ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕገ ወጥ የሚባሉት ቤቶች የትኞቹ ናቸው? ነዋሪዎችስ ምን መብት አላቸው?
አዲስ በተመሠረተው እና በኦሮሚያ ክልል ሥር በሚገኘው ሸገር ከተማ ተጠናክሮ በቀጠለው የቤት ፈረሳ፣ ነዋሪዎች ያላግባብ እና አድሏዊ በሆነ መልኩ ቤታቸው እየፈረሰባቸው እንደሆነ እየገለጹ ነው።
በሸገር ከተማ ሥር በሚገኙት ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ለገጣፎ፣ ለገዳዲ፣ ሱሉልታ ኤር ሞጆ፣ ገላን እና ሌሎች አካባቢዎች ቤታቸው የፈረሰባቸው ነዋሪዎች፣ በአድሏዊ ሁኔታ እና ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሕጋዊ የሆኑ ቤቶች ጭምር እንደፈረሰባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም የቤት ፈረሳው ሒደት ተገቢ ልየታ ያልተደረገበት፣ በቂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ያልተሰጠበት እና አድሏዊ ስለመሆኑም በሪፖርታቸው ላይ አመልክተዋል።
ነዋሪዎችን በግዳጅ በማስነሳት ሒደቱም የፀጥታ ኃይሎች በተጠቀሙት ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ የሰው ሕይወት ስለማለፉ፣ እንዲሁም ቤታቸው እንዳይፈርስ በተከላከሉ ነዋሪዎች እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ውጥረት ነዋሪዎች ለእንግልት፣ ለወከባ፣ ለእስር እና ለአካል እና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
ቢቢሲ የሸገር ከተማ ባለሥልጣናትን ለማነጋጋር ለቀናት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።
ይሁን እንጂ ባለሥልጣናቱ “ሕገ ወጥ” ያሏቸውን ቤቶች በስፋት እያፈረሱ እንደሆነ እና ፈረሳው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
ባለሥልጣናቱ እየፈረሱ ስላሉ ቤቶች በሰጡት መረጃ፣ የቤት ፈረሳው የአየር ካርታን ጨምሮ ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው፣ ከነባር የአርሶ አደር ይዞታ ውጪ የሆኑ እና በተለይም ከ2005 ዓ.ም በኋላ የተገነቡ ቤቶች እንዲፈርሱ የተላለፈውን ውሳኔ መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ቤታቸው የፈረሰባቸው ነዋሪዎች ግን የአየር ካርታን ጨምሮ ለአገልግሎት የከፈሉበት ሕጋዊ ደረሰኝ እንዲሁም ግዢ የፈፀሙበት ሰነድ ቢኖራቸውም ቤታቸው እንደፈረሰባቸው ገልጸዋል።
“የፈረሰው በሽፍታ ቢሆን አላዝንም ነበር”
በለገጣፎ ለገዳዲ አርባ አራት ማዞሪያ ላለፉት 15 ዓመታት እንደኖሩ ለቢቢሲ የገለጹት እና ለደኅንነታቸው ስንል ስማቸውን የማንጠቅሳቸው ነዋሪ፣ “ያለምንም የሕግ አግባብ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቤቴ ፈርሶብኛል” ብለዋል።
ነዋሪው በአካባቢው አሁንም መጠነ ሰፊ የቤት ፈረሳ ዘመቻ እየተካሄደ እንደሆነ እና በዚህም በርካታ ሰዎች ያለመኖሪያ ሜዳ ላይ ተበትነው እንደቀሩ ተናግረዋል።
በ2000 ዓ.ም ለአካባቢው ተወላጅ ወታደሮች የደም ካሳ ተብሎ 500 ካ.ሜ. መሬት እንደተሰጠ ያስታወሱት ነዋሪው፣ በዚያን ጊዜ ወታደሮቹ መሬታቸውን ሲሸጡ በሕጋዊ መንገድ የገዙ ሁሉ ቤታቸው ፈርሶባቸዋል።
“ወታደሮቹ አሁንም ካሉ አይፈርስም። ከእነርሱ የገዙት ግን ፈርሶባቸዋል” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
እርሳቸውም ከዓመታት በፊት ከገበሬ ላይ ገዝተው የሰሩት ቤት ፈርሶብኛል ይላሉ።
የሁለት ልጆች አባት የሆኑት እኚህ ነዋሪ፣ እግድ ለማውጣት ወደ ኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤት ቢያመሩም፣ መሬትን እና ቤትን በተመለከተ ምንም ዓይነት ፋይል እንደማይከፍቱ እና አቤቱታ እንደማይቀበሉ ተናግሯቸዋል።
ይህንን በተመለከተ በቢቢሲ የተጠየቀው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን ከዚህ ጋር በተገናኘ “ምንም መረጃ የለኝም” ብሏል።
ነዋሪው “ቤቴ ሲፈርስ ቅድመ ማስጠንቀቂያ አልተሰጠኝም። ከቤቴ ላይ የተነቀለውን ቆርቆሮም ወስደውታል” ሲሉም ይከሳሉ።
የ44 ማዞሪያ ከተማ መሥራች ነኝ የሚሉት ነዋሪው፣ ከሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉ የኦሮሞ ተዋላጆች እርዳታን ጨምሮ በአካባቢው የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ሲሳተፉ እንደቆዩም አክለዋል።
“ይህ የሆነው በሽፍታ ወይም በጠላት ቢሆን አላዝንም ነበር። በራሴ መንግሥት በመሆኑ ነው በጣም ያዘንኩት” ሲሉም የተፈጠረባቸውን ጥልቅ ምሬት ገልጸዋል።
ሌላኛው ስማቸውን የማንጠቅሳቸው የዚያው አካባቢ ነዋሪ እንደሚሉትም የክልሉ ፖሊስ፣ ሚሊሻ እና የአካባቢው ወጣቶች በተገኙበት እየተካሄደ ባለው ቤት የማፍረስ ሰፊ ዘመቻ በርካቶች ቤት አልባ ሆነዋል።
“በርካታ ቤት ነው የፈረሰው። እንዲፈርሱ የተለዩም ብዙ አሉ። ካርታ ያላቸውም፣ የሌላቸውም እየፈረሱ ነው። እቃቸውን ማጓጓዝ ያልቻሉት እና ጣሪያው በተነቀለ ቤታቸው ላይ ሸራ ወጥረው የተጠለሉትንም በግድ እያስወጧቸው ነው” ብለዋል።
ቤታቸውን በ2000 ዓ.ም በሕጋዊ ሰነድ እንደገዙት እና የአየር ካርታ እንዳለው የገለጹት ነዋሪው የመብራት፣ የውሃ እና የሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎችን ፈፅመው አገልግሎቱን ለማግኘት እየተጠባበቁ ባለበት ጊዜ ነው ቤታቸው የፈረሰባቸው።
ነዋሪው እንደሚሉት ቤታቸው ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ማለዳ 1፡30 አካባቢ ነው በድንገት የፈረሰባቸው።
“ባለቤቴ አራስ ናት። ወቅቱ ረመዳን ነው። ቤት ኪራይ እጅግ ከባድ ነው። የተመሳቀለ ሕይወት ውስጥ ነው የገባነው” ሲሉም አሁን ላይ ከባለቤታቸው ጋር ተነጣጥለው ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ዘመድ ጋ ተጠግተው እንደሚገኙ አስረድተዋል።
“ኢትዮጵያዊ እንዳልሆንኩ ነው የተሰማኝ። እየተለየ ነበር ቤት ሲፈርስ የነበረው። ኦሮምኛ ተናጋሪ የሆኑት ቤታቸው አይፈርስም ነበር። ባለቤቴ አረብ አገራት ለዓመታት በስደት ሰርታ ባጠራቀመችው፣ እኔም ለዓመታት በለፋሁበት ገንዘብ ነበር ያፈራነው። ቢሸጥ አራት ሚሊዮን ብር ገደማ ያወጣ ነበር። በ15 ደቂቃ አፈረሱት” ብለዋል።
በዚህም ልጆቻቸው ትምህርታቸውን እንዳቋረጡ፣ አዕምሯቸው እንደተረበሸ፣ ማኅበራዊ ሕይወታቸውም እንደተናጋ ገልጸዋል።
ኢሰመኮ ባደረገው ምልከታ ምን አገኘ?
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መጋቢት 22/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ቤቶች በፈረሱባቸው አካባቢዎች የመስክ ምልከታ ማድረጉን ገልጾ፣ በምልከታዬ አገኘኋቸው ያላቸውን ነጥቦች ይፋ አድርጓል። ከእነዚህም መካከል፡-
- የቤት ፈረሳው ተገቢ ልየታ ያልተደረገበት እና ያለበቂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ የተፈፀመ ነው።
- በአንዳንድ አካባቢዎች “ብሔር ተኮር” አድሏዊ እርምጃ አለ።
- ከ2005 ዓ.ም. በፊት የተገነቡ ቤቶችን በተመለከተ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ መሠረት፣ ወደ መደበኛ ግንባታ እንዲዘዋወሩ የሚያስችላቸውን መስፈርቶች ያሟሉ ቤቶችም ፈርሰዋል።
- እንዲፈርሱ ከተደረጉ ቤቶች ውስጥ መደበኛ ካርታ፣ የአየር ላይ ካርታ እና አረንጓዴ ደብተር ያላቸው እንዲሁም እንዳይፈርሱ የፍርድ ቤት እግድ ያለባቸው ቤቶች ይገኙበታል።
- በቤት ፈረሳው ሒደት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅመዋል።
ሕገ ወጥ የሚባለው ቤት የቱ ነው? የነዋሪዎች መብትስ ምን ድረስ ነው?
የሕግ ባለሙያው ታምራት ኪዳነማርያም እንደሚሉት በ1967 ዓ.ም. ሐምሌ 19 ከታወጀው አዋጅ በኋላ የከተማ ቦታ እና መሬት የመንግሥት ነው።
በዚህ ሕግ መሠረትም አንድ ቤት ሕገ ወጥ ነው የሚባለው ያለመንግሥት ምሪት በዘፈቀደ በተያዘ መሬት ላይ የተሰራ ከሆነ ነው። ይህም በተለምዶ የጨረቃ ቤት ይባላል።
መንግሥትም እነዚህ ቤቶች ላይ ወዲያውኑ እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን አለው።
ነገር ግን መንግሥት እርምጃ ሳይወስድ ቆይቶ፣ ቤቱ በመንግሥት ተመዝግቦ ግብር ሲከፈልበት ከቆየ በከፊል ሕጋዊ፣ በከፊል ሕግ ያላሟላ (ድብልቅ) እንደሚባል የሕግ ባለሙያው ያስረዳሉ።
ከዚያም መብራት እና ውሃ ሲገባለት፣ የስልክ መስመር ሲዘረጋለት እና ሕጋዊ በማድረግ ሒደት ውስጥ ካርታ ሲሰጠው ሕጋዊ ቤት ይሆናል።
ካርታው በመሠራት ላይ ያለ (ካዳስተር ቁጥር) የተሰጠው፣ ነገረ ግን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያልተሰጠው በከፊል ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ ለመሆን ብዙ ነገር ያሟላ ቤት ይባላል።
ታዲያ መንግሥት የማፍረስ ሥልጣን ያለው የትኛውን ቤት ነው?
አቶ ታምራት እንደሚሉት መንግሥት ሕገ ወጥ ብሎ ማፍረስ የሚችለው ያለ መንግሥት ምሪት በዘፈቀደ በተያዙ መሬቶች ላይ የተሰሩ፣ ብዙም ያልቆዩ እና ሕጋዊ ሒደት ውስጥ ያልገቡ ቤቶችን ነው።
መንግሥት ዝም ብሎ ከቆየ በኋላ ድንገት ተነስቶ ቤቶቹን ማፍረስ እና ውጡ ማለት ሕጋዊ መሠረት እንደሌለው አቶ ታምራት አስረድተዋል።
“ምንም ያላሟላ፣ ቀበሌም ያልመዘገበው፣ ካርታም የሌለው፣ የቤት ቁጥር ያልተሰጠው አዲስ ቤት ቢሆን እንኳ ለማፍረስ ሕጋዊ ሒደት አለው” ይላሉ ባለሙያው።
የመጀመሪያው ራሳቸው ባለቤቶቹ እንዲያፈርሱ ጊዜ መስጠት ነው።
በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ማፍረስ ካልቻሉ በመንግሥት ወጪ እንዲፈርስ ይደረጋል። ፍራሹም መንግሥት ጋር ይቀመጣል። ፍራሹ መንግሥት ጋር ቢቀመጥም ንብረትነቱ ግን የባለቤቶቹ ነው።
ስለዚህም ቤቱን ለማፍረስ የወጣውን የመንግሥትን የጉልበት ኪሳራ ከፍለው ንብረቱን አስለቅቀው መውሰድ ይችላሉ።
“አሁን ባለው ቤት ፈረሳ፣ ሕግ ያሟላል የተባለውንም ጭምር ማፍረስ እና ፍራሹንም መውሰድ አትችሉም ብሎ መከልከል በስፋት እየታየ ነው” የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ “ይህ ትልቅ ስህተት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው” ሲሉ ኮንነውታል።
ሕጋዊ ሰነድ ያላቸው ቤቶችስ?
አቶ ታምራት እንደሚሉት እነዚህን ቤቶች ለማፍረስ ምትክ ቦታ ማዘጋጀት ግዴታ እንደሆነ ሕጉ ያዛል።
“ሕጋዊ ሰነድ ያላቸው ቤቶች መንግሥት መዝግቧቸዋል። በመመዝገቡ መንግሥትም ኃላፊነት መውሰድ አለበት። ቤቱ ሕገ ወጥ ከሆነ መጀመሪያውኑ ማስፈረስ እና ማስቆም ሲገባው ሕጋዊ አድርጎ መዝግቦ ቆይቶ፣ ብድግ ብሎ ማፍረስ ተገቢ አይደለም” ይላሉ አቶ ታምራት።
በመሆኑም እነዚህን ቤቶች ወደ ሕጋዊ መንገድ ማምጣት ካልሆነ ደግሞ ካሳ ተሰጥቶ አሊያም እንደ ኮንዶሚኒየም ያሉ የመንግሥት ቤቶችን በመስጠት መስተናገድ እንዳለባቸው ይገልጻሉ።
ይህ ካልሆነስ?
የሕግ ባለሙያው እንደሚሉት ተበዳዮቹ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው ቀድመው በፍርድ ቤት ክስ መስርተው ፈረሳው እንዳይካሄድ አሳግደው መከራከር ይችላሉ።
“አሁን ላይ በሌሊት እና በድንገት እየሄዱ የሚያፈርሱት፣ ተበዳዮች ይህንን መብታቸውን እንዳይጠቀሙ ለማድረግ ይመስላል” የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ ይህም “አሰቃቂ፣ ትክክለኛ ያልሆነ፣ ሰብዓዊ መብትን የሚጻረር፣ ከሰው ልጅ የማይጠበቅና ሕገ ወጥ ድርጊት ነው” ሲሉ አውግዘውታል።
ቢሆንም ግን ተበዳዮች አሁንም መፍትሔ የመጠየቅ መብት እንዳላቸው የሕግ ባለሙያው ይጠቁማሉ።
በሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም፣ በሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንዲሁም በፓርላማ በተቋቋሙ ሕጋዊ አካላት አማካይነት ጉዳዩ እንዲጣራላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው።
ይህም ሆኖ መፍትሔ ካላገኙ ሌላ የሕግ አማራጭ እንዳለና የአፍሪካ ሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ድረስ ጉዳዩን በመውሰድ መጠየቅ እንደሚችሉ ባለሙያው ይመክራሉ።
“ይህ መንግሥትን እና አገርን ጭምር የሚያስከስስ ነው የሚሆነው” ያሉት ባለሙያው፤ እዚህ ላይ ሳይደርስ የሚመለከተው አካል ነገሩን አስተካክሎ ፈር ማስያዝ እንደሚገባው አሳስበዋል።