ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የማንቸስተር ሲቲ በድል መንበሻበሽ የተሞገሰውን ያህል ለምን ጥያቄ ጫረ?
ማንቸስተር ሲቲ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ድል ለዘመናት ሲታወስ የሚከርም ነው።
ሲቲ ላለፉት ዓመታት ሲጠማቸው የነበረውን ዋንጫ በስተመጨረሻ አንስተዋል። ሶስት ዋንጫ በማፈስም ታሪክ ፅፈዋል።
ይህን ድል ያጣጣሙት የቡድኑ አባላትና አሠልጣኙ ሁሌም ሲዘከሩ ይኖራሉ።
የማንቸስተር ሲቲ ባላንጣ የሆኑት ማንቸስተር ዩናይትድ ተመሳሳይ ታሪክ በፈረንጆቹ 1998-99 የውድድር ዘመን አሳክተዋል።
ይህ ሲሆን በወቅቱ ሲቲ በእንግሊዝ እግር ኳስ ሶስተኛ ደረጃ ውድድር ላይ ተሳታፊ ነበሩ።
ሲቲ በቱርኳ ኢስታንቡል ይህን ታሪክ ድል ከማጣጣሙ በፊትም ቢሆን ከዩናይትድ የተሻለ ቡድን ገንብቷል።
በማንቸስተር ከተማ፤ በአጠቃላይ እንግሊዝ፤ አልፎም በአውሮፓ አሉ ከሚባሉ ቡድኖች ተርታ ተሰልፏል።
ሲቲ በድል የተንበሻበሸው የኳታር ባለሃብት የፈረንሳዩን ፒኤስጂ፤ የሳዑዲው ደግሞ ኒውካስልን በገዛበት ዘመን ነው።
የኳታር ንጉሣዊ ቤተሰብ ማንቸስተር ዩናይድትን ለመግዛት ደፋ ቀና እያሉ ነው።
የኢስታንቡሉ ድል የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ስፖርት ላይ እያፈሰሱ ያሉት መዋዕለ ንዋይ ማሳያ ነው።
የማንቸስተር ሲቲ የጨዋታ ‘ስታይል’ ማራኪ ነው። የጉዋርዲዮላ አሠለጣጠን የተመሰከረለት ነው። ዘመኑን የዋጀ የስፖርት አካዳሚም ገንብተዋል።
ሲቲ ፉትቦል ግሩፕ የተሰኘው ቡድን በውስጡ 13 ክለቦች አቅፏል።
የሲቲ ከ18 ዓመት በታች ቡድን ሶስት ተከታታይ ዓመታት ብሔራዊውን ቻምፒዮንሺፕ በመርታት ታሪክ ፅፏል።
የሲቲ ከ21 ዓመት በታች ቡድንም በተከታታይ ሦስት ጊዜ የፕሪሚዬር ሊግ 2 ዋንጫን በማንሳት የመጀመሪያው ሆኗል።
2016 እንደ አዲስ የተመሠረተችው የሲቲ የሴቶች ቡድን ሦስት ጊዜ የኤፍ ኤ ዋንጫ አንድ ጊዜ ደግሞ የሴቶች ሱፐር ሊግ አሸናፊ ሆናለች።
ዓለም አቀፍ ፖለቲካ
ነገር ግን የሲቲ እንዲህ በድል መንበሽበሽ ጥያቄ ሳያጭር አያልፍም።
የማንቸስተር ሲቲን ዕጣ ፈንታ የቀየሩት የክለቡ አብይ የአክሲዮን ባለድርሻ ሼኽ መንሱር ከዓመታት በኋላ ቡድናቸው ዋንጫ ሲያነሳ ለማየት ኢስታንቡል ተገኝተዋል።
የአቡ ዳቢ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አለቃ በፈረንጆቹ 2008 ሲቲን የግል ንብረታቸው ካደረጉ በኋላ ስታድየም ሲታደሙ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
የዩናይትድ አራብ ኤሜሬትስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት መንሱር በ13 ዓመት ውስጥ ቡድናቸው ሲጫወት ያዩት ሁለት ጊዜ ብቻ መሆኑ ጥያቄ ይጭራል።
እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፤ ዩኤኢ ስፖርትን ተጠቅማ ‘ሰብዓዊ መብት ጥሰቷን እየሸሸገች’ ነው የሚል እምነት አላቸው።
ባለፈው ወር 40 ገደማ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዩኤኢ “ሰብዓዊ መብትና ነፃነት ትገፋለች፤ የመብት ተሟጋቾችን ዒላማ ታደርጋለች፤ ጨቋኝ ሕግ አላት፤ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉን ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ ሰዎችን ለማስወገድ ተጠቅማዋለች” ሲሉ ወቅሰዋል።
ዩናይትድ አራብ ኤሜሬትስ ከዚህም አልፎም አካባቢን በመበከል ከዓለማችን ቁንጮዎች ትመደባለች።
የዩኤኢ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲም ሌላው አከራካሪ ጉዳይ ነው። አቡ ዳቢ ከሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ያላት ግንኙነት ጥያቄ ላይ ወድቋል።
ባለፈው መጋቢት የአሜሪካ መንግሥት፤ የዩኤኢ ኩባንያዎች ግምታቸው ሚሊዮን ፓውንዶች የሆነ ዕቃ ወደ ሩሲያ ልከዋል፤ ይህ ደግሞ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦችን የጣሰ ነው ሲል ሁኔታው እንዳሳሰበው ገልጧል።
ምርመራው እስኪገባደድ
‘ኤምቢዜድ’ በተሰኘ ቅፅል ስማቸው የሚታወቁት የአቡ ዳቢ ገዥ፤ ከወንድማቸው ሼክ መንሱር አጠገብ ተቀምጠው የሲቲን ጨዋታ ተመልክተዋል።
የአቡ ዳቢ ልጥጥ ባለሃብቶች ከዓለም አቀፍ ፖለቲካው አንፃር ብቻ አይደለም ስማቸው የሚነሳው።
ሲቲ ምንም እንኳ ዘንድሮ ሶስት ዋንጫ በልቶ ታሪክ ቢጋራም፤ ከ2009 እስከ 2018 ባለው ጊዜ ከ100 በላይ ሕግጋት ጥሷል የሚል ክስ ፕሪሚዬር ሊጉ አቅርቦበታል።
የክለቡ ባለሥልጣናት ለምርመራው ተባባሪ አይደሉም የሚል ወቀሳም አስተናግደዋል።
ሲቲ የሚቀርብበት ክስ ሁሉ ያስተባብላል።
በፈረንጆቹ 2020 ክለቡ ከአውሮፓ እግር ኳስ ማሕበር ክስ ቀርቦበት በስተመጨረሻ ነፃ ነው ተብሎ ተለቋል።
ነገር ግን ፕሪሚዬር ሊጉ ዓመታት ሊወስድ የሚችል ምርመራውን እስኪያጠናቅቅ ድረስ የሲቲ ስም መንቋሸሹ የሚቀር አይደለም።
ሲቲ በቱጃሮች መያዙ እንዲሁም በእግር ኳሱ ዓለም ስኬታማ መሆኑ የስፖርቱን የውድድር መንፈስ እየበረዘው ነው የሚሉም አሉ።
ፕሪሚዬር ሊጉን ማን ያነሳል የሚለውን መገመት እጅግ ቀላል እየሆነ መጥቷል። ካለፉት ስድስት የውድድር ዘመኖች አምስቱ በሲቲ ድል አድራጊነት ነው የተጠናቀቁት።
በሚቀጥለው ዓመትም ዋንጫውን ያነሳሉ ተብለው ከሚገመቱ ቡድኖች አንዱ ሲቲ ነው። ለአራተኛ ተከታታይ ጊዜ ዋንጫውን ካነሳ በእንግለዝ ፕሪሚዬር ሊግ ታይቶ የማይታወቅ ይሆናል።
እርግጥ ነው በርካታ የሲቲ ደጋፊዎች ይህ ሁሉ ትችት እየተሰነዘረ ያለው ሲቲ ድል በድል ከመሆኑ የመነጭ ቅናት ነው ይላሉ።