ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሐዋሳው የፀጋ በላቸው ጠለፋ የቀሰቀሰው ስጋት እና ጥያቄዎች
ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ እና በመደበኛ የመገናና ብዙኃን ዘንድ በስፋት መነጋገሪያ የነበረው የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆነችው የፀጋ በላቸው መጠለፍ እና ለቀናት የደረሰችበት አለመታወቁ ነበረ።
በርካቶች ምስሏን አጋርተዋል። “ፀጋ የት ናት? ፍትህ ለፀጋ” ሲሉ ጠይቀዋል።
ግንቦት 24/2015 ዓ.ም. ፀጋ ከአጋቿ ቁጥጥር ነጻ በመውጣት ወደ ሐዋሳ መመለሷን ቤተሰቧ እና የከተማው ፖሊስ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ቢቢሲ ይህንን ዘገባ እያጠናቀረ በነበረበት ጊዜ ፀጋ ነጻ ብትወጣም፣ እገታውን የፈጸመው ግለሰብ ግን አለመያዙ ተገልጿል።
ግንቦት 15/2015 ዓ.ም. የግል ተበዳይ ፀጋ በላቸው፤ ከሥራ ወጥታ ወደ ግል ጉዳይ በምታመራበት ወቅት አሮጌው መነኸሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጠለፋው እንደተፈፀመባት በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
ፀጋ መጠለፏ ከተሰማ በኋላ ፖሊስ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን፣ እንዲሁም በተለያየ መንገድ ትብብር አድርገዋል የተባሉ የጠላፊውን እናት ጨምሮ አስር ሰዎች፣ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ቢቢሲ ከከተማዋ የፖሊስ አዛዥ ሰምቷል።
ጠለፋ “በፍቅር ከተማዋ” ሐዋሳ
ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ በከተማዋ ነዋሪ እንደሆነ የሚናገረው እና ለደኅንነቱ ሲባል ስሙን የማንጠቅሰው አንድ ነዋሪ፣ ይህ የፀጋ ጉዳይ የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስለሳበ እንጂ ሌሎች ሴቶችም ተጠልፈው ተወስደው እንባቸውን የሚያብስላቸው ማጣታቸውን ይናገራል።
በሐዋሳ ኢንዱስትርያል ዞን ጀርባ፣ ዳቶ መስመር ወጣቶች በባጃጅ እና በሞተር በመሆን አንዲት የ12ኛ ክፍል ተማሪን በመከታተል ለመጥለፍ ሲሞክሩ፣ አብረዋት በነበሩ ተማሪዎች ርብርብ መትረፏን አውቃለሁ ሲልም ለቢቢሲ ተናግሯል።
አክሎም ተማሪዋ ትምህርቷን በአግባቡ መከታተል ስላቻለች አካባቢዋን ለመቀየር ተገድዳለች ይላል።
በቁጭት “በፊት እኮ አንዲህ አልነበረም” የሚለው ይህ ግለሰብ፣ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት አንዲህ ዓይነት ወንጀል እየጨመረ መምጣቱን ያስታውሳል።
“በክልሉ ከሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች በርካቶች ወደ ከተማዋ እየመጡ ነው። ከተማዋ መሀል ተከራይተው መኖር ስለሚከብዳቸው ወደ ዳርቻ አካባቢዎች መኖር ይመርጣሉ። ይህ ደግሞ አንዲህ ዓይነት ወንጀሎች እንዲበረክቱ ያደረገ ይመስለኛል” ሲል የግል ምልከታውን አጋርቷል።
ይኸው ነዋሪ፣ ተበዳዮች በሽምግልና ሰበብ ጩኽታቸው ተዳፍኖ ቀርቷል ይላል።
በፉላ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የነበሩ ሁለት ሴቶች አውቃለሁ የሚለው ነዋሪው፣ ተጠልፈው ከተወሰዱ በኋላ ጉዳያቸው በሽምግልና በመያዙ እና በመካከል እርግዝና በመፈጠሩ ያለፍላጎታቸው ትዳር ውስጥ ለመቆየት መምረጣቸውን ያክላል።
ወጣት እና ታዳጊ ሴቶች ከትምህርት ቤት፣ ከሥራ ቦታቸው፣ ድንገት ከመንገድ ላይ፣ ከቤተክርስቲያን በር ላይ ተጠለፉ ሲባል መስማት እየተለመደ መምጣቱን በመጥቀስ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው ይላል።
እየተበራከተ የመጣው ጠለፋ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብች ኮሚሽን ጥቅምት 17/2015 ዓ.ም. ጠለፋ እና ሌሎች ጥቃቶች በሐዋሳ ከተማ ዙሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸው ገልጾ መረጃ አጋርቶ ነበር።
ኮሚሽኑ አክሎም ከዚሁ ጋር በተያያዘ በፍርድ ቤት የሚሰጡ ውሳኔዎች እስከ መጨረሻ አለመፈጸማቸው እና የወንጀል ምርመራ ከተጀመረ እንዲሁም ክስ ከተመሠረተ በኋላ ሂደቱ ተቋርጦ ጉዳዩ በሽምግልና እንዲያልቅ መደረጉን መታዘቡን አስቀምጧል።
ኮሚሽኑ በሲዳማ ክልል 7 ወረዳዎች ከተውጣጡ የክልሉ ሴት የሕፃናት ፓርላማ ተወካዮች ጋር በወቅቱ ባደረገው ውይይት የአገር ሽማግሌዎች የጠለፋ እና ሌሎች ጎጂ ድርጊቶች ተፈጽመው ሲገኙ ጉዳዩ በባሕላዊ የዕርቅ ሥርዓት እንዲፈታ ከፍተኛ ግፊት ማድረጋቸው እና ጣልቃ መግባታቸው እንዲሁም የወንጀል ምርመራ ወይም ክስ እንዲቋረጥ በሚያደርጉ የሕግ አስፈጻሚ አካላት ላይ የሥነ-ምግባር እርምጃ እንዲወሰድ አለመደረጉ የበለጠ ወንጀሉን ለማበረታታት እንደ ክፍተት መታየቱን ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር የሐዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ የሆነችው ሠላማዊት ካሳዬ በበኩሏ “በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዲህ ዓይነት ነገሮች [ከጠለፋ ጋር የተያያዙ] እየበዙ ነው” ብላለች።
ቢቢሲ ያነጋገረውም ነዋሪ “ባለፉት ሦስት እና አራት ወራት ውስጥ ደግሞ ሐዋሳ ከተማ ላይ በቁጥር ብዙ የጠለፋ ወንጀል ተፈጽሟል” ሲልም ያስረዳል።
ቢቢሲ ከከተማው አስተዳደር አንዲሁም ከክልሉ ሴቶች ቢሮ ያጋጠሙ የጠለፋ መረጃዎችን እና ተያያዥ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
እንደ ፀጋ ያልተጮኸላቸው ጠለፋዎች
የሕግ ባለሙያዋ ሠላማዊት፣ ፀጋ ከመጠለፏ አስራ አምስት ቀን ቀደም ብሎ አንዲት የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ከዩኒቨርስቲው በር ላይ መጠለፏን ታስታውሳለች።
“ጉዳዩ የሚዲያ ሽፋን የማግኘት እና ያለማግኘት ጉዳይ ሆኖ ነው እንጂ በርካታ ሴቶች ተጠልፈው ወደ ትዳር እንዲገቡ ይደረጋል” ስትል በሥራዋ አጋጣሚ የገጠሟትን በመጥቀስ ታስረዳለች።
ለሠላማዊት በከተማዋ የሚፈጸሙ ጠለፋዎች ከባሕል ጋር ጠንካራ ቁርኝት አላቸው።
“ከሕግ በበለጠ. . .በንግግር፣ በእርቅ አልያም በማስፈራራት መፍታት የተለመደ ነው” በማለት
ይህ ደግሞ አጥቂውን በሽምግልና መጥቀም መሆኑን አጽንኦት ሰጥታ ታስረዳለች።
በከተማው ከሕግ ይልቅ “ለሽምግልና እና ለባሕላዊ እርቅ ዋጋ ይሰጣል” የምትለው ሠላማዊት፣ በዚህ መካከል ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች በጫና ምክንያት ሀሳባቸውን እንዲቀይሩ ወይንም መጀመሪያ የሰጡትን ቃል እንዲያጥፉ ይደረጋል ትላለች።
በዚህም የተነሳ “አሁን በተለይ አንዲህ ዓይነት ነገሮች [ጠለፋ] እየበዙ ነው ያሉት” ሰትል ታስረዳለች።
በሐዋሳ ከተማ የሴቶች፣ የህጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ምክትል ኃላፊ የሆነችው ቅድስት ደሜ በከተማው ጠለፋ “አልፎ አልፎ” እንደሚከሰት ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ወቅት ተናግራለች።
የእርሷ ቢሮም እንዲህ ዓይነት ነገሮች ተከስተው ሪፖርት ሲደረጉለት ክትትል እና ድጋፍ አድርጎ ለመፍታት እንደሚሰራ ታስረዳለች።
ባለፈው ዓመት የሐዋሳ ከተማ አመራር የነበረ ግለሰብ በጠለፋ ላይ ተሳትፎ በመገኘቱ ከሥልጣኑ እንዲነሳ ማድረጋቸውን እና በሕግ መጠየቁንም በአስረጅነት ታቀርባለች።
ሕግ ባለሙያዋ የጠለፋን ጉዳይ ከባድ የሚያደርገው የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የፀጥታ አካላት ሲሳተፉበት መሆኑን ትናገራለች።
ሽምግልና እና ዕርቅ በጠለፋ ውስጥ
ለሕግ ባለሙያ ሴቶች አስተባባሪዋ ሠላማዊት በከተማዋ በተደጋጋሚ ጠለፋ ለመፈፀሙ ምክንያት የሆነው፣ በርካቶች ከሕግ ተጠያቂነት ይልቅ በባሕላዊ መንገድ ነገሮችን ወደ መፍታት ማዘንበላቸው ነው።
“ጠለፋ የተፈጸመባቸው ሴቶች ጉዳይ በበቂ ሁኔታ ወደ ቢሯችን መጥቷል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም በሽምግልና፣ በቤተሰብ ስምምነት ልጅቷ ተጎድታም ተዳፍነው የሚቀሩ ብዙ ጠለፋዎች አሉ።”
ለቤተሰብም ገንዘብ በመስጠት አፍ የማዘጋት ሂደት መኖሩን ስታስረዳም “ልጅቷ ከማኅበረሰቡ እና ከቤተሰብ ጫና ሲበዛባት ጉዳዩ በእርቅ በሽምግልና እንዲፈታ ትፈልጋለች” ስትል ታክላለች።
“ተስማምታ ነው የሄደችው ብሎ ቤተሰብም የመሸፈን ነገር አለ . . . ሽማግሌዎች ደግሞ ባሕላችንን አታከብሩም፣ ከሽማግሌ በላይ ምንም ነገር የለም” የሚሉ ነገሮች ጠለፋ ለሚፈጽሙ ወንዶች የልብ ልብ ከሰጡ ነገሮች መካከል መሆናቸውነም ገልጻለች።
በሠላማዊት ሀሳብ የሚስማማው ላለፉት 14 ዓመታት በሐዋሳ በከተማ የኖረው ግለሰብ፣ የከተማዋ መስፋትን ተከትሎ የፀጥታ አካላት በሁሉም አካባቢዎች አለመዳረሳቸው ሌላው ምክንያት ነው ይላል።
አክሎም በሕግ አካላት ዘንድ ያለው “ቸልተኝነት” በዳዮች ጉዳዩን በአገር ሽማግሌ አንጨርሰዋለን ብለው መደምደማቸውን ጠቅሶ ያስረዳል።
ይህም የልጅቷ መብት መጣሱ፣ መበደሏን ሳይሆን ባሕሉን በመጠቀም አጥቂን ነጻ በማውጣት ላይ ያተኮረ ነው ስትል የነዋሪውን ሀሳብ የሕግ ባለሙያዋ ሠላማዊት ታጠናክራለች።
የከተማዋ የሴቶች ጉዳይ መምሪያ ምክትል ኃላፊ በበኩላቸው፣ ጠለፋን ለማስቀረት የእርሳቸው ቢሮ ከሌሎች ግብረ ኃይሎች ጋር በመሆን እንደሚሰራ ይናገራሉ።
ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ጠለፋው ግንዛቤ ባላቸው ሰዎችም ሲፈጸም መታየቱን እንደችግር በመጥቀስ “በደንብ መሥራት ያሉብን ነገሮች እንዳሉ ይታየናል” ብለዋል።
የሕግ ባለሙያዋም ሆኑ የከተማዋ ነዋሪ ሐዋሳ እንደሚነገርላት የፍቅር ከተማ ሆና እንድትቀጥል እንዲህ ዓይነት የሴቶችን መብት የሚጥሱ ድርጊቶችን በጋራ መታገል ይኖርባታል።
የሕግ አካላትም ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ከተጎጂ ጎን ያለማመንታት መቆም ይጠበቅባቸዋል ሲል ነዋሪው ሀሳቡን ያጠቃልላል።