የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለን ጨምሮ ሦስት የቦርዱ አባላት በአዲስ ሊተኩ ነው

የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ (ግራ)፣ ብዙወርቅ ከተተ (መሀል) እና ዶ/ር አበራ ደገፉ (ቀኝ)

የፎቶው ባለመብት, National Election Board of Ethiopia

የምስሉ መግለጫ, የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ (ግራ)፣ ብዙወርቅ ከተተ (መሀል) እና ዶ/ር አበራ ደገፉ (ቀኝ)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለን ጨምሮ የሥራ ዘመናቸው ሊጠናቀቅ የተቃረቡ ሦስት የቦርዱ አባላት በአዲስ ሊተኩ ነው። የሦስቱን አዲስ የምርጫ ቦርድ አመራር ዕጩ ለመመልመል የተዋቀረው ኮሚቴ፤ ከነገ ረቡዕ ሚያዝያ 1/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ጥቆማ መቀበል እንደሚጀምር አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስምንት አባላትን የያዘ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ዕጩ መልማይ ኮሚቴ እንደሰየሙ ይፋ የተደረገው ባለፈው ሳምንት መጋቢት 22/2017 ዓ.ም. ነበር።

ኮሚቴው ከተቋቋመ በኋላ የዕጩ ምልመላ ሥራውን ለመምራት የሚያስችሉ እንደ የውስጥ አሠራር መመሪያ ማጽደቅ እና የመመልመያ የጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀት ያሉ ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱን የኮሚቴው ሰብሳቢ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም. በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ከነገ ጀምሮ ጀምሮ ለቀጣዮቹ 21 ቀናት ከሕዝብ የዕጩ ጥቆማ እንደሚቀበል ይፋ እንደሚያደርግም ሰብሳቢው ገልጸዋል። ከነገ ሚያዝያ 1 እስከ ሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም. ጥቆማ የሚካሄደው ቦርዱ ካሉት አምስት አባላት ውስጥ ምክትል ሰብሳቢውን ጨምሮ ሦስት አባላቱን ለመተካት ነው።

ቀሲስ ታጋይ እንደሚያስረዱት እነዚህን የምርጫ ቦርድ አመራሮች ለመተካት ሂደት የተጀመረው የሥራ ዘመናቸው የማጠናቀቂያ ጊዜ በመቃረቡ ነው። ዕጩ ጥቆማ የሚደረግባቸው የቦርድ አባላት፤ ምክትል ሰብሳቢው አቶ ውብሸት አየለ እንዲሁም ዶ/ር አበራ ደገፉ እና ብዙወርቅ ከተተ ናቸው።

ላለፈው አምስት ዓመት ከ10 ወራት ገደማ የተቋሙ ሥራ አመራር ቦርድ አባላት ሆነው ሲሠሩ ቆዩት እነዚህ አመራሮች የተሾሙት ከስድስት ዓመት በፊት በምርጫ ቦርድ ላይ ከተደረገው የሕግ ማሻሻያ በኋላ ነበር።

በ2011 ዓ.ም. የወጣው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ተቋሙ "ሙሉ ጊዜ የሚያገለግሉ አምስት የሥራ አመራር ቦርድ" አባላት እንደሚኖሩት እና የሥራ ዘመናቸውም ስድስት ዓመት እንደሆነ ደንግጓል። የሥራ አመራር ቦርዱ አባላት "ለአንድ ተጨማሪ ሥራ ዘመን በድጋሚ ሊሾሙ" እንደሚችሉ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።

የቦርዱ አባላት በአዋጁ ከተሰጧቸው ኃላፊነቶች መካከል "የምርጫ ውጤቶች ይፋ ከመደረጋቸው በፊት ማጽደቅ" የሚለው ይገኝበታል። በምርጫ ሂደት ውስጥ "ውጤትን የሚያዛንፍ የሕግ ጥሰት" በሚከሰትበት ወቅትም፤ የምርጫ ውጤትን የመሰረዝ እንዲሁም ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ የመወሰን ኃላፊነት የተሰጠው ለእነዚሁ የቦርዱ አባላት ነው።

በ2011 ዓ.ም ከተሾሙት የቦርዱ አመራሮች መካከል ዶ/ር ጌታሁን ካሳ ከአንድ ዓመት በኋላ የለቀቁ ሲሆን ሰብሳቢዋ ብርቱካን ሚደቅሳ ደግሞ በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ ከኃላፊነት ተሰናብተዋል

የፎቶው ባለመብት, Fana/youtube

የምስሉ መግለጫ, በ2011 ዓ.ም ከተሾሙት የቦርዱ አመራሮች መካከል ዶ/ር ጌታሁን ካሳ ከአንድ ዓመት በኋላ የለቀቁ ሲሆን ሰብሳቢዋ ብርቱካን ሚደቅሳ ደግሞ በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ ከኃላፊነት ተሰናብተዋል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ምርጫ ቦርድ በአሁኑ ሰዓት ካሉት አምስት የሥራ አመራር ቦርድ አባላት መካከል ሦስቱ የተሾሙት ሰኔ 2011 ዓ.ም. ነበር። ከአዋጁ መጽደቅ በኋላ የተሾሙት የቦርድ አባላት፤ ምክትል ሰብሳቢው አቶ ውብሸት አየለ፣ ዶ/ር አበራ ደገፉ፣ ብዙወርቅ ከተተ እና ዶ/ር ጌታሁን ካሳ ናቸው።

ከዚህ አስቀድሞ በኅዳር 2011 ዓ.ም. በምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት የተሾሙት ብርቱካን ሚደቅሳ ደግሞ በኃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ ተደርገው ነበር።

በወቅቱ ከተሾሙት የቦርድ አባላት አንዱ የነበሩት ዶ/ር ጌታሁን ካሳ ከአንድ ዓመት ከሦስት ወር በኋላ በመስከረም 2013 ዓ.ም. በፈቃዳቸው ከኃላፊነት ለቅቀዋል። በምትካቸውም አቶ ፍቅሬ ገብረሕይወት ኅዳር 2013 ዓ.ም. ተሾመዋል።

ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ላይ ምርጫ ቦርድን በሰብሳቢነት እንዲመሩ ከተሾሙት ሜላትወርቅ ኃይሉ እና አቶ ፍቅሬ ውጪ ያሉት የቦርድ አባላት የሥራ ዘመናቸው ሊጠናቀቅ የቀረው የሦስት ወራት ገደማ ዕድሜ ነው።

ከብዙዎቹ የቦርዱ አባላት በአንድ ዓመት ከሦስት ወር ዘግይተው የተመረጡት አቶ ፍቅሬ የሥራ ዘመናቸው ለመጠናቀቅ ከሁለት ዓመት ያነሰ ጊዜ ይቀረዋል።

የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ለአንድ ተጨማሪ የሥራ ዘመን በድጋሚ ሊሾሙ እንደሚችል የሚገልጸው የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ይህንን የማድረግ ሥልጣን የጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሆነ ደንግጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የትኛውንም የሥራ አመራር ቦርድ አባል" የሥራ ዘመኑ "ባለቀ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ" በድጋሚ የሚያሾሙት "በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ" እንደሆነ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።

አሁን የሥራ ዘመናቸው የተጠናቀቀ የቦርዱ አመራሮች በድጋሚ ሊመረጡ ይችሉ እንደሆነ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው ቀሲስ ታጋይ፤ የዕጩ መልማይ ኮሚቴው መቋቋም በሥራ ላይ ያሉት የቦርድ አባላት ጊዜ እንደማይራዘም የሚያመለክት መሆኑን የሚገልጽ ምላሽ ሰጥተዋል።

ቀሲስ ታጋይ፤ "ሥልጣኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሆነ እዚያው ማራዘም ይችሉ ነበር። ነገር ግን ቀጥታውኑ እንድናስመርጥ ይህንን ኮሚቴ የማዋቅር ሥልጣን የእሳቸው ስለሆነ አድርገውታል" በማለት አብራርተዋል። ይሁንና ነባሮቹ የቦርድ አባላት በሕዝብ የሚጠቆሙ እና የማጣራት ሂደቱን የሚያልፉ ከሆነ በዕጩነት የሚቀርቡበት መንገድ ዝግ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በምርጫ ቦርድ ማቋቋሚ አዋጅ መሠረት አዲስ የሥራ አመራር ቦርድ አባላትን የመሾም ሂደት ሦስት ደረጃዎችን ያልፋል። የመጀመሪያው ሂደት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቋቋም ገለልተኛ ኮሚቴ አካማካኝነት ዕጩ አባላትን መመልመል ነው።

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ

የፎቶው ባለመብት, House of Peoples Representatives

የምስሉ መግለጫ, ሜላትወርቅ ኃይሉ ታኅሣሥ 2016 ዓ.ም. የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት የዕጩ መልማይ ኮሚቴ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ካቀረባቸው ሁለት ዕጩዎች መካከል ተመርጠው ነው

ይህ ኮሚቴ የሚዋቀረው ከሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ከሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ከሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን፣ ከሳይንስ አካዳሚ እንዲሁም ከንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከሚወከሉ አምስት አባላት ነው። ቀሪዎቹ ሦስት የኮሚቴ አባላት የሚመመረጡት ደግሞ ከሲቪል ማኅበራት እና ከሀገር ሽማግሌዎች ነው።

በዚህ መልኩ የሚዋቀረው ዕጩ መልማይ ኮሚቴ፤ ለሥራ አመራር ቦርዱ አባልነት የሚጠቆሙ ግለሰቦችን ጥቆማ የመቀበል፣ የመለየት እና ፈቃደኝነታቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ተጥሎበታል። ኮሚቴው፤ ማጣራቱን ያለፉ ዕጩዎች ዝርዝር "ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ" እንደሚልክ አዋጁ ያስረዳል።

ባለፈው ሳምንት የተዋቀረው ኮሚቴም ከሚያዝያ 1 ጀምሮ ጥቆማ መቀበል እንደሚጀመር ይፋ አድርጓል። የዕጩ ጥቆማው በኢሜይል፣ በአካል እንዲሁም በፖስታ ሊከናወን እንደሚችል ቀሲስ ታጋይ ገልጸዋል። ሕዝቡ ጥቆማ ሊሰጥ የሚችልበት የቴሌግራም እና ዋትስአፕ ቁጥርም ይፋ እንደሚደረግ የኮሚቴው ሰብሳቢ አስታውቀዋል።

እንደ ቀሲስ ታጋይ ገለጻ፤ እስከ ሚያዝያ 21 የሚካሄደው የዕጩ ጥቆማ ከተጠናቀቀ በኋላ ቦርዱ "የተጠቆሙ ሰዎች በአዋጁ መሠረት የተቀመጡ መስፈርቶች መሟላታቸውን" እንደሚያረጋግጥ እንዲሁም "የተለዩትም ለቃለ መጠይቅ ሊጋብዝ" ይችላል።

በምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት በቦርድ አባልነት የሚሾሙ ሰዎች አምስት መስፈርቶች ማሟላት ይኖርባቸዋል። ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆን፣ የማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል አለመሆን፣ "መልካም ሥነ ምግባር እና ሰብዕና" መኖር እንዲሁም "ኃላፊነት ለመሸከም የሚያስችል ከፍተኛ የአመራር በቃት" ከመስፈርቶቹ መካከል ናቸው።

"ከምርጫ ጉዳዮች ጋር ተያያዥነት ባላቸው በተለይም በሕግ፣ በፖለቲካል ሳይንስ፣ በሕዝብ አስተዳደር፣ በስታትስቲክስ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ተዛማጅነት ባላቸው ዘርፎች ከፍተኛ ሙያዊ ብቃት" መያዝም በመስፈርትነት ተቀምጧል።

የዕጩ መልማይ ኮሚቴው በዚህ መስፈርት መሠረት የለያቸውን ግለሰቦች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያቀርባል። ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ዕጩዎች ብዛት ከሚፈለገው የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ብዛት "እጥፍ" መሆን እንዳለበት አዋጁ ያስረዳል።

በዚህ መሠረት በዕጩነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ግለሰቦች ብዛት ስድስት እንደሚሆን ቀሲስ ታጋይ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀረበላቸው የዕጩዎች ዝርዝር ላይ "ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር ምክክር" ማደረግ እንደሚጠበቅባቸው በአዋጁ ላይ ተደንግጓል።

አዋጁ "[ጠቅላይ ሚኒስትሩ] ምክክር ካደረገ በኋላ ከቀረቡት ዕጩዎች መካከል በሥራ አመራር ቦርዱ ውስጥ ባሉት ክፍት ቦታዎች ዕጩዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሾሙ ያቀርባል" ሲል ቀጣዩን ሂደት ያስረዳል።

ክፍት ከሆኑት የኃላፊነት ቦታዎች መካከል የቦርድ ሰብሳቢ እና ምክትል ሰብሳቢ ቦታ የሚገኝበት ከሆነ የትኞቹ ዕጩዎች ለዚህ ኃላፊነት እንደታጩ ተለይቶ እንደሚቀርብም በአዋጁ ላይ ተጠቅሷል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡት ዕጩዎች የሚሾሙት "የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ ሹመቱን ሲያጸድቀው" እንደሆነም የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ይደነግጋል።