሳ ለአራት ዓመት ከመንፈቅ የያዙትን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት ለመረከብ ከሜላትወርቅ ኃይሉ ጋር ዕጩ ሆነው የቀረቡት ሌላኛው ግለሰብ አቶ ታደሰ ለማ ናቸው። አቶ ታደሰ የምርጫ ቦርድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው።

የ48 ዓመት ጎልማሳው አቶ ታደሰ ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ ነው። በጋምቤላ የመምህራን እና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ውስጥ በመምህርነት ሠልጥነዋል። በመቀጠልም ከኮተቤ መምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርነት በዲፕሎማ ተመርቀዋል።

አቶ ታደሰ ዲፕሎማቸውን ካገኙ በኋላ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር እና ርዕሰ መምህር ሆነው ሰርተዋል። አቶ ታደሰ ዲፕሎማቸውን ካገኙ ከስድስት ዓመታት በኋላ እንደገና ወደ ትምህርት ዓለም ተመልሰው ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ እና በሥነ ጽሁፍ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።

ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ ታደሰ፣ ከቡለን ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት እስከ ክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥልጠና ባለሙያነት የሰሩባቸው ቦታዎች ናቸው። በተጨማሪም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ነበሩ። አቶ ታደሰ ባለፈው ዓመት ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ግንኙነት የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

የቦርድ ሰብሳቢዋ/ው ቀጣይ የቤት ሥራ

አቶ ታደሰም ሆኑ ወይዘሮ ሜላትወርቅ የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው ከተመረጡ በኋላ የቀድሞዋ ሰብሳቢ ያላጠናቀቋቸው የቤት ሥራዎች ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል። ከእነዚህ ሥራዎች ቀዳሚው እና ትልቁ ያለፈው ምርጫ ባልተካሄደባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች ምርጫ ማካሄድ ነው።

ለሁለት ዓመት ጦርነት ሲካሄድበት በቆየው የትግራይ ክልል የፓርላማም የክልል ምክር ቤት ምርጫ አልተካሄደም። ክልሉ ላለፉት ሦስት ዓመታት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካይ የለውም። ከዚህ በፊት የነበረው የክልሉ ምክር ቤትም ሥልጣኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር አስተላልፏል።

ቦርዱ በተያዘው 2016 ዓ.ም. በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ ዕቅድ መያዙን ለፓርላማ አስታውቆ ነበር። መጪው የቦርዱ ሰብሳቢ ይህን ዕቅድ ያሳኩታል ወይ የሚለው በሂደት የሚታይ ጉዳይ ነው።

ምርጫ ያልተካሄደበት የትግራይ ክልል ብቻ አይደለም። አቶ ታደሰ ለማ ተወልደው ያደጉበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በተወሰኑ አካባቢዎች ነው ምርጫ የተካሄደው። በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በክልሉ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ድምጽ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት የለም።

ከ99 የክልሉ ምክር ቤት አባላት መካከል 72 በመቶ ያህሉ ከዘጠኝ ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ ነው ተወዳድረው ወደ ምክር ቤት የገቡት። ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ ብዙ ነገሮች ተቀያይረዋል።

ከዘጠኝ ዓመት በፊት በ2007ቱ ምርጫ በክልሉ ገዢ ፓርቲ ሆኖ የተወዳደረው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (ቤጉህዴፓ) ነበር። ቤጉህዴፓ ህልውናው አክትሞ ብልጽግና ሆኗል፤ ቤጉህዴፓን ወክለው የክልሉን ምክር ቤት የተቀላቀሉት ተመራጮች አሁንም እዚያው ናቸው።

እስካሁን ምላሽ ባያገኙም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከ2013 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ በክልሉ ምርጫ እንዲካሄድ እየወተወቱ ነው። እንደ ትግራይ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባይሆንም በአማራ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች በፀጥታ ችግር ምርጫ ያልተካሄደባቸው አካባቢዎችም አሉ። ቦርዱ በእነዚህ አካባቢዎችም በዚሁ ዓመት ምርጫውን ለማካሄድ ዕቅድ ይዟል።

የአካባቢ ምርጫም እንደዚሁ የመጪው የቦርዱ ተሿሚ ዋነኛ የቤት ሥራ ነው። በኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ የአካባቢ ምርጫ ተካሄደው ከ11 ዓመታት በፊት በ2005 ዓ.ም ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች የአካባቢ ምርጫ በአጠረ ጊዜ እንዲካሄድ ፍላጎታቸው ነው። ቦርዱ ሰብሳቢ በመሆን የሚሾሙት ግለሰብ ይህን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፍላጎት ማሳካት ይቻላቸው ይሆን?