ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዓለም ዙሪያ በርካቶች ከዜና ሲርቁ፣ ወጣቶች ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ እያተኮሩ ነው - ጥናት
በመላው ዓለም የተደረገ ጥናት በርካታ ሕዝብ የሚቀርቡ ዜናዎች የሚደብቱ፣ የማያቋርጡ እና አሰልቺ ናቸው በማለት እራሱን ከዜና እያራቀ መሆኑን አመለከተ።
እየተስፋፉ ያሉት የማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር መድረኮች ደግሞ ወጣቶችን በመሳብ፣ በርካቶች ፊታቸውን ቲክቶክን ወደ መሳሰሉ የቪዲዮ ማጋሪያ መድረኮች እያዞሩ መሆኑን ጥናቱ ጠቅሷል።
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ካለው ሕዝብ ከአስሩ አራት የሚሆኑት (39%) አንዳንድ ጊዜ ወይም በብዛት ሆን ብለው እራሳቸውን ከዜና ያርቃሉ። ይህ አሃዝ ከሰባት ዓመት በፊት ከነበረው በአስር በመቶ መጨመሩን የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲው የሮይተርስ ኢኒስቲቲዩት ጥናት ጠቁሟል።
የጥናቱ አዘጋጆች እንዳሉት በዩክሬን እና በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄዱት ያሉት ጦርነቶች ሰዎች ፊታቸውን ከዜና እንዲያዞሩ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
ጥናቱ ጨምሮም ከዜና እራሳቸውን የሚያርቁት ሰዎች መጠን ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ነው።
ለዚህ ዓመት ‘ዲጂታል ኒውስ ሪፖርት’ ለተባለው ጥናት ባለፈው ጥር እና የካቲት ወር ላይ በ47 አገራት ውስጥ የሚገኙ በአጠቃላይ ለ94,943 አዋቂዎች መጠይቅ ቀርቦላቸው ነው ይህ ውጤት የተገኘው።
በጥናቱ በበርካታ አገራት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ድምጽ ለመስጠት በምርጫ የሚሳተፉ ሲሆን፣ አሜሪካንን ጨምሮ በተወሰኑ አገራት ምርጫዎች ሰዎች ለዜና ያላቸውን ፍላጎት እንዲጨምሩ እንደሚያደርግ ጠቅሷል።
ቢሆንም ግን በአጠቃላይ ያለው ዝንባሌ በከፍተኛ ሁኔታ የመቀነስ አዝማሚያን እያሳየ መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል።
በአውሮፓውያኑ 2017 በዓለም ዙሪያ ካለው ሕዝብ 63% የሚሆኑት በጣም ወይም በከፍተኛ ደረጃ ዜና የመከታተል ፍላጎት ነበረው፤ አሁን ግን ይህ አሃዝ ወደ 46% ወርዷል።
የጥናቱ መሪ የሆኑት ኒክ ኒውማን ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ዜናዎች የሚያተኩሩት በወረርሽኝ እና በጦርነቶች ላይ ነበር፤ ሰው ደግሞ በተፈጥሮው ለአእምሮ ጤናው ሲል ወይም ሌሎች ጉዳዮቹ ላይ ለማተኮር ከዜና ፊቱን ያዞራል” ብለዋል።
ጥናቱ በተለይ ሴቶች እና ወጣቶች በሚቀርቡት የዜናዎች ብዛት የመሰላቸት ሁኔታቸው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዜና ላይ ያለው ዕምነት በአራት በመቶ ቢቀንስም ብዙም አልተሸረሸረም። በአሁኑ ጊዜ ዜና ከሚከታተለው ሕዝብ 40 በመቶው ዕምነት እንዳለው ሲሆን፣ በኮቪድ ጊዜ በዜና ላይ የነበረው መተማመን እጅግ ከፍተኛ ነበር ብሏል።
በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ቢቢሲ ታማኝነት ካላቸው የዜና ተቋማት መካከል ቀዳሚው ሲሆን፣ ቻናል4 እና አይቲቪ ይከተሉታል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ድርሻ
ወጣቶች ዜና ከኢንተርኔት እና ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ማግኘትን ስለሚመርጡ፣ ቀደምት የሚባሉት ቴሌቪዥን እና የህትመት መገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚዎች ቁጥር ባለፉት አስር ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ጥናቱ አመልክቷል።
ከማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መድረኮች መካከል ዜናዎችን በማቅረብ በኩል ምንም እንኳን በተከታታይ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም ፌስቡክ ቀዳሚ ነው።
ኤክስን (ትዊተር) ቀድሞ የበላይ የሆነው ቲክቶክ ተደራሽነቱ እየጨመረ ሲሆን፣ ዩቲዩብ እና ዋትስኣፕ ለበርካቶች የዜና ምንጭ በመሆን ተፈላጊ ናቸው።
አስር በመቶ ከሚሆኑት የኤክስ ተጠቃሚዎች ጋር ሲነጻጸር 13% የሚሆኑ ሰዎች የቪዲዮ ማጋሪያ መተግበሪያን ዜና ለማግኘት ይጠቀሙበታል።
የቲክቶክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ደግሞ ከዚህም ከፍ ያለው ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ 23% ከ18 አስከ 24 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች ቲክቶክን እየተጠቀሙ ነው።
ከዚህ አንጻርም በአሁኑ ወቅት በበይነ መረብ ላይ ለሚቀርቡ ዜናዎች በተለይም ለወጣቶች ቪዲዮዎች ዋነኛ የዜና ምንጮች ናቸው።
ጥናቱ እንዳለው አጭር የዜና ቪዲዮዎች በታዳሚው ዘንድ በስፋት ተመራጭ ሲሆኑ፣ ምንም እንኳን ውስን እና የተማሩ ታዳሚዎች ላይ የሚያተኩሩ ቢሆኑም የዜና ፖድካስቶች ደግሞ የማደግ ተስፋ እንዳላቸው ጠቁሟል።
የጥናቱ ተሳታፊዎች ከዜና አንጻር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ላይ ስጋት እና ጥርጣሬ እንዳላቸው አንስቷል።
ጦርነት እና ፖለቲካን ከመሳሰሉ ጠንካራ ዜናዎች ጋር በተያያዘ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሠራሽ ልህቀት) ዘገባዎችን ለማዘጋጀት ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ የሚል ሰፊ ጥርጣሬ እንዳለ ገልጿል።