ወታደራዊ ሕግ ለመደንገግ የሞከሩት የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ከአገሪቱ እንዳይወጡ ታገዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወታደራዊ ሕግ ለመደንገግ በመሞከር ምርመራ እየተደረገባቸው የሚገኙት የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል ከአገር እንዳይወጡ ዕገዳ ተጣለባቸው።
የደቡብ ኮሪያ አመራሮች ፕሬዝዳንቱ ከአገሪቱ እንዳይወጡ የጉዞ ዕቀባ መጣላቸውን አስታውቀዋል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ክስ ሊመሠርትባቸው ከጫፍ ደርሶ ነበር። ሆኖም ግን የገዢው ፓርቲ (ፒፒፒ) አባላት የሆኑ የአገሪቱ ምክር ቤት አባላት ፕሬዝዳንትቱ እንዲከሰሱ የተሰጠውን ድምጽ አግደዋል።
ፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማገድ እና በውጭ እንዲሁም በአገር ውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ላለመግባት መስማማታቸውን ተከትሎ ነው እንዳይከሰሱ የተወሰነው።
ተቃዋሚ ፓርቲው 'ዴሞክራቲክ ፓርቲ' ግን ክስ ሳይመሠረት መቅረቱን አልተቀበለውም።
የፓርቲው መሪ ፓርክ ቻን-ዴ "ይህ ሕገ ወጥ፣ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር እና ሁለተኛ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ለአጭር ጊዜ የቆየው ወታደራዊ ሕግ መደንገጉን ተከትሎ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን እንዲወገዱ እና እንዲከሰሱ ጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ ባይከሰሱም ከወታደራዊ ሕጉ መደንገግ ጋር በተያያዘ ተሳትፎ ያላቸው ቁልፍ የአገሪቱ ባለሥልጣናት እርምጃ ተወስዶባቸዋል።
ወታደራዊ ሕግ እንዲደነገግ ለፕሬዝዳንቱ ሐሳብ ያቀረቡት የቀድሞው መከላከያ ሚኒስትር ኪም ዮንግ-ሁን ትናንት በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ያለፈው ሳምንት ረቡዕ ሥልጣናቸውን ለቀው "ኃላፊነት እወስዳለሁ" ብለው ነበር።
የመከላከያው ስለላ ክፍል ኮማንደር ይዎ ኢን-ሁንግ እና ኤታማዦር ሹሙ ፓርክ አን-ሱ ላይ የጉዞ ማዕቀብ ተጥሏል።
ሥልጣናቸውን ለቀው "የሕዝቡ እና የፕሬዝዳንቱን ፍላጎት ባለማስጠበቄ ኃላፊነት እወስዳለሁ" ያሉት የቀድሞው የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሊ ሳንግ-ሚንም የጉዞ ዕቀባ ተጥሎባቸዋል።
የገዢው ፓርቲ ፒፒፒ መሪ ሀን ዶንግ-ሁን፣ ፕሬዝዳንቱ በአገር ውስጥ እና በውጭ ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገቡ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ሀን ደክ-ሱ ኃላፊነት እንደሚረከቡ ተናግረዋል።
"ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን ሳይለቅ በፊት ዲፕሎማሲን ጨምሮ በማንኛውም ጉዳይ ጣልቃ አይገባም" ብለዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲው 'ዴሞክራቲክ ፓርቲ' መሪ ፓርክ ቻን-ዴ ግን "ሁለተኛ መፈንቅለ መንግሥት" ሲሉ ነው ክስተቱን የገለጹት።
የፓርቲው ተወካይ ኪም ሚን-ሱክም የገዢው ፓርቲ መሪ ውሳኔ ለማሳለፍ "ሥልጣን የለውም" ሲሉ ተችተዋል።
"ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የገዢው ፓርቲ ማንም ሥልጣን ሳይሰጣቸው የፕሬዝዳንቱን ኃላፊነት መረከባቸው ሕገ መንግሥቱን ይጻረራል" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ለአገሪቱ ብሔራዊ መከላከያ ትዕዛዝ የማስተላለፍ ሥልጣናቸው ባለበት እንደሚቆይ ተገልጿል። ይህ ማለት ከሰሜን ኮሪያ ትንኮሳ ቢኖር የመጨረሻውን ውሳኔ የሚሰጡት ፕሬዝዳንቱ ይሆናሉ ማለት ነው።
በሚዮንግጂ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ሺን ዩል ለኮሪያ ሄራልድ እንዳሉት፣ ፕሬዝዳንቱ "ሐሳባቸውን ከለወጡ ወደ መሪነት መመለስ" ይችላሉ።
"ማንም ሊያስቆማቸው አይችልም" ሲሉ አስረድተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ወታደራዊ ሕግ በመደንገጋቸውና ሕዝቡ ላይ በፈጠረው "ጭንቀትና ውጣ ውረድ" በይፋ ዜጎችን ይቅርታ ጠይቀው በድጋሚ ወታደራዊ ሕግ እንደማይደነግጉ አስታውቀዋል።
ተቃዋሚዎች ግን ፕሬዝዳንቱ እንዲከሰሱ ግፊት ማድረግ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
"ለመጪው የገና በዓል እና ለአዲስ ዓመት ስጦታችን አገራችንን ወደነበረችበት መመለስ ነው። ፕሬዝዳንቱ የደቡብ ኮሪያን ምጣኔ ሃብት በማዳከሙ ሥልጣን ሊለቅ ይገባል" ብለዋል የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው።












