የአፍሪካ አገራት በእስራኤል እና ሐማስ ግጭት የተለያየ አቋም ይዘዋል

የአፍሪካ መሪዎች የፍልስጥኤም ታጣቂ ቡድን ሐማስ በሰነዘረው ድንገተኛ ጥቃት ምክንያት የተቀሰቀሰውን ግጭት እንዲያቆሙ ሁሉንም ተፋላሚ ወገኖች ጠይቀዋል።

የአገራቱ አቋም ግን ሙሉ ለሙሉ ተመሳሳይ አልነበረም።

ዛምቢያ፣ ኬንያ እና ጋና ሐማስን በግልጽ አውግዘዋል። እስራኤልን እንደሚደግፉም አስታውቀዋል። ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ደቡብ አፍሪካ ለፍልስጥኤማውያን ያላቸውን ድጋፍ በይፋ ገልጸዋል።

እስራኤል ባለፉት አስር ዓመታት በአህጉሪቱ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎ አሳድጋለች። በርካታ የአፍሪካ አገራትም ኤምባሲዎቻቸውን ከቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም ለማዛወር አቅደዋል። ይህ ግን እስራኤል በዚህ ግጭት ከአፍሪካ የምትጠብቀውን ድጋፍ ሙሉ በሙሉ አላስገኘላትም።

የአፍሪካ ህብረት በፈረንሳይኛ እና በእንግሊዘኛ መግለጫ አውጥቷል። የግጭቶቹ መነሻ "የፍልስጥኤም ህዝብ በተለይም ነፃ እና ሉዓላዊ መንግስት የመመስረት መሠረታዊ መብቶች መነፈግ" መሆኑን ገልጿል።

“ሊቀመንበሩ ሁለቱ ወገኖች ወታደራዊ ግጭቶችን እንዲያቆሙ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር ጠረጴዛው እንዲመለሱ ጠይቀዋል። የፍልስጥኤምን ህዝብ እና የእስራኤላውያንን ጥቅም ለማስጠበቅ የሁለት መንግስታትን መርህ ተግባራዊ እንዲደረግም በአስቸኳይ ጥሪ አቅርበዋል” ሲሉ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ አክለዋል።

እስራኤል ቀደም ሲል በአፍሪካ ህብረት ስብሰባዎች ላይ በታዛቢነት ለመሳተፍ የነበራት ፍላጎት በአንዳንድ አገራት ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል።

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ተፋላሚ ወገኖች ወደ "ሁለት አገራት መፍትሔ" እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል። በተከሰተው ግጭት ማዘናቸውን በመግለጫቸውም አስታውቀዋል።

የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረትም ሙሴቬኒ የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በአውሮፓውያኑ 2016 እና 2020 አቀባበል አድርገውላቸዋል። የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት እአአ በ2020 በእስራኤል እና በሱዳን መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ሠርተዋል።

ድጋሚ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ግን የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለፍልስጥኤማውያን ድጋፍ ሰጥተዋል።

"በአሁኑ ጊዜ በፍልስጥኤምእየተከሰተ ያለውን አደገኛ እና አሳሳቢ ሁኔታ ሱዳን በቅርበት እየተከታተለችው ነው። የፍልስጥኤም ህዝቦች ነፃ አገር እና ህጋዊ መብት እንዲኖራቸው ሱዳን ድጋፏን በድጋሚ ትገልጻለች። ዓለም አቀፍ የግጭት አፈታቶች እንዲተገበሩ እና ንፁሃን ዜጎችን ከጥቃት እንዲጠብቁ ትጠይቃለች" ሲል በመንግስታዊው የዜና ወኪል ሱና በፌስቡክ ገጹ መግለጫውን አስነብቧል።

ደቡብ አፍሪካ "አፋጣኝ የተኩስ አቁም" እንዲደረስ ጥሪ አቅርባለች።

የአገሪቱ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ቢሮ "ቀጠናው በተባበሩት መንግስታት የሁለት መንግሥታት መፍትሔ እና በእስራኤል እና በፍልስጥኤም መካከል ፍትሐዊ እና ሁሉን አቀፍ ሠላም እንዲሰፍን ቀደም ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች የሚተገብር የሠላም ሂደት ይፈልጋል" ሲል አስታውቋል።

ናይጄሪያ በበኩሏ “አሁን ያለው የተባባሰው የብጥብጥ እና የበቀል አዙሪት በህዝብ ላይ የማያቋርጥ የስቃይ አዙሪት እንዲኖር ያደርጋል” በማለት አስጠንቅቃለች።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ “የጉዳቱ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ ተፋላሚዎቹ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

"ኬንያ ለዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት ከፍተኛ ስጋት ለሆነ ሽብርተኝነት ምንም አይነት ምክንያት ሊኖር እንደማይገባ አጥብቃ ታምናለች። ወንጀለኛው ማንም ይሁን ማን፤ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ሁሉም የሽብርተኝነት፣ የአመጽና የጽንፈኝነት ድርጊቶች አስጸያፊ፣ ህገወጥ እና ኢፍትሐዊ ነው" ሲሉ ኤክስ ላይ ጽፈዋል።

የዛምቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስታንሊ ካኩቦ የሐማስን ጥቃት በማውገዝ እስራኤልን ደግፈዋል።

"በሚያሳዝን ሁኔታ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት በሆነው እና በእስራኤል ላይ በቅርቡ የተፈጸመውን ጥቃት አጥብቀን እናወግዛለን። ሁሉንም ጥቃት እና የጥቃት ድርጊቶች በማያሻማ ሁኔታ እናወግዛለን። ዓለም አቀፍ ግጭቶችን ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን መከተል አስፈላጊ መሆኑንም አበክረን እናሳውቃለን" ብለዋል።