ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩቲዩብ ተመልካች ለማግኘት ሆነ ብሎ አውሮፕላን የከሰከሰው ዩቲዩበር ተፈረደበት
አሜሪካዊው ዩቲዩበር የተመልካች ቁጥር ለማግኘት ሲል ሆነ ብሎ አውሮፕላን በመከስከሱ እና የአደጋ መርማሪዎችን በመዋሸቱ በስድስት ወራት እስር እንዲቀጣ ተፈረደበት።
የ30 ዓመቱ ትሬቨር ጄኮብ አውሮፕላኑ በአደጋ ምክንያት የተከሰከሰ የሚያስመስውን ተንቀሳቃሽ ምስል ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር ዩቲዩብ ላይ የጫነው።
ይህ ቪዲዮ በጉግል ከዩቲዩብ ገጽ እንዲሰረዝ ከመደረጉ በፊት ከሦስት ሚሊዮን ጊዜ በላይ ተመልካችን ለማግኘት ችሎ ነበር።
ጥፋቱን ለማመን ከዐቃቤ ሕግ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ግለሰቡ ቪዲዮውን የቀረጸው አንድ ምርትን ለማስተዋወቅ በደረሰው ስምምነት ምክንያት መሆኑን አመልክቷል።
የቀድሞ የኦሊምፒክ ተሳታፊ የሆነው ትሬቨር ጄኮብ ንብረት በማውደም እና ከፌደራል መርማሪዎች መረጃ በመሰወር ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን ከአንድ ዓመት በፊት አምኖ ነበር።
በካሊፎርኒያ ያሉ መርማሪዎች ጄኮብ ይህን ጥፋት የፈጸመው የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮችን ቁጥር በመጨመር እና እራሱን የዜና ማዕከል በማድረግ የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ነው ብለዋል።
የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ጄኮብ ባወጣው መግለጫ የተላለፈበት ፍርድ “ትክክለኛ ውሳኔ ነው” በማለት በቅጣቱ እንደሚስማማ ገልጿል።
ግለሰቡ ከሁለት ዓመት በፊት ከካሊፎርኒያ ሳንታ ባርባራ አየር ማረፊያ ብቻውን በሚያበራት አውሮፕላን ላይ ካሜራዎችን ገጥሞ የተነሳ ሲሆን፣ ካሜራዎችን ይዞ አውሮፕላኗ አየር ላይ እንዳለች በፓራሹት ዘሎ በመውረድ ስትከሰከስ የሚያሳየውን አጠቃላይ ሂደት ቀርጿል።
አውሮፕላኗ ለበረራ ከተነሳች ከ35 ደቂቃዎች በኋላ ሎስ ፓድሬስ በተባለ ደን ውስጥ ነበር ወድቃ የተከሰከሰችው።
“ቀድሞም ቢሆን ከአንድ መዳረሻ ላይ የማረፍ ዕቅድ አልነበረውም። የነበረው ዕቅድ በፓራሹት ከአውሮፕላኑ ዘሎ ሲወርድ እና አውሮፕላኑ ቁልቁል ሄዶ ሲከሰከስ መቅረጽ ነበር” ብሏል የካሊፎርኒያ ዐቃቤ ሕግ።
ከዚያም የኪስ ቦርሳ የሚያመርት ኩባንያ ማስታወቂያን ጨምሮበት “አውሮፕላኔን ከሰከስኩ” በሚል ርዕስ ከሁለት ዓመታት በፊት ዩቲዩብ ላይ ቪዲዮ ጭኗል።
ቪዲዮ እንደወጣ አንዳንድ ተመልካቾች ትንሿ አውሮፕላን የተከሰከሰችው ድንገት ባጋጠመ አደጋ መሆኑን ሲጠራጠሩ ነበር።
ጄኮብ ቀድሞዉን ፓራሹት አጥልቆ መሳፈሩን እንዲሁም አውሮፕላኗን ከአደጋ ለማዳን ምንም አይነት ጥረት አለማድረጉን በመጥቀስ ሆነ ብሎ አውሮፕላኗን ከስክሷል ሲሉ ተደምጠው ነበር።
ጄኮብ ክስተቱን ለአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ ሪፖርት ያደረገ ሲሆን፣ ባለሥልጣኑም የአውሮፕላኗን ስብርባሪ መሰብሰብ እንዳለበት ሲነገረው አውሮፕላኗ የት እንደወደቀች እንደማያውቅ ገልጾ ነበር ተብሏል።
ከዚያ ግን ወደ አደጋው ስፍራ በሄሊኮፕተር በመሄድ ስብርባሪውን አግኝቶ ከስፍራው እንዲነሳ አድርጎ ማስረጃዎችን ማጥፋቱን የዐቃቤ ሕግ መረጃ አመልክቷል።