ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሶማሌ ልዩ ኃይል የአልሸባብ አባላትን እንደከበበ ተነገረ
የሶማሊያ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አልሻባብ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ወደ ምትዋሰንበት ግዛት ዘልቆ በመግባት ጥቃት ሰንዝሮ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሶ ነበር።
እስላማዊ ቡድኑ ይህን ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ በወሰደው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን እና የአልሸባብ አባላት ተከበው እንደሚገኙ ምንጮች ተናግረዋል።
ረቡዕ ዕለት ሐምሌ 13/2014 ዓ.ም. የአልሻባብ ታጣቂዎች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ገብተው ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ ከሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ከባድ ግጭት መካሄዱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እስላማዊው ቡድን አልሸባብ ከሶማሊያ ጋር ወደ ሚዋሰነው የኢትዮጵያ አፍዴር ዞን በመግባት ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት የተነገረ ሲሆን፣ የክልሉ ልዩ ኃይል ታጣቂዎቹን በሐረገሌ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ሁልሁል በተባለው ስፍራ እስላማዊ ታጣቂ ቡድኑን ከበው እንደሚገኙ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለሁለት ቀናት በዚህ በአልሻባብ እና በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል መካከል በተደረገው ግጭት አስካሁን ስለደረሰው ጉዳት የተረጋገጠ መረጃ ባይወጣም፣ ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ በርካታ ተዋጊዎች መገደላቸውና ጥቂት የማይባሉ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸው ተገልጿል።
ቢቢሲ ሶማሊኛ ያናጋራቸው አንድ የአካባቢው የፀጥታ ባለሥልጣን እንዳረጋጡት፣ የታጣቂዎቹ አባላት ሐርገሌ ወረዳ ውስጥ ሁልሁል በተባለ ስፍራ በተለይም ጎልድሂር በሚባል ቦታ ላይ ተከበዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው የገቡት የአልሻባብ ታጣቂዎች አላማቸው ምን እንደነበርና ወደዬት ለማምራት አስበው ጥቃት እንደከፈቱ የታወቀ ነገር የለም።
ቢቢሲ ሶማሊኛ እንደዘገበው ከዚህ ጥቃት ቀደም ብሎ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በኤልከሬ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ ሂሎ ማዶው በተባለ መንደር ውስጥ ባካሄደው አሰሳ በጉድጓድ ውስጥ ተቀብረው የነበሩ የተለያዩ አይነት የጦር ማሳሪያዎችን አግኝቷል።
ከዚህም ጋር በተያያዘም የአልሻባብ አባላት ናቸው የተባሉ ሰዎችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን፣ አሁን አልሻባብ የሰነዘረው ጥቃትም ከዚሁ ጋር የተገናኘ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለ።
የጥቃቱ ጅማሬ
ይህ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት አለው በሚባለው አልሻባብ ረቡዕ ዕለት የተፈጸመው ጥቃት ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንበት ባኩል በተባለው ግዛት ውስጥ በሚገኙት ዬድ እና አቶ ላይ ነው።
ይህንንም ተከትሎ ከኢትዮጵያ ጋር በሚዋሰኑት የሶማሊያ አካባቢዎች ውስጥ ነበሩ ከተባሉት የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት ጋር ውጊያ መካሄዱም ተዘግቧል።
ቢቢሲ ሶማልኛ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የአልሸባብ ተጣቂዎች በበርካታ ተሽከርካሪዎች ተጭነው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው ሲገቡ መመልከታቸውንና ከፍተኛ ውጊያ ከሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ጋር መደረጉን ተናግረዋል።
ጥቃቱን በሚመለከት ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከሶማሌ ክልል አስካሁን የተባለ ነገር ባይኖርም፣ ተቃዋሚው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ባወጣው መግለጫ ላይ ጥቃቱ መፈጸሙን አመልክቶ አልሻባብን አውግዟል።
እስላማዊ ቡድኑ የኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ከሶማሊያዋ ባኩል ግዛት ጋር በሚዋሰንበት አፍዴር ዞን ረቡዕ ሐምሌ 13/2014 ዓ.ም. ጥቃት ፈጽሞ በሕይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጿል።
ጨምሮም የክልሉ የፀጥታ ኃይል ጥቃቱን "በመመከት ተበታትነው የሚገኙትን የአልሻባብ አባላት በማሳደድ ላይ መሆናቸውን" ገልጾ፣ የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን ደኅንነት ለማስጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ በአስቸኳይ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል።
ለዚህ በአልሻብብ ለተፈጸመው ጥቃት ምክንያቱ ቀደም ብሎ አንድ የአልሻባብ ታጣቂዎች አዛዥ በአዋሳኝ የኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ከተገደለ በኋላ መሆኑን ሮይተርስ የዜና ወኪል ከኢትዮጵያ ወገን ያለ አዛዥን ጠቅሶ ዘግቧል።
የተገደለው የአልሻባብ ኣዛዥ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ የገባው በኢትዮጵያ ውስጥ ታጣቂ ቡድን ለማቋቋም እንደሆነ፣ ለመገናኛ ብዙኃን ለመናገር ሥልጣን ስለሌለኝ ስሜ አይጠቀስ ያለው ባለሥልጣን መናገሩን ሮይተርስ አመልክቷል።
ከኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ ባሉ መንደሮች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ሦስት ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ 17 ሰዎች መገደላቸውንና 63 የአልሻባብ ተዋጊዎች መገደላቸውን በስፍራው ያለ የፀጥታ ኃላፊ መገልጹን ሮይተርስ ዘግቧል።
ነዋሪዎች ምን ይላሉ?
ጥቃቱን ተከትሎ በአልሻባብ እና በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል መካከል ከባድ ውጊያ መካሄዱን ያረጋገጡት የድንበር አካባቢ ነዋሪዎች ግጭቱ በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ መካሄዱን ገልጸዋል።
“በስተመጨረሻ የአልሻባብ ታጣቂዎች ልዩ ኃይሎችን አሸንፈው የኢትዮጵያ ድንበርን በማለፍ ወደ ሶማሌ ክልል ገብተዋል” ሲል አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ነገር ግን በበርካታ መኪኖችና ሞተር ሳይክሎች በመሆን ድንበር ተሻግረው የገቡት ታጣቂዎቹ በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በተሰነዘረባቸው መልሶ ማጥቃት ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸውና ተበታትነው ወደ በሶማሊያ እንደሸሹ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የአልሸባብ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ቃል አቀባይ አብዱያሲስ አቡ ሙሳብ በሶማሊያ ውስጥ ሁለት ቀበሌዎችን በቁጥጥር ሥር ማድረጋቸውን እና በርካታ የልዩ ፖሊስ ኃይል አባላትን መግደላቸውን ተናግሯል።
ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት የአልሻባብ ታጣቂዎች በአፍዴር ዞን በሚገኘው ሀርጌሌ ወረዳ የጠረፍ አካባቢ እንደሚገኙ በመግለጽ፣ ነዋሪዎች የታጣቂዎቹ እንቅስቃሴ በፈጠረባቸው ስጋት ምክንያት መኖሪያቸውን በመልቀቅ ወደ ጫካ እንደሸሹ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የአልሸባብ ታጣቂዎች የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በመግባት ጥቃት ፈጽመው እንደማያውቁ እና ለዚህም በሶማሌ ክልል እና በሶማሊያ መካከል መካከል ባለው የድንበር አካባቢ የክልሉ ልዩ ኃይል እና የአገር መከላከያ ሠራዊት በመኖራቸው መሆኑን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሠራዊት በአፍሪካ ኅብረት ስር ታጣታቂውን አልሻባብ ለመዋጋት በሶማሊያ ውስጥ ተሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን፣ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ደግሞ የድንበር አካባቢ ጥበቃ ያከናውናል።
በዚህም ልዩ የፖሊስ ኃይሉ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንበት ባኮል ግዛት ውስጥ በሚገኙ ዬድ እና አቶ በተባሉት ከተሞች ተሰማርቶ እንደሚገኝ አንዳንድ ምንጮች አመልክተው፣ የአልሻባብ ጥቃትም የጀመረው በዚህ ስፍራ ነው።
የአልሻባብ ታጣቂዎች በተጠቀሱት የድንበር አካባቢዎች ባሉ የልዩ ኃይል አባላት ካምፖች ላይ ጥቃት ሰንዝረው ከፍተኛ ውጊያ የተካሄደ ሲሆን፣ በሰው ላይ ስለደረሰው ጉዳት አስካሁን የተገኘ ይፋዊ ዝርዝር መረጃ የለም።
ነገር ግን ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ አብዛኞቹ የአልሻባብ ታጣቂዎች የሆኑ ወደ ሰማኒያ የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል።
አልሻባብ ረቡዕ ዕለት በአዋሳኝ አካባቢዎች ከፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ በቡድኑ ላይ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት ምንጩን ጠቅሶ የዘገበው ሮይተርስ፣ የሶማሌ ክልል ፖሊስ ከባድ መትረየሶችና ተሽከርካሪዎችን ከቡድኑ ታጣቂዎች መማረኩን ጨምሮ አመልክቷል።
በተመሳሳይ የአልሻባብ ወታደራዊ ዘመቻዎች ቃል አቀባይ ሁለት መንደሮችን መያዛቸውን፣ በርካታ የልዩ ፖሊስ አባላት መግደላቸውን እንዲሁም የጦር መሳሪያዎችን መማረካቸውን ለሮይተርስ ሲገልጽ፣ በቡድኑ ታጣቂዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት ግን ከመናገር ተቆጥቧል።
በሶማሊያ ውስጥ በሚፈጽማቸው ከባድ ጥቃቶች የሚታወቀው አስላማዊው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ፣ አልፎ አልፎ በጎረቤት አገር ኬንያ ውስጥም ጥቃት ሲፈጽም ይታወቃል።
ነገር ግን ከዓመታት በፊት ጀምሮ ሠራዊቷን ሶማሊያ ውስጥ አሰማርታ እየተዋጋችው ባለችው ኢትዮጵያ ላይ ቡድኑ ይህ ነው የሚባል ጥቃት ፈጽሞ አያውቅም።
ቢቢሲ በዚህ ጥቃት ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከሶማሌ ክልል አስተዳደር በኩል ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።