ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“የተወለድኩት በመደፈር ቢሆንም ይህ የእኔ መገለጫ እንዲሆን አልፈቅድም”
“ውድ ታስ፣
አሁን ላይ የ10 ቀን ጨቅላ ሕጻን ነሽ፤ ምናልባት ይህንን ስታነቢ በዕድሜ ከፍ ብለሽ ይሆናል።
በጣም እወድሻለሁ!”
ይህ የታስኒም እናት በማስታወሻዋ ላይ ያሰፈረችው መልዕክት ነው።
ታስኒም የእናቷን ሉሲ ማስታወሻ ለመጀመሪያ ጊዜ ስታነብ ዐይኖቿ በእምባ ተሞልተው ነበር።
ታስኒም እናቷን ያጣችው ሕጻን ሳለች በደረሰ የእሳት አደጋ ነው።
እርሷ ከዚህ አደጋ ስለመትረፏ ይቅርና የእናቷ ማስታወሻ ስለመኖሩ የምታውቀው ነገር አልነበረም።
የዚያን ዕለት ምሽት ያጋጠመው አደጋ በጉልህ የሚታየው በታስኒም ጉንጭ ላይ ባለው ጠባሳ ብቻ ነው።
እሳቱ ሲነሳ የታስኒም አባት እርሷን አቅፎ ከወጣ በኋላ በብርድ ልብስ ጠቅልሎ በአትክልት ሥፍራው ከሚገኝ የአፕል ዛፍ ሥር አስቀመጣት። በዚህም ሕይወቷን መታደግ ቻለ።
ይሁን እንጂ ነዳጅ ቤቱ ላይ በማርከፍከፍ እሳቱን ያስነሳው እሱ እራሱ ነበር። ይህ የእሳት አደጋ ከእናቷ በተጨማሪ የታስኒምን አክስት እና ሴት አያቷን ገድሏል።
ታስኒም አባቷ የዕድሜ ልክ እስር የተፈረደበት ገዳይ እንደሆነ ታውቃለች።
ይሁን እንጂ በፖሊስ መዝገብ ውስጥ ተረስቶ የተቀመጠው የእናቷ የግል ማስታወሻ (ዲያሪ) ሌላ አስከፊ ምስጢር ይፋ አውጥቷል።
ታስኒም ለ18 ዓመታት በፖሊስ መዝገብ ውስጥ የተቀመጠውን ይህንን ማስታወሻ ያገኘችው የእናቷን ጉዳይ የተመለከቱ ማስረጃዎችን ለማየት ጥያቄ ካቀረበች በኋላ ነበር።
ታስኒም ማስታወሻውን ስታነበው፣ የተወለደችው አባቷ በእናቷ ላይ በፈፀመው ወሲባዊ ጥቃት ሳቢያ እንደሆነ ተረዳች።
ሉሲ በማስታወሻዋ ላይ ካሰፈረችው ተስፋ እና የወደፊት ህልሞቿ በተጨማሪ ያሳለፈችውን እንግልት እና መከራ በዝርዝር ጽፋለች።
ሉሲ ከ12 ዓመት ዕድሜዋ ጀምሮ በ10 ዓመት በሚበልጣት የታክሲ አሽከርካሪው የታስኒም አባት አዝሃር አሊ መሐመድ ወሲባዊ ጥቃት እና ብዝበዛ ተፈፅሞባታል።
የምታነበው እውነት ታስኒምን አቅም አሳጣት።
ምንም እንኳን ሌሎች ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ጥናቶች ቢያመልክቱም፣ በዓለም ላይ እንደዚህ ዓይነት በደል የደረሰባት ብቸኛዋ ሴት እንደሆነች ተሰማት።
በዩናይትድ ኪንግደም ምን ያህል ሰዎች በአስገድዶ መድፈር እና በወሲባዊ ጥቃት ሳቢያ እንደተወለዱ ማወቅ አዳጋች ነው።
ነገር ግን እንደ ዳራም ዩኒቨርሲቲ እና የሴቶች የፍትሕ ማዕከል ግምት፣ እንደ አውሮፓውያኑ 2021 ብቻ በኢንግላንድ እና በዌልስ 3300 የሚሆኑ ሴቶች በተፈፀመባቸው የመድፈር ጥቃት ሳቢያ አርግዘዋል።
ኢንግላንድ እና ዌልስን የሚያካትተው የጾታዊ ጥቃት ተጎጂዎች ረቂቅ ሕግ፣ በመድፈር ሳቢያ የተወለዱ ልጆች የወንጀል ተጠቂዎች መሆናቸውን እንደሚፈርጅ መንግሥት አስታውቋል።
እንደ ሚኒስትሮች ከሆነ በዚህ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ መካተታቸው የሥነ ልቦና ድጋፍ እና የምክር አገልግሎትን ጨምሮ ስለ ጉዳዮቻቸው መረጃ የማግኘት መብት እንዲኖራቸው ያደርጋል።
በተጨማሪም በአልኮል እና በአደንዛዥ ዕፅ ጥገኝነት፣ በትምህርት፣ በመኖሪያ ቤት ጥቅማጥቅሞች ዙሪያ ከሚሰጡ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ “እውቅና እንደሚሰጣቸውም” ቃል ገብተዋል።
ሆኖም በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የመድፈር ተጎጂዎችን ለመርዳት የተቋቋመ ምንም ዓይነት ግብረ ሰናይ ድርጅትም ሆነ የድጋፍ አገልግሎት የለም።
በመሆኑም እንደ ታስኒም ያሉ ተጎጂዎች እነዚህን ከባድ እና ውስብስብ ስሜቶች ያለ ምንም የባለሙያ እርዳታ እንዲያልፉ ተደርገዋል።
ታስኒም “ወላጆቼ በፍቅር ውስጥ እንደነበሩ ማሰብ እፈልጋለሁ” ትላለች።
“ይህ በትንሹም ቢሆን የማውቀውን ነገር ሁሉ ይለውጣል። ስለቤተሰብ እና እራሴን በተመለከተ ነገሮችን የምቀበልበትን መንገድ ይቀይራል። ምክንያቱም እኔ ከገዳይ እና ከደፋሪ ጋር ዝምድና አለኝ። በጣም የሚያስፈሩ ነገሮችን አስብ ነበር፤ ሳድግ እንደ እሱ ብሆንስ እያልኩ” ትላለች ታስኒም።
ለታስኒም የተወሰኑ የእናቷን ማስታወሻ ክፍሎች ማንበብ የሚያሳምሙ ነበሩ።
በዚህም እናቷ በማስታወሻዋ ላይ በግልጽ ባሰፈረችው እና ለእርሷ ያላትን ፍቅር በገለጸችበት ላይ ትኩረት ለማድረግ ትሞክር ነበር።
የማስታወሻው ገጾች በግጥም እና አብረው ባሳለፏቸው ታሪኮች የተሞሉ ናቸው።
“ስለራሴ መጥፎ ሊሰማኝ አይገባም። ምክንያቱም እናቴ ያንን አትፈልግም” ትላለች ታስኒም።
ኒል በረጅሙ ተንፍሶ የያዘውን ፖስታ ከፈተው።
በዌስት ዮርክሻየር፣ ኢልክሊ ውስጥ በጉዲፈቻ ያደገው ኒል፣ ልጅነቱ በደስታ የተሞላ ነበር።
ነገር ግን ሁልጊዜም ስለወላጅ እናቱ ለማወቅ ይጓጉ ነበር።
አንድ ቀን እንደሚገናኙም ህልም ነበረው።
የ27 ዓመቱ ኒል፣ እናቱን ለመፈለግ ከተቀጠረው የግል መርማሪ የተቀበለውን ደብዳቤ ከፈተው።
ደብዳቤውን ሲያነበው ሰማይ ምድሩ የዞረበት ያህል ነበር የተሰማው።
የኒል እናት በአስራዎቹ እድሜ ላይ ሳለች በፓርክ ውስጥ በማይታወቅ ሰው ተደፍራለች። ኒልም የተወለደው በዚሁ አጋጣሚ በተከሰተ እርግዝና ነው።
“ይህንን ለመስማት ቀድሞ የሚያዘጋጅ ምንም ዓይነት ቃል የለም” ይላሉ።
በጥቃት፣ በጥላቻ በተሞላበት ስሜት በተፈጠረ ግንኙነት መጸነሱን ሲያውቅ፣ የሆነ ሰው ደረቴን የደሰቀኝ ያህል ነበር የተሰማኝ ብሏል።
ኒል ጨምሮም “እፍረት፣ ሐዘን፣ ግራ መጋባት፣ ስለራስህ ጨለማ የሆነ የሚያስጣላ ስሜት ውስጥ መግባት ይፈጠራል። መንፈሴን ሰብሮታል” ሲል ተናግሯል።
ኒል ስለራሱ ያስብ የነበረው ነገር በሙሉ ጠፍቷል።
የማያውቀው እና በእናቱ ላይ ጥቃት የፈፀመው ግለሰብ የሚመለከተው ስለሚመስለው መስታወት ፊት መቆም አይችልም።
በጥቃት ሳቢያ መወለድ ምን ማለት ነው? ፍቅር የለም ማለት ነው? የኒል ወላጅ እናትስ ለመገናኘት ፈቃደኛ ትሆን ይሆን?
ታስኒም ከባዱ የእስር ቤት በር ከጀርባዋ ሲዘጋ ልቧ ድው፣ ድው ሲል ተሰማት። የእስር ቤቱ ጠባቂ እየመራት ወደ ጠባብ እና ቀዝቃዛ ክፍል ወሰዳት። አንድ ጠረጴዛ እና ሁለት ወንበሮች ተዘጋጅተዋል።
በሌላ በኩል ያለው በር ተከፈተ። ታስኒም ለመጀመሪያ ጊዜ አባቷን አየችው።
ግራጫ ቀለም ያለው የእስር ቤት ቱታ ለብሷል። ካሰበችው በላይ አጭር ነው።
በቁመት አጭር ቢሆንም ግርማ ሞገስ አለው። አቀፋት። ‘ቀኑን ለማክበር’ ቸኮሌት ኬክ ገዝቶ ነበር።
ታስኒም ግን የምትፈልገው ይህንን አልነበረም።
እርሱ የፈፀመው ነገር ያደረሰውን ተፅዕኖ እንዲረዳ ነበር ፍላጎቷ። እናቷን የበደለ እና በቁጥጥር ሥር አድርጎ ጥቃት የፈፀመውን ግለሰብ ተመለከተችው።
ታስኒም ቃል ሳትተነፍስ እስር ቤቱን ጥላ ወጣች። ከዚያ በኋላ ተመልሳ ወደዚያ ሄዳ አታውቅም። አሁን ላይ የምትፈልገውን መልስ ሁሉ አግኝታለች።
ኒል ለመጀመሪያ ጊዜ ወላጅ እናቱን ለማግኘት ከባቡር ጣቢያ ውጭ እየተጠባበቀ ነው። ኒል ሆዱ እርብሽብሽ ብሎበታል። ይህንን አጋጣሚ ብዙ ጊዜ አስቦበታል። ምን ማለት እና ማድረግ እንዳለበት ያሰላስላል።
ልክ እናቱ እንደመጣች ኒል እናቱ እንደሆነች ለማወቅ ጊዜ አልወሰደበትም።
ሁለቱም ዐይን ለዐይን ተያዩ። ኒል ከእርሷ ወገን እንደሆነ ነበር የተሰማው “አንቺን የደፈረሽን ሰው የምመስል ቢሆን ኖሮ፣ አሁኑኑ ነበር የምሄደው” አላት።
“አታደርገውም” አለች እናቱ። ኒል እናቱ እንዲህ ስትለው ከትከሻው ላይ አንድ ሸክም ሲወርድለት ይታወቀው ነበር።
እናት እና ልጅ የሆድ የሆዳቸውን ተጫወቱ። የሕይወት ታሪካቸውን አብረው እየተራመዱ አወሩ። ስለቤተሰብ፣ ኒል እንዳሉት ስለማያውቃቸው የእናቱ ልጆች አወሩ።
ሁለቱም ተመሳሳይ ሳቅ፣ ተመሳሳይ ገጽታ እና አገላለጽ አላቸው።
ኒል እሱ በተጸነሰበት ምሽት ስለሆነው ነገር አልጠየቀም። ማወቅም አልፈለገም።
እናቱ እንደገና በዚያ ስሜት ውስጥ እንድታልፍ አልፈለገም። ኒል ወላጅ አባት እንደሌለው ነው የሚያስበው። “ወላጅ እናት አለችኝ። ያ ደግሞ በቂ ነው” ይላል።
“ማም፣ እኔ የመደፈር ውጤት ነኝ?” የሳሚይ ልጅ የሰነዘረው ጥያቄ ነበር።
ሳሚይ በመኪና ውስጥ ከጎኗ የተቀመጠውን ታላቅ ልጇን ዞራ ተመለከተችው።
ሳሚይ ልጇን ከዚህ ዓይነት ስሜት ለመጠበቅ ልትረዳው ትፈልጋለች። ነገር ግን እንዴት መርዳት እንዳለባት አታውቅም።
“አይደለም። አንተ የእኔ ልጅ ነህ!” አለችው።
ሳሚይ ለ12 ዓመቱ ልጇ ምን እንደተፈጠረ እና እርሱ አባቴ እያለ ከሚጠራው ግለሰብ እንዴት እንደተጸነሰ እውነቱን ያስረዳችው በቅርቡ ነው።
አርሺድ ሁሴን ከ14 ዓመቷ ጀምሮ ሲደፍራት ነበር። ግንኙነት ውስጥ እንደሆኑ ያሳምናት ነበር። የ24 ዓመት እድሜ የነበረው ሁሴን፣ በሌሎች ሴቶችም ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ይፈፅም ነበር።
ከዚያ ግን ሳሚይ ከእርሱ ቁጥጥሩ ውጭ ወጣች። በወቅቱ ግን ራሷን እና በሳውዝ ዮርክሻየር፣ ሮተርሃም ውስጥ ወሲባዊ ብዝበዛ የተፈፀመባቸው ከ1 ሺህ በላይ ሕጻናትን ለመጠበቅ የሚያስችል አገልግሎት እንዳልነበር ትናገራለች።
ሁሴን በፖሊስ ምርመራ እየተካሄደበት ነበር።
የሳሚይ ልጅ ዘረ መልም በእሱ ላይ የቀረቡት ማስረጃዎች አካል ነው።
ሆኖም ልጇ በዚህ ስሜት ምን ያህል እንደተጎዳ ማየት ችላለች። ሁሉንም ነገር ይጠይቃል። ይፈለግ ነበር? ይወደድ ነበር? ይጠይቃል።
ጉዳዩ የብሔራዊ የዜና አውታሮች መነጋገሪያም ሆኗል። ሕዝብ ያውቀዋል። በእነርሱ ላይ ብቻ የሆነ እንደሆነ ይሰማቸዋል።
ሳሚይ የምትችለውን ያህል ጥሩ እናት ለመሆን ትሞክራለች፤ ግን ሁሉም ነገር የእርሷ ጥፋት እንደሆነ ነው የሚሰማት።
ልጇን ብትወደውም ከእርሷ ውጭ የተሻለ እንደሚሆን ታስባለች።
ልክ እንደ ታስኒም እና ኒል ሁሉ ሳሚይም ለዓመታት በምን ስሜት ውስጥ እንዳለች ማንም ሰው ሳያውቅ ብቻዋን ታግላለች።
ስለደረሰባት ነገር በነጻነት በትክክል ሊረዳት ለሚችል ሰው ማውራት የቻለችው በ2021 ማንዲ የተባለች ሌላ እናት ስታገኝ ነበር።
አሁን ላይ ሁሴን የ35 ዓመት እስር ተፈርዶበት በእስር ላይ ይገኛል።
ሳሚይ ከማንዲ ኩሽና ውስጥ ተቀምጣለች።
ማንዲ ታሪኳን ለሳሚይ አጫወተቻት። 30 ዓመታት ቢነጉዱም አሁንም የሚያሳምም ታሪክ ነው።
ማንዲ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቃት የተፈፀመባት የ11 ዓመት ታዳጊ ሳለች ነበር። በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ክብር የሚሰጠው ፖሊስ እና የጦር አባል ልብሱን አወላልቆ ከእርሷ ጋር ወደ መታጠቢያ ቤት ገባ።
ከዚያን በኋላ የሚፈፅምባት ጥቃት በእያንዳንዱ ቀን ምሽት ሆነ። እያደባ መኝታ ቤቷ ውስጥ ይገባል።
ማንዲ ይህንን ለማንም ደፍራ አልተናገረችም። ያስፈራራት ስለነበር ወጥመድ ውስጥ እንደገባች ነበር የሚሰማት።
አንድ ቀን ነፍሰ ጡር እንደሆነች አወቀች።
“መርዝ የተወጋሁ ያህል ነበር የተሰማኝ። አባቴ በእኔ ላይ ያደረገው ይህ ነው። የራሳችንን ዘር መልሶ ለእኔ አወረሰኝ” ስትል ለሳሚይ ነገረቻት።
ምንም ማድረግ እንደነበረባት አላወቀችም። አባቷ ምን እንደተፈጠረ ባወቀ ጊዜ ማንዲ ልጁን ከመውለድ ውጭ ሌላ ምርጫ አልነበራትም።
ስትወልድ አባቷ ማዋለጃ ክፍል ውስጥ ነበር። አዋላጅ ነርሷ አዲስ የተወለደውን ልጁን ሰጠችው።
“ልጄን መጀመሪያ ማቀፉ ይበልጥ ስሜቴን ሰበረው። ‘እጅህን ከእርሱ ላይ አንሳ’፣ ‘ዞር በል’ እያልኩ እያሰብኩ ነበር” ትላለች።
“የእኔ ልጅ ነው፣ ውድ ነው፣ እስከ መጨረሻው እጠብቀዋለሁ” ትላለች ማንዲ።
ከዚያም ማንዲ ልጇን ለማቀፍ ዕድል ስታገኝ የሕጻን ንጽህና መጠበቂያ እና ወተት በሕጻን ጋሪው ላይ አስቀምጣ ወጣች። ከዚያ በኋላ አልተመለሰችም።
ልጆችን በጥቃት በመውለድ እና በደስተኛ ግንኙነት ውስጥ በመውለድ መካከል ልዩነት አለው ብላ ታስብ እንደሆነ ሳሚይ ማንዲን ጠየቀቻት።
“አዎ! ከፍቅር ውጭ የተጸነሰ ነው፣ ከእኔ ፍቅር ውጭ የተፈጠረ ነው። ግን እወደዋለሁ” አለች ማንዲ።
የማንዲ ልጅ በባለቤቷ ፔቴ እጅ እያደገ ነው። ከሌሎች ልጆቻቸው ጋር ሆነው አብረው እየኖሩ ነው።
ምንም እንኳን ማንዲ የአባቷን ጥቃት ማምለጥ ብትችልም፣ መዘዙን ግን ማምለጥ አልቻለችም። ልጇ በዘር በሚመጣ ችግር የአካል ጉዳት ገጥሞታል።
ላለፉት 30 ዓመታት እስካሁን ድረስ በቀን 24 ሰዓት እርሱን እየተንከባከበች ነው የምታሳልፈው።
በእናቱ ላይ በተፈፀመባት ጥቃት እንደተወለደ የመረዳት አቅም የለውም። ማንዲ ይህንን ማስረዳት ስለማይጠበቅባት ደስተኛ ናት። ግን ሕይወታቸው ላይ የማይሽር ጠባሳ ጥሏል።
“ሁልጊዜም ‘እኔ ተርፌያለሁ። ልጄ ግን ተጎጂ ነው’ እላለሁ።”
"በዚህ ሁኔታ እንዲወለድ አልጠየቀም። እኔ ላይ የተፈፀመው ወንጀል በእርሱም ላይ ደረሰ” ትላለች።
ማንዲ እና ሳሚይ እስከሚተዋወቁ ድረስ ሁለቱም ብቻቸውን ያሉ ይመስላቸው ነበር።
“ማንዲ ያሳየችኝ ምንም ሁኔታ ውስጥ ብናልፍ ወደፊት መቀጠል እና ደስተኛ መሆን እንደሚቻል ነው” ትላለች ሳሚይ።
ሰዎች መነጋገር አለባቸው ስትልም ትመክራለች።
የመብት ተሟጋቾች ጉዳዩ ትኩረት እየተሰጠው ነው ይላሉ።
እንደ አውሮፓውያኑ በ1970ዎቹ በመደፈር በተወለደው አክቲቪሲት ደሲ ስም የተሰየመውና ‘የደሲ ሕግ’ ላይ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የተጎጂዎች ሕግ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ታቅዷል።
ለኒል እና ታስኒም፣ የታቀደው የሕግ ማሻሻያ እንደ እነሱ ያሉ ተጎጂዎች ድምጽ በመጨረሻም ለመሰማቱ እውቅና የሰጠ ነው። ሌሎች በመደፈር የተጸነሱ ሕጻናት ብቻቸውን እንዳልሆኑ እንደሚያሳይም ተስፋ ያደርጋሉ።
“ብዙ መገለል አለ። ግን ሊኖር አይገባም” የምትለው ታስኒም፣ “የምዛመደው ሰው ሳይሆን፣ እኔ የራሴ ሰው ነኝ። ደግሞም የእኔ ጥፋት አይደለም። በዚያ የተጎዳሁ እንጂ” ብላለች።
ታስኒም ስለሆነው በግልጽ መናገሯ የእናቷን ማስታወሻ ሕያው የምታደርግበት መንገድ ነው። ታሪካቸው አሳዛኝ ሆኖ እንደማይደመደምም ታምናለች።
“እናቴን ማናገር ብችል ምን ያህል ጀግና ሴት እንደነበረች እነግራት ነበር፤ እናም ሁሉ ነገር ሰላም መሆኑን፣ እኔም ደህና መሆኔን” ብላለች ታስኒም።