የባይደን አስተዳደር አሜሪካ በትርምስ ከአፍጋኒስታን ለመውጣቷ ተጠያቂው ትራምፕ ናቸው አለ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ከአፍጋኒስታን ለመውጣት የነበረው ትርምስ የተፈጠረው በትራምፕ ምክንያት ነው ሲል የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ተጠያቂ አደረገ።

ዋይት ሃውስ አሜሪካ ከአፍጋኒስታን የወጣችበትን ሁኔታ እና ከአፍጋኒስታን ለመውጣት የተወሰዱ ውሳኔዎችን የሚያብራራ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

ሪፖርቱ ላይ የቀድሞው አስተዳደር ጦርነቱን ለማስቆም ከታሊባን ጋር የደረሰውን ስምምነት ጨምሮ በትራምፕ የተወሰዱት እርምጃዎች ባይደን ሊሰጡት የሚችሉትን ውሳኔ እንዲገደብ አድርጓል ይላል።

አሜሪካ እአአ 2021 ላይ በጥድፊያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት ያደረገችው ጥረት ትልቅ ትርምስን ፈጥሮ ነበር። በቀናት ውስጥ 120 ሺህ ሰዎችን ለማስወጣት በተደረገው ጥረት አየር ማረፊያ አቅራቢያ 13 የአሜሪካ ወታደሮች እና 200 የአፍጋኒስታን ዜጎች መገደላቸው ይታወሳል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ እና መከላከያ ቢሮው ከአፍጋኒስታን ለመውጣት የተወሰዱ ውሳኔዎችን መርምረው ሪፖርቱን ትናንት ሐሙስ ለኮንግረሱ ልከዋል።

ሪፓብሊካን ፖርቲ ተወካዮች ይህ ሪፖርት እንዲሰጣቸው ለሳምንታት ሲጠይቁ ቆይተዋል።

ዝርዝር ሪፖርቱ በሚስጥር የሚያዝ ቢሆንም የሪፖርቱ ጭምቅ ሃሳብ በዋይት ሃውስ አማካይነት ለሕዝብ ይፋ ሆኗል።

ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት የአፍጋኒስታን መንግሥት ወድቆ ታሊባን ግዛቱን እያስፋፋ ሲመጣ ከአፍጋኒስታን ለመውጣት በካቡል አየር ማረፊያ ትልቅ ትርምስ ተፈጥሮ ነበር።

በአየር ማረፊያው ላይ ሁለት አጥፍቶ ጠፊዎች ባደረሱት የቦምብ ጥቃት 170 የአፍጋኒስታን ዜጎች እና 13 የአሜሪካ ወታደሮች ተገድለዋል።

ከቀናት በኋላ አሜሪካ አጥፍቶ ጠፊን ዒላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት ማድረጓን የገለጸች ቢሆንም በጥቃቱ ግን ሕይወታቸውን ያጡት 7 ሕጻናትን ጨምሮ 10 ንጹሃን ሰዎች መሆናቸውን አምናለች።

የፕሬዝዳንት ባይደን የብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ በመጨረሻ ቀናት ትርምስ የተፈጠረው የትራምፕ አስተዳደር በአፍጋኒስታን የነበረውን ኦፕሬሽን እንዲዳከም በማድረጋቸው ነው ብለዋል።

ሪፖርቱ “ቸልተኝነት ነበረበት። ሆነ ተብሎ ትኩረት እንዳያገኝ ተደርጓል" ሲል የቀድሞው አስተዳደር የአፍጋኒስታን ፖሊሲን አጥብቆ ይተቻል።

ሪፖርቱ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከታሊባን ጋር በኳታር ስምምነት መድረሳቸውን፣ ተሰማርተው የነበሩ የአሜሪካ ወታደሮችን ቁጥር መቀነሳቸው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የታሊባን እስረኞችን ከእስር መልቀቃቸው እና የአፍጋኒስታን አጋሮችን ለመውሰድ የተዘረጋውን የቪዛ ፕሮግራም መሰረዛቸው ይተቻል።

ትራምፕ ይህ ሪፖርት ይፋ በሆነ በሰዓታት ልዩነት በዋይት ሃውስ ያሉ “አላዋቂ ሰዎች” አዲስ ሐሰተኛ መረጃ የመልቀቅ ጨዋታን ተያይዘዋል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ትራምፕ የባይደን አስተዳደር በብቃት ማነስ ምክንያት በአፍጋኒስታን እጅ ለመስጠት እኔ ተጠያቂ መሆን የለብኝም ብለዋል።

“ተጠያቂው ባይደን ነው፤ ሌላ ማንም አይደለም!” ብለዋል ትራምፕ።