ሰሜን ኮሪያ ተደጋጋሚ የክሩዝ ሚሳኤል ሙከራ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰሜን ኮሪያ ተከታታይ የክሩዝ ሚሳኤል ሙከራ አደረገች።
ሚሳኤሎቹ ያረፉት ምሥራቃዊ ጠረፍ የዉሃ አካል ላይ ነው።
ከቅርብ ወራት ወዲህ ሰሜን ኮሪያ ተከታታይ የሚሳኤል ሙከራዎችን ማድረጓ በአካባቢው ውጥረት እንዲሰፍን አድርጓል።
ትናንት እሑድ የተተኮሱት ክሩዝ ሚሳኤሎች የተደረጉት ሲንፖ ወደብ አቅራቢያ ነው።
ምን ያህል ሚሳኤሎች ስለመተኮሳቸውም ሆነ የሚሳኤሎቹ ዓይነት በዝርዝር አልታወቀም።
ባለፈው ረቡዕ ሰሜን ኮሪያ ፑልዋሳል-3-31 የሚባል አዲስ ዓይነት ክሩዝ ሚሳኤል መተኮሷን ዮንሃፕ የተባለ የደቡብ ኮሪያ የዜና ወኪል ዘግቦ ነበር።
ይህን የክሩዝ ሚሳኤል ሙከራ ተከትሎ የደቡብ ኮሪያ ጦር ማስተባበሪያ ቢሮ “ጉዳዩን ከአጋራችን አሜሪካ ጋር በመሆን በቅርብ እየተከታተልነው ነው፤ ምናልባት ከሰሜን ኮሪያ የሚሰነዘር ተጨማሪ ጠብ አጫሪነት ካለ” ሲል አስታውቋል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በንግግርም በፖሊሲ አቅጣጫም ጠንከር ያለ አቋም እየወሰደኑ የመጡ ይመስላሉ።
ፒዯንግያንግ በቅርቡ አዲስ ዓይነት ሚሳኤል እየሞከረች እንደሆነ፣ በውሃ ሥር የሚሰግር ኒክሊየር ኃይልን መሸከም የሚያስችል አቅም ያለው ድሮን ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ወዲህ የመሞከር እቅድ እንዳለ አስታውቃለች።
ሰሜን ኮሪያ እንዲህ ዓይነት የጦር መሣሪያ ሙከራዎችን ከማምረትም ሆነ ከመጠቀም እንድትቆጠብ የተባበሩት መንግሥታት የጫነባት ማዕቀብ ቢኖርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ አዲስ የሚሳኤል ሙከራዎችን እያደረገች ጎረቤቷን ደቡብ ኮሪያንና የምዕራብ አገር አጋሮቿን ስጋት ላይ ጥላለች።
ባለፈው ወር መጀመርያ ኪም ጆንግ ኡን ከደቡብ ኮሪያ ጋር አንድ ቀን አንድ እንሆናለን የሚለውን ሐሳብ ጨርሶውኑ መሰረዙን ይፋ አድርገው ነበር።
ከዚህ ዕለት ወዲህ ደቡብ ኮሪያ የሰሜን ኮሪያ "ቀዳሚ ጠላት" ተደርጋ ተፈርጃለች።
ከዚያ ወዲህ ደግሞ ተከታታይ የሚሳኤል ሙከራዎች እየተደረጉ መጥተዋል።
ይህ ሁኔታ ምናልባት ሰሜን ኮሪያ ለጦርነት እየተዘጋጀች ይሆን? የሚል መላምት እንዲኖር ምክንያት ሆኗል።
የደቡን ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዩኦል ለካቢኔ አባሎቻቸው እንደተናገሩት ምናልባት ሰሜን ኮሪያ ጥቃት ከፈጸመች አገራቸው በብዙ እጥፍ ምላሽ ትሰጣለች።
“ይህን ለማድረግ ደግሞ ወደር የለሽ አቅም ገንብተናል” ብለዋል።












