ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኮሮናቫይረስ በአንዳንድ ምግቦች ላይ ለቀናት እንደሚቆይ ጥናት አረጋገጠ
የኮሮናቫይረስ በተለይም ታሽገው በሚሸጡ ምግቦች ላይ እንደሚቆይ የዩናትድ ኪንግደም ተመራማሪዎች ገለጹ።
የአገሪቱ የምግብ ጥራት ኤጀንሲ ባሰራው ጥናት ሳይንቲስቶች ቫይረሱን ሆነ ብለው በተወሰኑ የምግብ ማሸጊያዎች ላይ በማድረግ ሙከራውን አድረገዋል። ይህም በአትክልት እና ፍራፍሬ፣ ኬክ እና ዳቦ እንዲሁም የታሸጉ መጠጦች ሙከራው ተደርጎባቸዋል።
ሳይንቲስቶቹ ሳይታጠቡ ወይም ሳይበስሉ ሊበሉ የሚችሉ ምግቦችን በመምረጥ ነው ጥናቱን ያካሄዱት። ነገር ግን ይህ ሸማቾች ላይ የሚያመጣው አደጋ ያነሰ መሆኑን ገልጸዋል።
በአብዛኛው የምግብ ምርቶች ላይ ሳይንቲስቶቹ ያስቀመጡት የቫይረስ መጠን በ24 ሰአት ውስጥ ከፍተኛ ማሽቆልቆል ታይቶበታል። ነገር ግን በአንዳንድ ማሸጊያዎች ላይ ቫይረሱ ለአንድ ሳምንት ያህል እንደሚቆይ የሳውዝ ሃምፕተን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ተናግረዋል።
ሳርስ ኮቭ 2 የተሰኘውን የቫይረስ አይነት ወስደው ምርምሩን ያደረጉት አጥኚዎች እንደሚሉት ''እንደዚህ ያለ በንክኪ ብቻ በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰራጭ የቫይረስ አይነትን በተመለከተ ያገኘነው ግኝት ትኩረት የሚገባው ነው'' ሲሉ ተናግረዋል።
ሳይንቲስቶች ሸማቾች በተለይም ምግብ በሚያዘጋጁበት ወቅት እጃቸውን እንዲታጠቡ እና በጥሬው የሚበሉ ምግቦችን አጥበው እንዲመገቡ አሳስበዋል።
ተመራማሪዎች በጥናታቸው የኮሮናቫይረስ በንክኪ ከሚተላለፈው ይልቅ በምራቅ ፍንጣቂዎች በአየር አማካይነት የበለጥ እንደሚተላለፍ አረጋግጠዋል።
ጥናቱ እንዳረጋገጠው ቫይረሱ በተለይም ሸካራ ገጽ ባላቸው እንደ ብሮኮሊ ባሉ አትክልቶች ላይ እንደ ፖም ባሉ ልሙጥ ከሆኑት በበለጠ እንደሚቆዩም አረጋግጧል። ጥናቱ አክሎም ፖም በቅርፊቱ ላይ በያዘው ኬሚካል አማካኝነት በቂቃዎች ወይም በሰዓታት ውስጥ በላዩ ላይ ያረፈውን ቫይረስ መግደል እንደሚጀምርም አረጋግጧል።
በኬክ እና ዳቦ ላይ በተደረጉ ሙከራዎችም በአንዳንድ ደረቅ ገጽ በላቸው ኬኮች ላይ ቫይረሱ በሰአታት ውስጥ ቁጥሩ መቀነሱን ተናግረዋል። ለዚህም ምናልባት ኬኮቹ በሚበስሉበት ወቅት እንቁላል ስለሚቀቡ እና ይህም እንቁላል ውስጥ ካለ አሲድ አማካኝነት ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል።
በቺዝ እና ቀዝቃዛ ስጋ ቫይረሱን ለቀናት አንዳንዴም ለሳምንት ሊያቆዩ እንደሚችሉ ተመላክቷል።
ኮቪድ በፕላስቲካ እቃዎች ላይ እስከ አንድ ሳምንት ድረስ ሊቆይ ይችላል። በካርቶን ላይ ለተወሰኑ ቀናት ብሎም በአልሙኒየም ማሸጊያዎች ላይ የተወሰኑ ሰአታትን ሊቆይ እንደሚችል ሳይንቲስቶቹ ተናግረዋል።