በመድኃኒት እስከ 38 ኪሎ ውፍረት የቀነሱ ሴቶች ስለ ልምዳቸው ምን ይላሉ?

ከመጠን በላይ ውፍረት ከስንፍና እና ከአስቀያሚነት ጋር በሚያይዝባት ዓለም በርካቶች በውፍረታቸው ምክንያት ይሸማቀቃሉ፣ መድልዎም ይደርስባቸዋል።

ከመጠን በላይ ወፍራም የነበረችው ብራኔይሻ ኩፐር ለየት ያለ ፍጡር ነኝ የሚል ስሜት ይሰማት ነበር።

አካሏም ሌሎችን ይማርካል የሚል ሃሳብ አልነበራትም።

ከጓደኞቿ ጋር አብረው ለመዝናናት በሚወጡበት ወቅት ሌሎች በሰዎች ትኩረቶችን ሲያገኙ እሷን ዘወር ብሎ የሚመለከታት አልነበሯም።

የሚመለከቷትም ካሉ እንደ ልዩ ፍጡር በማፍጠጥ እና በጥያቄ እንደነበር ትገልጻለች።

የየእለት እንቅስቃሴዋም ሆነ ተግባሯ ያስጨንቃት ነበር።

እነዚህ መቀመጫዎች ይበቁኝ ይሆን? ይሄ ልብስስ ይለካኛል? ሌላም ሌላም በተለያዩ ስፍራዎች በአዕምሮዋ የሚመላለሱበት ጥያቄዎች ነበሩ።

በቴክሳስ ነዋሪ የሆነችው የ28 ዓመቷ ብራኔይሻ ከሶስት ዓመታት በፊት ሞንጃሮ የተሰኘውን የክብደት መቀነሻ መርፌን መወጋት ጀመረች። በዚህም መድኃኒት አማካኝነት 38 ኪሎግራም ቀነሰች።

ይህንን ያህል ኪሎ ከቀነሰች በኋላ ህይወቷ በብዙ መልኩ ተቀየረ። ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ስታደርግ የሚሰማት አካላዊ ህመም ቀነሰ እንዲያውም ጠፋ።

ከዚህ ቀደም ዝም የሚሏት የስራ ባልደረቦቿ በሌላ መልኩ ይመለከቷት እና ያናግሯት ጀመር። ዳንስ፣ የመኪና ውድድርን ጨምሮ ከዚህ በፊት ምቾች ይነሷት የነበሩ እንቅስቃሴዎችን ከወንድ ጓደኛዋም ጋር አብራ ታደርግ ጀመር። ውፍረት በመቀነሷ ምክንያት በህይወት ሁለተኛ ዕድል የተሰጣት ያህል ተሰማት።

"በአንድ ጀምበር ወደ ሌላ ዓለም የገባሁ ያህል ነበር" ትላለች ብራኔይሻ

"ሰዎች በድንገት የበለጠ ይቀርቡኝ፣ አትኩሮት ይሰጡኝ ጀመር። ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ዕድሎች እና አክብሮት ይደርሱኝ ጀመር" ስትል ታስረዳለች።

"ይህንን ያህል ለውጥ ማየቴ በባህላችን ውስጥ ውፍረትን አስመልክቶ ስር የሰደደ አድሏዊነት እንዳለ ለማየት ዓይኖቼን ከፈተልኝ፤ ያንኑ ተመሳሳይ ሰው ብሆንም በውፍረቴ ምክንያት ሰዎች በተለያየ መንገድ ነው የተመለከቱኝ" ትላለች

በበርካታ የዓለማችን ህዝብ ከመጠን በላይ ወፍራም (ኦቤሲቲ) መጨመር ጋር ተያይዞ ጉዳዪ መነጋገሪያ ከሆነ ውሎ አደረ። ለባለፉት ሶስት አስርት ዓመታትም ውፍረት አንድ የዓለማችን ርዕስ ሆኗል።

በአውሮፓውያኑ 90ዎቹ እና 2000ዎቹ ክብደት (ውፍረትን) መቀነስ የሚመለከቱ ጋዜጦች፣ የታዋቂ ተዋናዮች እና ሙዚቀኞችን የያዙ የአመጋገብ ምክሮች ተቸብችበዋል።

በተጨማሪም በመቶ ኪሎዎች የሚመዝኑ ሰዎች ከፍተኛ ክብደት ሲቀንሱ የሚያሳዩ እንደ 'ዘ ቢገስት ሉዘር'፣ 'ዩ አር ዋት ዩ ኢት' እና ሌሎችም ተከታታይ የቴሌቪዥን ትዕይንቶች ታዋቂ ሆነዋል።

በባለፉት አራት ዓመታት ሲማግሉቲድ እና ቲርዜፓታይድ የተሰኙ የክብደት መቀነሻ መርፌዎች ኦዜምፒክ፣ ዌጎቪ እና ሞንጃሮ በተሰኙ የምርት ስሞች ይሸጣሉ።

እነዚህ መርፌዎች ያለ ቀዶ ህክምና ከፍተኛ መጠን ያለው ውፍረት መቀነስ የሚያስችሉ ናቸው። መርፌዎቹ የምግብ ፍላጎትን በመግታት እንዲሁም ቶሎ ሆድ እንዲሞላ ያደርጋሉ።

በዩናትድ ኪንግደም ዌጎቪ በተሰኘው የምርት ስም የሚሸጡ መድኃኒቶች በብሔራዊ የጤና አገልግሎት ስር የተለያዩ መስፈርቶችን ለሚያሟሉ ይሰጣል።

ሆኖም ሌሎች የክብደት መቀነሻ መድኃኒቶች የበለጠ ተደራሽ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

ለሁሉም ሰዎች ተስማሚ ያልሆኑ እና ከባድ የጎንዮሽ ጉዳት የሚያስከትሉ መድኃኒቶችም በዩኬ ፋርማሲዎች ይገኛሉ። እነዚህ መድኃኒቶች በዶክተሮች የሚታዘዙ አይደሉም። ብራኔይሻ ብቻ ሳትሆን መርፌዎችን በመጠቀም ክብደት የቀነሱ በርካታ ሰዎች በህይወታቸው ከፍተኛ ለውጥ አግኝተናል ይላሉ። በሚወዷቸው እንዲያውም በማያውቋቸው ሰዎች ዘንድ ውፍረት ከቀነሱ በኋላ በተለየ መንገድ እንደሚታዩ እንዲሁም ህይወትን የሚመለከቱበት መንገድ እንደተለየም ያስረዳሉ።

በዩናይትድ ኪንግደም፣ ኬንት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆነችው የ29 ዓመቷ ጄስ ፊሊፕስ ከመጠን በላይ ወፍራም ስትሆኑ በርካቶች ዓይናችሁን ይሸሻሉ ወይም ደግሞ በማይሆን መልኩ ያፈጡባችኋል ትላለች።

ከዚህ ቀደም በአውሮፕላን ለመብረር፣ በህዝብ ትራንስፖርት ለመጓጓዝም ሆነ በሬስቶራንቶች ለመመገብ ምቾት አይሰማትም ነበር። በመኪና ሲያልፉ እንዲሁም በሙዚቃ ፌስቲቫል "ወፍራም" እያሉ የሚሰድቧት አልታጡም። ከሁለት ዓመት በፊት በጣልያኗ የባህር ዳርቻ ሶሬንቶ ያደረገችው ጉዞ ውፍረት ለመቀነሻ ምክንያት ሆናት። "ሁሉም ሰው ያፈጡብኝ ነበር። በዚህ ስፍራ እንዲህ አይነት ውፍረት አልለመዱም" ትላለች።

ጄስ ውፍረት ለመቀነስ ወሰነች። ክብደቷን መቀነሷም ሰዎች እሷን የሚመለከቱበትን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል ትላለች።

"አሁን ወደተለያዩ ቦታዎች ስሄድ ሰዎች የሚመለከቱት አይመስለኝም። እንደ ሌላው ሰው የሆንኩ ይመስለኛል" ስትል ታስረዳለች።

"ወፍራም ሰዎችን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች የሚገለሉ ሰዎች ወይ ሙሉ በሙሉ ትኩረት ይነፈጋሉ ወይም ደግሞ እንደ ልዩ ፍጥረት ያፈጡባቸዋል" ሲሉ በቴክሳስ ክርስቲያን ዩኒቨርስቲ የሶሺዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ጂኒን አ ጋይሌይ ያስረዳሉ።

ማህበረሰቡ ከመጠን ያለፈ ወፍራም ሰዎች ሊያሳዩት የሚገባ ባህርይ እንደሚጠብቅ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ካሌብ ሉና ይናገራሉ።

"ወፍራም ሰዎች እንድንደበቅ፣ በራሳችን እንድንሸማቀቅ እንዲሁም መኩራት እንዳይገባን ይጠበቅብናል" ሲሉ ፕሮፌሰር ሉና ይገልጻሉ።

በዩናይትድ ኪንግደምም ሆነ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ውፍረት (ክብደትን) ያካተተ ጥበቃ የለም። ውፍረት እንደ አካል ጉዳተኝነት ካልተፈረጀ በስተቀር በክብደታቸው ምክንያት ሰዎች ላይ መድልዎ መፈጸም ህገወጥ አይደለም።

የዘርፉ ምሁራን እንደሚናገሩት ከውፍረት ጋር የሚፈጠሩ መድልዎች በስራ ቃለ መጠይቅ ወቅት እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች በሚያናግሯቸው ወቅት እንደሚንጸባረቅ ያስረዳሉ። የሰዎችን ክብደት በማየት ምን አይነት ስብዕና ሊኖራቸው እንደሚችል ውሳኔ ላይ የሚደርሱም እንዳልታጡ ፕሮፌሰሯ ይናገራሉ።

"አንዳንድ ሰዎች ከመጠን በላይ ወፍራም ሰዎችን ሲያዩ ከፍተኛ ቁጣ ለምን እንደሚሰማቸው አይገባኝም" ስትል የምትናገረው የ35 ዓመቷ ባዮሎጂስት አሊክስ ሃርፊ ናት። አሊክስ የክብደት መቀነሻ መርፌ ተወግታ 20 ኪሎግራም የቀነሰች ሲሆን "ወፍራም ሰዎችን መጥላት በማህበረሰቡ የተወሰነ ተቀባይነት አለው"ስትል ታስረዳለች።

ክብደትን መቀነሳ መድኃኒቶች እንደ ብራኔይሻ፣ ጄስ እና አሊክስ ያሉ ሰዎችን ውፍረት እንዲቀንሱ ቢረዱም ለሁሉም ሰው ተስማሚ አይደሉም። የሴግማሉታይድ እና የቲርዜፓታይድ የተለመዱ የጎንሽ ጉዳቶች መካከል ተቅማጥ፣ ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ እንደሚገኙበት የብሔራዊ የጤና እና የእንክብካቤ ተቋም (ናይስ) ገልጿል።

አልፎ አልፎ ደግሞ ከሚከሰቱ የጎንዮሽ ጉዳቶች መካከል የከፋ የሐሞት ጠጠር በሽታ፣ የጣፊያ በሽታ እንዲሁም የብሔራዊ ጤና አገልግሎት ደግሞ የደም ስኳር በከፍተኛ መጠን መውረድ (ሃይፖግላይኬሚያ) አደጋዎች እንዳሉ ያስጠነቅቃሉ።

በፕሎማውዝ ዩኒቨርስቲ የስኳር በሽታ እና ኢንዶክሪኖሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆናታን ፒንኒ በበኩላቸው "በመድኃኒቶቹ ዙሪያ የሚጠበቁ ታላላቅ ሁኔታዎች እና ተስፋዎች ቢኖሩም" መድኃኒቶቹን ወስደው የቀነሱ ሰዎች ቢያቆሙ ውፍረታቸው ተመልሶ እንደሚመጣ ነው።

ይህም ማለት ክብደት ቅነሳው ዘላቂ አለመሆኑን ነው።

በዘለቄታው ክብደት ለመቀነስ መርፌዎቹ በተመጣጠነ ምግብ፣ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ መታገዝ አለባቸው።