ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቴን ሃግ ዩናይትዶች እንደሚፈልጉኝ የነገሩኝ ለሽርሽር የሄድኩበት ድረስ መጥተው ነው አሉ
አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ማንቸስተር ዩናይትዶች እንደሚፈልጉኝ የነገሩኝ ለሽርሽር የሄድኩበት አይቢዛ ድረስ መጥተው ነው አሉ።
አሰልጣኙ ኖስ ለተባለ የኔዘርላንድስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ ለሽርሽር በሄዱበት አይቢዛ ደሴት ድንገት የቡድኑ ኃላፊዎች መጥተው ለስራው እንደሚፈልጉኝ ነግረውኛል ብለዋል።
“የክለቡ አስተዳዳሪዎች ለሽርሽር በሄድኩበት አይቢዛ መጥተው አግኝተውኛል። . . . ድንገት ካረፍኩበት ቦታ በር ላይ መጥተው ከእኔ ጋር አብረው መቆየት እንደሚፈልጉ ነገሩኝ” ሲሉ አሰልጣኙ ተናግረዋል።
ዩናይትድ በተጠናቀቀው የፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዓመት በታሪኩ ዝቅተኛ በሆነ 8ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል።
የክለቡ ቦርድ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት ከገመገመ በኋላ እና የክለቡ የድርሻ ባለቤት የሆኑት ሰር ጂም ራትክሊፍ ከቀድሞው የባየርን ሙኒክ አሰልጣኝ ቶማስ ቱህል ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ኤሪክ ቴን ሃግ በስራቸው እንዲቆዩ መደረጉ ተገልጿል።
“ማንችስተር ዩናይትድ ከቱህል ጋር መነጋገራቸውን ነግረውኛል። በመጨረሻ ግን ምርጡ አሰልጣኝ እንዳላቸው ከድምዳሜ ደርሰዋል” ሲሉ ቴን ሃግ ጨምረው ተናግረዋል።
የዩናትድ አዲሱ አስተዳደር ለእግር ኳስ አዲስ መሆናቸውን ግልጽ ነው ያሉት ቴን ሃግ፤ ያለፈውን የውድድር ዓመት ገምግመው ያላቸውን ሌሎች ዕጩ አሰልጣኞችንም ከግምት አስገብተው ነበር ብለዋል።
በውጤት ቀውስ ውስጥ ዩናይትድን ሲመሩ የቆዩት አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ በቀጣይ የውድድር ዓመት ከቡድኑ ጋር ሊለያዩ እንደሚችሉ በስፋት ሲገብ ቢቆይም ከጥቂት ቀናት በፊት አሰልጣኙ በዩናይትድ ቤት እንዲቆዩ ከስምምነት መደረሱ ይታወሳል።
ኤሪክ ቴን ሃግ ያለፈው ዓመት የፕሪሚር ሊግ ውድድር ተጠናቆ በኤፍኤ ዋንጫ ግጥሚያ ቡድኑን እየመሩ የሚያደርጉት የመጨረሻ ጨዋታቸው እንደሚሆን ተጠብቆ ነበር።
ይሁን እንጂ ቀያይ ሴጣኖቹ በዌምብሌ ስታዲየም ሲቲን 2-1 በማሸነፍ የኤፍኤ ዋንጫ ማንሳታቸው ቦርዱ የቴን ሃግ የውድድር ዓመትን በአዎንታዊ እንዲመለከተው እንዳደረገው ተገልጿል።
ቴን ሃግ አሁን ላይ የክለቡ ቦርድ ድጋፍ እንዳላቸው እርግጥ ቢሆንም እስካሁን ግን ውል አለመፈረማቸው ተገልጿል።
“እኔ እና ማንቸስተር ዩናይትድ አዲስ ውል መፈራረም ይኖርብናል። ይህ በቀላሉ የሚሆን አይደለም። በዚህ ዙሪያ ገና ብዙ ንግግር ማድረግ ይኖርብናል” ብለዋል።