እስራኤል በሶሪያ የኬሚካል ጦር መሣሪያ ይገኝባቸዋል ባለቻቸው ቦታዎች ላይ የአየር ጥቃት ፈጸመች

የእስራኤል ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ወታደሮች

እስራኤል በሶሪያ የኬሚካል ጦር መሣሪያ እና ሚሳዔሎች ይገኙባቸዋል ባለቻቸው አካባቢዎች ላይ የአየር ጥቃት እየፈጸመች መሆኑን አስታወቀች።

የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ጌድዮን ሳር ጥቃቱ እየተፈጸመ ያለው "የጦር መሣሪያዎቹ በጽንፈኞች እጅ ላይ እንዳይወድቁ ነው" ብለዋል።

የእስራኤል መከላከያ አባል በእስራኤል ይዞታ ሥር ካለው የጎላን ተራራማ አካባቢ ተነስቶ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች ወደሚገኙበት ሥፍራ ሲሻገር የሚያሳይ ምሥልም አጋርቷል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ወታደሮቻቸው በጎላን ተራራ የሚገኘውን እና ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ የሆነውን አካባቢ በጊዜያዊነት እንደተቆጣጠሩ መናገራቸው ይታወሳል።

የሶሪያ አማጽያን አገሪቱን በመቆጣጠራቸው ምክንያት በአውሮፓውያን 1974 ከሶሪያ ጋር የተደረሰው ስምምነት "ተቀልብሷል" ሲሉም ተደምጠዋል።

የጎላን ተራራማ አካባቢ ከዋና ከተማዋ ደማስቆ በ60 ኪሎሜትር ርቀት ይገኛል።

እስራኤል የጎላን ተራራማ አካባቢን ከሶሪያ የወሰደችው እአአ በ1967 በተካሄደው የስድስቱ ቀናት ጦርነት ወቅት ነበር።

በይፋ የግዛቷ አካል ያደረገችው ደግሞ በ1981 ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን ዕውቅና አልሰጣትም።

አሜሪካ ግን በ2019 የጎላን ተራራማ አካባቢ በእስራኤል ለመያዙን ዕውቅና ሰጥታለች።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ጌድዮን ሳር "የእስራኤል መከላከያ ኃይል የተወሰነ እና ጊዜያዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ያለው በደኅንነት ምክንያት ነው" ብለዋል።

እስራኤል በሶሪያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላት እና ዋነኛ ግባቸው ዜጎቻቸውን መከላከል እንደሆነም አክለዋል።

እስራኤል ወረራ የፈጸመችው የሶሪያ አማጽያን መዲናዋ ደማስቆን ተቆጣጥረው ፕሬዝዳንት በሻር አል አሳድን ካስወገዱ በኋላ ነው።

የአማጺ ቡድኑ ሃያት ታሕሪር አል-ሻም እሁድ ዕለት ደማስቆን ሲቆጣጠር በብሔራዊ ቴሌቭዢን ባስተላለፈው መልዕክት ሶሪያ "ነጻ ወጥታለች" ማለቱ ይታወሳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እሁድ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ የአሳድ መንግሥት የመወደቀበትን ዕለት "በመካከለኛው ምሥራቅ ታሪካዊ ቀን" ብለውታል።

የአሳድ መንግሥት ለዓመታት በተካሄደው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ዋነኛውን ድጋፍ ከሄዝቦላህ እና ከሩሲያ ሲያገኝ ቆይቷል።

ሆኖም ባለፈው አንድ ዓመት ሄዝቦላህ ሐማስን ደግፎ በጋዛው ጦርነት መሳተፉ እንዲሁም በሊባኖስ በኩል ከእስራኤል ጋር በገባው ጦርነት ሲዳካም፣ በተጨማሪ ደግሞ ሩሲያ ያላትን ሀብት በዩክሬን ወደምታደርገው ጦርነት ስታዞር የአሳድ ድጋፍ ተመናምኖ ነበር።

ይህንን አጋጣሚ የተጠቀመው አማጺው ቡድን በፍጥነት የሶሪያን ዋና ዋና ከተሞች በመቆጣጠር በሳምንታት ውስጥ አሳድን ለመገልበጥ ችሏል።

በአውሮፓውያኑ 2011 በበሻር አል አሳድ ላይ ሕዝባዊ አመጽ ሲቀሰቀስ እስራኤል ሶሪያ ምንም እንኳን የዋነኛ ጠላቶቿ የኢራን እና የሄዝቦላህ አጋር ብትሆንም ከአሳድ ቀጥሎ ሊመጣ ከሚችለው መንግሥት ይሻሉኛል ብላ በዝምታ ቆይታ ነበር።

የአሳድ አስተዳደር መውደቅን ተከትሎ ኔታኒያሁ እሁድ ዕለት ባደረጉት ንግግር ከእስራኤል ጋር በሰላም ለመኖር ለሚፈልጉ ሶሪያውያን አገራቸው "የሰላም እጇን ትዘረጋለች" ብለዋል።

ጨምረውም በሶሪያ ውስጥ በሚገኘው የመከላከያ ቀጣና ውስጥ ወታደሮቻቸውየተሰማሩት "ተስማሚ የደኅንነት ሁኔታ እስኪመቻች ድረስ ጊዜያዊ የመከላከያ ይዞታ ለመፍጠር ነው" በማለት ጦራቸው ከሶሪያ ግዛት እንሚወጣ አሳውቀዋል።

"በሶሪያ ሥልጣን ከሚይዙት ኃይሎች ጋር የመልካም ጉርብትና እና የሰላም ግንኙነት መፍጠር ከቻልን፣ ያ የእኛ ፍላጎት ነው። ያ ካልሆነ ግን የእስራኤል አገረ መንግሥትን እና ድንበሯን ለመከላከል አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን" ብለዋል።

አሳድን የገለበጠው አማጺ ቡድን መሪ የአቡ ሞሐመድ አል ጃውላኒ ቤተሰቦች መሠረታቸው ለዘመናት በእስራኤል ወረራ ስር ከሚገኘው የጎላን ተራራማ ስፍራ በመሆኑ በእስራኤል በኩል ስጋት መፈጠሩ አይቀርም። በድንበር አካባቢ ያለው ስፍራ በእስራኤል ከተያዘ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች 20 ሺህ ከሚሆኑ ሶሪያውያን ጎን ለጎን ይኖራሉ።

እስራኤል አሁን በሶሪያ ውስጥ የፈጸመችው ጥቃት አዲስ ነገር አይደለም። ከዚህ ቀደምም ከኢራን እና ከሄዝቦላህን ጨምሮ ከሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው ባለቻቸው ዒላማዎች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአየር ድንደባዎችን ሶሪያ ውስጥ አካሂዳለች።

በተለይ በጋዛ ውስጥ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በሶሪያ እና በሊባኖስ ያሉ ሄዝቦላህ እና ሌሎች ታጣቂ ኃይሎች በሰሜን እስራኤል የሚፈጽሙትን ድንበር ዘለል ጥቃት ለመበቀል ተደጋጋሚ የአየር ድብደባዎችን ስትፈጽም ቆይታለች።